ስብራቱን ለመጠገን ሁላችንም እንረባረብ!

0
19

የተሻለ ነገን ማለም የሰው ልጆች ሁሉ ራዕይ እና ፍላጎት ነው። ይህን ራዕይ እና ፍላጎት ለማሳካት ደግሞ ዘመኑን የዋጀ ዕውቀት እና ክህሎትን ይጠይቃል። ለዚህም ዋና ምሰሶው ትምህርት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ትምህርት መሠረታዊ ዕውቀትን ለማስጨበጥ፣ የአገርን ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማቀላጠፍና ሁሉን አቀፍ ልማትን ለማስፈን፣ የሰው ልጅን በአስተሳሰብ፣ በአመለካከትና በችሎታ ለማነፅ የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ ነው።

ትምህርት ለሁሉም ዕውቀቶች፣ ግኝቶች፣ ጥበቦች፣ ቴክኖሎጂዎችና ሌሎች መሠል ውጤቶች መሠረት በመሆኑ ይህ ቁልፍ መሣሪያ ለሁሉም ዜጎች በወቅቱ እና በየደረጃው ሊሰጥ ይገባል። ለዚሕም ይመስላል የሐገሬው ማሕበረሰብ  ገና ድሮ ትምሕርት ሳይስፋፋ ጀምሮ የትምሕርትን አስፈላጊነት በፅኑ  ያመነው።

በዚሕ እሳቤውም ምንም እንኳን ‘እኔ ባልማርም ልጀ ተምሮና ተመራምሮ ኑሮየን ያሻሽልልኛል፤ ጎስቋላ ሕይወቴን ይታደግልኛል’ በማለት እንዲሕ እንደ አሁኑ የትምሕርት ተቋማት በአካባቢው ሳይከፈቱ በፊት ልጆቹ ከሩቅ ወዳለው ትምህርት ቤት ተራራውን ወተው፣ ወንዙን አቋርጠው እንዲማሩ ስንቃቸውን በአገልግል አስይዞ በመላክ ያስተምር የነበረው።

አገሬው ልጆቹ ትምሕርትን እንዲወዱትም ስለ ትምሕርት ጠቀሜታ እና አስፈላጊነት በስነ ቃሎቹ እና በምሳሌያዊ ንግግሮቹ ሳይቀር ይሰብክ ነበር።

ተማር ልጄ ተማር ልጄ፣

ወዳጅ ዘመድ የለኝ ሀብት የለኝም ከእጄ፡፡

ተማር ልጄ ልብ ዐይን ነው፣

ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው!

ያለመሠረት ቤት፣ ያለ ትምህርት ዕውቀት  የለም!

ትምህርት የማያልቅ  ሀብት ነው! በሚሉና በመሠል መልዕክቶች ልጆቹ ትምህርትን እንዲወዱትና እንዲያከብሩት በማድረግ የትምሕርትን ወሳኝነት በአፅንኦት ሰብኳል። ልጆቹንም እድሜያቸው ለትምሕርት ሲደርስ ከትምሕርት ይቅሩና እኔን በሥራ ያግዙኝ ሳይል ወደ ትምሕርት ቤቶች በመላክ እሱ ያጣውን ዕውቀት ልጆቹ እንዲቀስሙ በማድረግ የወላጅነት ኃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል። እየተወጣም ነው፡፡

ሁሉም ዜጎች ትምሕርትን የማግኘት መብት እንዳላቸው እና ትምሕርት ሰብዓዊ መብት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መካከል በአንቀፅ 26 ላይ ተጠቅሷል።

በዚህ አንቀፅ እንደተመለከተውም ሁሉም ዜጋ ትምሕርት የማግኘት መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ ነው። ከዚሕ ባሻገርም ትምሕርት ከሰብዓዊ መብትነት ባለፈ ለሌሎች የሰብዓዊ መብቶች መከበርም የጎላ ድርሻ እንዳለው አመላክቷል።

ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልላችን በተከሠተው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የትምህርት ዘርፉ እክል  ገጥሞት በርካታ ተማሪም ከትምሕርት ገበታ ርቋል። ይሕም በትምህርት ዘርፉ  ላይ ከፍተኛ ስብራትን  አድርሷል።

ይህንን ስብራት ለመጠገንም የክልሉ መንግሥት ሥራወችን ሲሰራ ቆይቷል፤ እየሠራም ይገኛል። ስብራቱ በቶሎ እንዲጠገንና ወደ ነበረበት እንዲመለስም ከመንግሥት በተጨማሪ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ርብርብ በማድረግ ትምሕርትን መታደግ የወቅቱ ዐቢይ ተግባር ነው።

የተከሠተው የፀጥታ መደፍረስ በርካታ ተማሪዎችን ከትምህርት አፈናቅሏል። በዚህም  በርካታ ችግሮች በተማሪዎችና በወላጆች ላይ ተከስቷል። ይህን ችግር ለመቅረፍም በተደረገው ርብርብ ዘንድሮ ቁጥራቸው ከአምናው የሚበልጡ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምሕርት ጀምረዋል። በተመሳሳይ በ2017 የትምህርት ዘመን በነበረው የተቀናጀ ሥራ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከተፈተኑት መካከል ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር ከአምናው የተሻለ ሆኗል። ተፈታኞች የወቅቱ ችግር ሳይበግራቸው በዓላማ ፅናት ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው የተሻለ ውጤት በማምጣቸው የክልሉ ትምሕርት ቢሮ ዕውቅና እና ማበረታቻ ከሰሞኑ ሰጥቷቸዋል።

አገር የምትሠራው እና የምትለማው  በተማረ እና በስነ ምግባር በታነፀ በተሟላ ዕውቀት እና ሰብዕና ባለው ወጣት በመሆኑ የክልሉን ሁኔታ ተገንዝበው ለራሳቸው፣ ለቤተሠቦቻቸው እና ለአገራቸው ክብር እና ኩራት ከፍተኛ ውጤትን ላስመዘገቡ  ታታሪ እና ምጡቅ ተማሪዎች ዕውቅና እና ማበረታቻ መስጠት ውጤቱ ለራስ ነውና ተግባሩ በእጅጉ ይበረታታል።

ተሸላሚዎቹ በቀጣይ ሕይወታቸው ውስጥ ይበልጥ አሸናፊ ሆነው ለመውጣት በተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎችም ውስጥ ሆነው ራሳቸውን በማላመድ በስነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ ዕውቅና እና ሽልማቱን የሰጡት የክልሉ ትምሕርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ  (ዶ/ር)  የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዛሬው አርዓያነታችሁ ለተተኪ እህት እና ወንድሞቻችሁ ትልቅ ኃይል እንዲሆን የዛሬውን ስኬታችሁን በቀጣይ የትምሕርት ዘመንም ይበልጥ እንድታጠናክሩት በማለት አሳስበዋል።

በመሆኑም የዛሬ ተማሪወቻችንን ማበረታታት የነጋችንን ሐኪም፣ መሐንዲስ፣  ዳኛ፣ ካፒቴን፣ መምሕር፣ ጠበቃና  የሌሎች ሙያዎች ባለቤቶችን ለማፍራት ነውና እናበረታታቸው፤ ተከታዮቻቸውም የእነሱን ፈለግ እንዲከተሉ መንገዱን እናሳይ ብለዋል፡፡

ለትምሕርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት  በኩል ወላጆች፣ የትምሕርት ባለሙያዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትምሕርት ዙሪያ በሚሠሩ ልዩ ልዩ ሥራዎች ላይ በመሣተፍ ዘርፉ የደረሠበትን ስብራት መጠገን  ይጠበቅብናል፤ ለተግባራዊነቱ ሁላችንም እንረረብ፤ እንበርታ!!

 

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here