የሀገራችን እግር ኳስ ፌደሬሽን ከሚያስተዳድራቸው የሊግ ውድድሮች በተጨማሪ “የኢትዮጵያ ዋንጫ” አንዱ ነው።
ይህ መድረክ ከፕሪሚየር ሊግ እና ከከፍተኛ ሊግ ውድድሮች ጎን ለጎን የሚደረግ ተጨማሪ የውድድር ስርዓት ነው።
በቀድሞ ስያሜው “የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ” ሲባል የነበረው ውድድር ዘንድሮ ስሙን እና ቅርጹን ለውጦ በአዲስ መልኩ ተጀምሯል። ባሳለፍነው የጥቅምት ወር መጨረሻ “የኢትዮጵያ ዋንጫ” የሚል ስያሜን ይዞ ነው የተጀመረው። ውድድሩ ከተጀመረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን እድሜ በላይ አስቆጥሯል። ውድድሩ በየጊዜው በተለያዩ ምክንያቶች ቢቆራረጥም በ1945 እ.አ.አ ነው የተጀመረው።
የመጀመሪያውን የመድረኩ ዋንጫ አሸናፊው ክለብም ብሪቲሽ ሚሊተሪ ሚሽን እንደነበረ የታሪክ ማህደሩ ያስረዳል። አርሚ ፣ቢዲጋርድ ፣ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻልን የመሳሰሉ ክለቦችም ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልኩ እስከ ተዋቀረበት ጊዜ ድረስ ዋንጫውን ካሳኩት መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
በ1990 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልኩ ከተደራጀ በኋላ ላለፉት ዓመታት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ብቻ ናቸው በመድረኩ ሲሳተፉ የቆዩት። የዚህ ውድድር አሸናፊ የሆነው ክለብም በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ውድድር የሚሳተፍበትን እድል ያገኛል።
የኢትዮጵያ ዋንጫ ለመጨረሻ ጊዜ የተከናወነው በ2010 ዓ.ም ነው። ከዛ ወዲህ ባሉት ዓመታት ግን በተለያየ ምክንያቶች ውድድሩ አልተከናወነም።
ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደውን የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከነማን በማሸነፍ በአፍሪካ መድረክ መሳተፍ ችሏል።
የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ እርከን ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልኩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ዓመታት ቅዱስ ጊዮርጊስ የመድረኩን ዋንጫ 4 ጊዜ በማንሳት ቀዳሚ ባለ ታሪክ ክለብ ነው።መቻል ደግሞ 3 ጊዜ ዋንጫውን አሳክቷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሀዋሳ ከነማ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ሙገር፣ደደቢት፣ ሀረር ቢራ እና ወላይታ ዲቻ ዋንጫውን የወሰዱ ሌሎች ክለቦች ናቸው።
ይህ መድረክ ዘንድሮ ሲመለስ አዲስ የውድድር ቅርጽ ይዞ በመምጣት የተሳታፊ ክለቦች ቁጥርም ከፍ እንዲል አድርጓል።
ውድድሩ ከዚህ በፊት የከፍተኛ ሊግ ክለቦችን የማሳተፍ እቅድ ይዞ ሳይሳካ መቅረቱ አይዘነጋም። ዘንድሮ ግን ዕቅዱ ሰምሮ በሀገሪቱ የሁለተኛ የሊግ እርከን የሚገኙ ክለቦች እየተሳትፉ ነው።
የከፍተኛ ሊግ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ውድድር እርስ በእርሳቸው ተገናኝተው የበረቱት እና አሸናፊዎቹ በሁለተኛው ዙር መርሀ ግብር ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር በጥሎ ማለፉ እንደሚጫወቱ በውድድሩ ሕግ ተቀምጧል።
በዚህ መሰረትም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 32ቱ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች በዚህ መድረክ ተካፋይ ሆነዋል። ወደ ሁለተኛው ዙር ያለፉ ክለቦችም ተለይተው ታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዋንጫ ተቋርጦ በነበረበት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ክለቦች በአፍሪካ መድረክ እንደተሳተፉ አይዘነጋም።
ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ግን የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው ክለብ ነው በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ የሚሳተፈው። ይህ ውድድር በቀደሙት ጊዜያት የተለያዩ ችግሮች የነበሩበት ቢሆንም ለብሔራዊ ቡድን፣ለክለቦች እና ለተጫዋቾች ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንደነበረው የእግር ኳስ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ።
በአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊጎች፣ ክለቦቹ እንደየ ደረጃቸው የሚፎካከሩበት፣ በየ ዓመቱ የሚከናወን ቋሚ የውድድር መድረኮች እንዳሉ ይታወቃል።
ለአብነት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የፕሪሚየር ሊጉ ፣ የኤፍኤ እና የካራባው ዋንጫ ሲኖር ጥቂት ክለቦች ደግሞ በአውሮፓ መድረክ በቻምፒዮንስ ሊግ እና ኢሮፓ ሊግም ይሳተፋሉ።
ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባትም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወት አንድ ቋሚ ተሰላፊ ተጫዋች በአማካኝ በዓመት ውስጥ ከ40 በላይ ጨዋታዎችን የማከናወን ሰፊ እድል እንዳለው Research Gate የተባለ የእግር ኳስ አጥኚ ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ይህ ደግሞ ተጫዋቾቹ ጠንካራ የአካል ብቃት፣ ትልቅ የአሸናፊነት መንፈስ እና እንደ አለት የጠነከረ ስብዕና እንዲኖራቸው ያግዛል። በዚህም ክለቦቹ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ቡድኖችንም ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ይላል ጥናቱ።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዓመት ውስጥ 30 ጨዋታዎች ብቻ ናቸው የሚከናወኑት። ከዚህ ውጪ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ውጪ ተጨማሪ ውድድር የሚያገኙበት እድል አነስተኛ ነው። ለብሔራዊ ቡድኑ የሚመረጡ ተጫዋቾችም በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ የተሻሉ ብቃት ያሳዩት እንደሆኑ ይታመናል። በየጊዜው ለብሔራዊ ቡድኑ የሚመረጡ ተጫዋቾች ከሌሎቹ አቻ ቡድኖች ጋር ሲነፃፀሩ ጠንካራ የአካል ብቃት እና ወጥ የሆነ አቋም እንደሌላቸው ብዙዎቹ ይመሰክራሉ።የተጫዋቾች የጉዳት ሰለባ መሆን በብዙ ጨዋታዎች ተፈትነው ወደ ብሔራዊ ቡድኑ አለመምጣታቸው እንደ አንድ ምክንያት ይነሳል።
አሁን ግን ተቋርጦ የቆየው የኢትዮጵያ ዋንጫ መጀመሩ ለብሔራዊ ቡድኑ የሚመረጡ ተጫዋቾች በበርካታ ጨዋታዎች ተፈትነው እንዲያልፉ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል። ተጫዋቾችም ለብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ ራሳቸውን የሚያበቁበት እና የሚያሻሽሉበትን አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።
በዚህ ውድድር የሚሳተፉ በየደረጃው ያሉ ክለቦችም ተጠቃሚ ናቸው ተብሎ ይታመናል። ከተጠቃሚዎቹ መካከል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ይገኙበታል። ዘንድሮ እንኳ እነዚህ ክለቦች ይህን ውድድር ለ2016 ዓ.ም የከፍተኛ ሊጉ ውድድር እንደ አቋም መፈተሻ ጨዋታ ተጠቅመውበታል:: ባለፉት ዓመታት ጥቂት የማይባሉ ክለቦች ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደጉበት ዓመት ወደ መጡበት የታችኛው የሊግ እርከን መውረዳቸው አይዘነጋም።ለአብነት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ለገጣፎ ለገዳዲን ማንሳት ይቻላል። በዚህ ዓመትም ሻሸመኔ ከተማ ሊጉን ለመልመድ እየተቸገር ስለመሆኑ እያስተዋልን ነው።
ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለሚመጡ ክለቦችም የኢትዮጵያ ዋንጫ በትንሹም ቢሆን የካበተ ልምድ ካላቸው ክለቦች ጋር የመጫወት እድሉን እንዲያገኙ እና ልምድ እንዲወስዱ ያግዛቸዋል።ከሜዳ ላይ ባለፈ በስነ ልቦና እና በአካል ብቃት ዝግጁ ሆነው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲመጡም ይረዳቸዋል።
የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እና በሊጉ ለመቆየት በሚደረገው ትንቅንቅ ምክንያት አብዛኞቹ አሰልጣኞች ለታዳጊ ተጫዋቾች ተደጋጋሚ የመሰለፍ እድል ሲሰጡ አይታዩም።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባስቀመጠው ሕግ መሰረት እያንዳንዳቸው የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በአረንጓዴ እና በቢጫ ቴሴራ አምስት ተጫዋቾችን በዋናው ቡድን ውስጥ ማካተት እንዳለባቸው ሕጉ ያትታል።
ነገር ግን አብዛኞቹ ታዳጊ ተጫዋቾች በነጥብ ጨዋታ የመሰለፍ እድል ሲያገኙ አንመለከትም:: የኢትዮጵያ ዋንጫ ለእነዚህ ታዳጊዎች ራሳቸውን የሚያሳዩበት ትልቅ አጋጣሚ ይሆናል። ሌሎቹ የመሰለፍ እድል የማያገኙ ነባር ተጫዋቾችም ቢሆኑ ራሳቸውን የሚያሻሽሉበት እና የሚያበቁበት ውድድር እንደሚሆን ይገመታል።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ባለፉት ዓመታት በመድረኩ የታዩ ችግሮች ተቀርፈው የተሻለ የውድድር ስርዓት ሲዘረጋ ነው።
ውድድሩ በየጊዜው ሲቆራረጥ እንደ ነበር ያገኝነው መረጃ ያመለክታል።በ1990 እና 1991 ዓ.ም አለመከናወኑም በታሪክ ማህደሩ ተቀምጧል። በቅርቡ በ2010 ዓ.ም ደግሞ ውድድሩ ቀደም ብሎ ባለመጀመሩ ዘግይቶ ነበር የተጠናቀቀው ።በወቅቱ ክረምት በመግባቱ እና የመጫዎቻ ሜዳው በመበላሸቱ በጊዜው ለመርሀ ግብሩ መቆራረጥ እንደ ምክንያት ተነስቷል።
ዳኞችም ቢሆኑ ይህንን ውድድር ትኩረት አለመስጠታቸው ሲያስተቻቸው ቆይቷል። እነዚህ እና መሰል ችግሮች ከተቀረፉ የኢትዮጵያ ዋንጫ ከውድድር ስርዓትነትም አልፎ የሀገራችንን የእግር ኳስ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም