ስምምነቱ ጦርነቱን ያስቆመው ይሆን?

0
123

የሩሲያ እና  የዩክሬን ጦርነት  ከተጀመረ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከሰሞኑ  የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሀገራቸው ይህ ጦርነት በፍጥነት ብቻ ሳይሆን በፍትሐዊነት እንዲጠናቀቅ ፍላጎት እንዳላት አሳውቀዋል፡፡ በሕዝብ ብዛት፣ በግዛት ስፋት እና በኢኮኖሚ ከሩሲያ በእጅጉ የምታንሰው ዩክሬን ሦስት ዓመታቱን የጦርነት ዘመን የዘለቀችው በአሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ እና በአውሮፓዊያኑ እገዛ ነበር፡፡ ሆኖም የአሜሪካ የእርዳታ ዕጆች ቢታጠፉ ምን ትሆናለች? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ሰሞኑን የሚታየው የሁለቱ ሀገራት እሰጥ አገባም ለዚህ ሰሞነኛ ጥያቄ መነሻ ምክንያት ሆኗል፡፡

የአሜሪካ እና የሩሲያ ባለስልጣናት የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ  ፊት ለፊት ተገናኝተው ለመወያየት ችለዋል። የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለምታካሂደዉ ጦርነት ተጠያቂ ናት ሲሉም ወንጅለዋል።

ቢቢሲ እንደዘገበው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ሀገራቸው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሰላም አስከባሪዎችን በዩክሬን መስፈርን በፍጹም እንደማትቀበለው መግለጻቸውን ተከትሎ ትራምፕ ለጦርነቱ ጅማሮ ዩክሬንን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ “በፍፁም ጦርነቱ መጀመር አልነበረበትም፤ ስምምነት ማድረግም ይቻል ነበር” ብለዋል። ትራምፕ በሳዑዲ አረቢያ የአሜሪካ እና የሩሲያ ባለሥልጣናት የሰላም ንግግር ካደረጉ በኋላ  በሰጡት አስተያየት ጉዳዩ ከፍተኛ መተማመን እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን አቻቸውን ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን “አምባገነን” በማለትም ጠርተዋቸዋል። በመካከላቸው ያለው ልዩነት  የሰላሙ ድርድር ከተጀመረ በኋላ እየሰፋና እየጠነከረ መምጣቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ትራምፕ ሰሞኑን ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን  የአሜሪካን ገንዘብ እንደወሰዱ በማንሳት ሀገሪቱንም “ማለቂያ በሌለው ግጭት ውስጥ አስገብተዋታል” በማለት በዩክሬን መሪ ላይ የቃላት  ጥቃት ሰንዝረዋል።

አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ድርድር ማድረጓን ተከትሎም የአውሮፓ መሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል፡፡ ጉባኤው በፈረንሳይ እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ  ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን ለመቋጨት የሚያስችል ንግግር ለመጀመር ቃል መግባታቸውን ተከትሎ አሜሪካ እና ሩሲያ የሚያቀርቡትን ማንኛውንም የሰላም ስምምነት ሀገራቸው ካልተሳተፈችበት እንደማይቀበሉ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ አስጠንቅቀዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩሲያ አቻቸው ፑቲን ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ጦርነቱን ለማቆም ጥሩ እድል እንዳለ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

ለሁለቱ ሀገራት የጦርነት መንስኤ የሆነውን የዩክሬን ኔቶን የመቀላቀል ጥያቄ  አፈር ከድሜ የቀላቀሉት ትራምፕ የዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል መሆን የማይታሰብ እንደሆነ ነው ያሳወቁት፡፡ የዩክሬን “ከወረራው በፊት ወደነበረችበት ድንበር መመለስም የማይመስል ነገር ነው” በማለትም የዜሌንስኪን ተስፋ አጨልመዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ዜለንስኪ አጋሮች የሆኑት  አውሮፓውያን ጭምር  ይህንን የትራምፕ እና የሩሲያ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያርጉትን ውይይት በስጋት እንዲያዩት አድርጓቸዋል፡፡  የእንግሊዝ  የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሌይ “ከዩክሬን ውጭ ስለ ዩክሬን ምንም አይነት ድርድር ሊኖር አይችልም። የዩክሬን ድምጽ የየትኛውም ንግግሮች ማዕከል መሆን አለበት” ማለታቸውን ቢቢሲ በዘገባው ጠቁሟል፡፡

ቀደም ሲል  ትራምፕ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም ካልቻሉ በሩሲያ ላይ ከፍተኛ ታሪፍ እና ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ፑቲን በበኩላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረውን ጦርነት ለማስቆም ለመደራደር መዘጋጀታቸውን ደጋግመው መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡  ይህ የሚሆነው ግን 20 በመቶ የሚሆነውን መሬቷን በሩሲያ የተነጠቀችው ዩክሬን ግዛቷን የመነጠቁን እውነታ መቀበል ስትችል ብቻ መሆኑን ፑቲን ተናግረዋል፡፡ ዩክሬን ኔቶን እንድትቀላቀልም ፍላጎታቸው እንዳለሆነ አሳውቀዋል፡፡

ሰሞኑን በሳዑዲ አረቢያ የተገናኙት የአሜሪካ እና የሩሲያ ባለሥልጣናት (ተወካዮች) የሁለቱን ሀገራት ትስስርን ለማሻሻልና የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ጥረት ለማድረግ መስማማታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ከትራምፕ መመረጥ በኋላ በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ላይ መጠነ ሰፊ ለውጥ ተደርጓል፤ ይህን ተከትሎም ሩሲያና አሜሪካ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማቆምና ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ለመጀመር ተስማምተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሁለቱ ወገኖች ሦስት ግቦችን ለማሳካት ተስማምተዋል። ይኸውም በዋሺንግተን እና ሞስኮ በሚገኙ ኤምባሲዎቻቸው ውስጥ የሠራተኞችን ብዛት መልሶ ለማቋቋም፣ የዩክሬንን የሰላም ውይይት የሚደግፍ ከፍተኛ ቡድን ለመፍጠርና የጠበቀ ግንኙነት እና የምጣኔ ሀብት ትብብርን ለመመርመር ነው የተስማሙት።

ላቭሮቭ የሩቢዮን አስተያየት በማስተጋባት ለጋዜጠኞች “ውይይቱ በጣም ጠቃሚ ነበር” ብለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሩሲያና አሜሪካ መካከል ያለው ትስስር በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ልዩነት ሩሲያ እ.አ.አ በ2014 ክሬሚያን ከዩክሬን ከወሰደችበት ጊዜ አንስቶ እየሰፋ የመጣ ሲሆን ሞስኮ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ተባብሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሀገራቸው በአሜሪካ እና ሩሲያ መካከል በተካሄደው ውይይት እንድትሳተፍ ባለመጋበዟ ምክንያት እንደማትቀበለው ነው የገለጹት፡፡ እንደሚታወቀው አሜሪካ ከአውሮፓ ሀገሮች ጋር በማበር በሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ለማድረስ በዓለማችን ከፍተኛ የተባለ ማዕቀብ ጥላለች፡፡ ኤምባሲዎችን በመዝጋት፣  ዲፕሎማቶችን በማባረርና በሌሎች እገዳዎች ከባድ ጉዳት አድርሳባታለች፡፡

ከዚህ ሁሉ በኋላ ታዲያ ጦርነቱን ለማስቆም በሚል የአሜሪካ እና ሩሲያ ባለስልጣናት ተገናኝተው የመከሩት፤ የክሬምሊን  ቃል  አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮፍ ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር ሁሉንም ስሌቶች በጠበቀ መልኩ ውይይቱን እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ባላባራው ጦርነት ምክንያት የሩሲያ  ኢኮኖሚ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እያጋጠመው እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ይህም ሩሲያ  በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ   ሊገታው  ይችላል ሲል የዘገበው ናይንቲን ፎርቲ ፋይቭ (www.19fortyfive.com) የተባለው ድረ ገጽ ነው፡፡

ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን በጽኑ እየተቃወሙት የሚገኙት ትራምፕ ከሰሞኑ “አምባገነን”  ሲሉም ወርፈዋቸዋል፡፡ የሰሞኑ የትራምፕ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ የያዙት አቋም የአውሮፓ ሀገራትን አስደንግጧል፡፡ ዩክሬንም ሆነ አውሮፓ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በሚመራው ልዑካን መካከል ከሳዑዲ አረቢያ የሰላም ውይይት ላይ እንዳይገኙ በመደረጋቸው ቅሬታ ተሰምቷቸዋል፡፡

ትራምፕ ዜሌንስኪን የዘለፉበት አካሄዳቸው እና ንግግራቸው  ከደጋፊዎቻቸው ሳይቀር  ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል፡፡ ለአብነትም የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቦሪስ ጆንሰን ቭላድሚር ፑቲን ጦርነት ጀምረው እያለ ዩክሬንን ተወቃሽ ማድረግ  “አሜሪካ በፐርል ሃርበር ጃፓን ላይ ጥቃት ሰነዘረች” እንደ ማለት ነው ሲሉ የትራምፕ ንግግር ላይ ተሳልቀዋል፡፡

ጆንሰን እንዲህም ብለዋል፥ “እርግጥ ዩክሬን ጦርነቱን አልጀመረችም። ነገር ግን አሜሪካ ፐርል ሃርበር ላይ በጃፓን ላይ ጥቃት እንደሰነዘረች ልትናገር ትችላለህ” ሲሉ የትራምፕን ንግግር አጣጥለዋል፡፡ ጃፓን እ.አ.አ ታኅሣሥ 7 ቀን 1941 በሃዋይ በሚገኘው ፐርል ሃርበር በተባለ የአሜሪካ የባሕር ኃይል ሰፈር ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሯ ይታወቃል። በአሜሪካ ፓስፊክ መርከቦች ላይ በደረሰው ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ጦር ሠራተኞች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል። አራት የአሜሪካ ጦር መርከቦች ሰጥመዋል፤ ወደ 200 የሚጠጉ አውሮፕላኖችም ወድመዋል። ይን ተከትሎም የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት በቀጣዩ ቀን በጃፓን ላይ ጦርነት በማወጅ አሜሪካ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ልትገባ ችላለች።

የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ትራምፕ  ዜሌንስኪን አምባገነን ብሎ መጥራት “ሐሰተኛና አደገኛ” እንደሆነ ተናግረዋል። የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በበኩላቸው ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን እና የዩክሬንን ዴሞክራሲ ለመደገፍ ወደ ዩክሬን ለመጓዝ ማቀዳቸውን አሳውቀዋል፡፡።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here