ስብራቱ እንዲጠገን

0
135

ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ክፉኛ እየተጎዳ የሚገኝ ዘርፍ ነው – ትምህርት። ይህ ደግሞ የትውልድ ክፍተትን የሚፈጥር ስብራትን ያስከትላል። የሰሜኑ ጦርነት በስምምነት ቢቋጭም በአማራ ክልል ያለው ግጭት ግን 18 ወራትን ተሻግሯል። ይህም ወትሮውንም በችግር ውስጥ የነበረውን ዘርፍ ይበልጥ እንዲጎብጥ አድርጎታል።

ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ሰባት ሚሊዮን ያህል ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ትምህርት ገበታ መምጣት የቻሉት ከ40 በመቶ የሚያንሱት ናቸው።

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን በተያዘው ወር የመጀመሪያ ሳምንት  ማካሄዱ ይታወሳል። የትምህርት ጉዳይ ደግሞ በአባላቱ ዘንድ ጠንከር ያለ ሐሳብ የተነሳበት ነበር። የምክር ቤት አባላትም አሁን ላይ የክልሉ የትምህርት ሥራ እንቅፋት ገጥሞታል ብለዋል። “በመሆኑም የክልሉን ሰላም በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ በማረጋገጥ የትምህርት ሥራው እንከን እንዴት ይፈታ? የሚል ጥያቄ ከአባላት ተነስቷል፡፡

በግጭት ውስጥ ያለፉ እና በትምህርት ላይ ስብራት የገጠማቸው ሀገራት በሁሉም ዘርፍ ወደ ፊት መራመድ እንዳልቻሉ ታሪካቸው ያሳያል። ይህ የሚያመላክተው ታዲያ ትምህርት የሁሉም ዘርፎች ዕድገት ቁልፍ መሆኑን ነው። በኢትዮጵያም በትምህርት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ፈጥኖ መፍታት ካልተቻለ ዳፋው የከፋ ይሆናል።

ኮንሰርን ወርልድ ዋይድ (www.concernworldwide.com) የዓለም ሀገራትን የትምህርት ሁኔታ በጥናት አስደግፎ ይፋ እንዳደረገው በርካታ ሀገራት በግጭት ምክንያት የከፋ ጉዳት አስተናግደዋል፣ እያስተናገዱም ነው። ከጉዳቱ ሁሉ የከፋው ደግሞ በትምህርት ላይ የደረሰው መሆኑን አብነቶችን በማንሳት አብራርቷል። አፍጋኒስታን፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ደግሞ በቅደም ተከተል የትምህርት ስብራት የገጠማቸው (የትምህርት ሥርዓታቸው ክፉኛ የተጎዳ) ሀገራት ሲል ጠቅሷቸዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት ሚሊዮኖች ከትምህርት ገበታ ከመፈናቀላቸው ባለፈ በርካቶች ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲፈጽሙ ተገደዋል፡፡ ከዚያም አለፍ ሲል በደረሰባቸው ሥነ ልቦናዊ  ስብራት ምክንያት ራሳቸውን ያጠፉ እንዳሉ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያስጠናውን ጥናት ዋቢ አድርጎ ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።

በሌላ በኩል ትምህርት ሚኒስቴር ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በሀገራችን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ90 በመቶ በላይ ከደረጃ በታች ናቸው። ይህ በሆነበት ግጭቱ ዳፋውን ሲያሳርፍበት ታዲያ ስብራቱ ይከፋል።

ከሰሞኑ በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ከአባላት የተነሳውን ሀሳብ ርእሰ መስተዳድሩ ይጋራሉ፡፡ የክልሉ ሕዝብ ልጆቹን የማስተማር ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አቶ አረጋ፤ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ግን የዘርፉ ሳንካ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በግጭት ምክንያት ከተጎዱ ዘርፎች ውስጥ ትምህርት አንዱ ነው፤ ለአብነትም የትምህርት ዘርፍ የዕድገት ምጣኔ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እየቀነሰ መጥቷል። የ2016 በጀት ዓመት የትምህርት ዘርፍ ዕድገትን በማንሳትም ዘርፉ በእጅጉ መጎዳቱን ጠቁመዋል።

የዝቅተኛ ዕድገት ምጣኔው መነሻ ክልሉ የገጠመው ተከታታይ ግጭት እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መምጣት አለመቻላቸው እንደሆነም አስገንዝበዋል።

“የትምህርት መቋረጥ የትውልድ ቅብብሎሽን የሚገታ ታላቅ ስብራት ነው፤ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በጉልህ መክሮ አቅጣጫ ሊያስቀምጥለት ይገባል” ሲሉም ነው ዘርፉ የደረሰበትን ከፍተኛ ጉዳት የገለጹት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ 3ኛ ዙር የተማሪ ምዝገባን በማካሄድ የማካካሻ ትምህርት ጊዜንም በማመቻቸት እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በጎንደር ከተማ በተካሄደበት ወቅት የተገኙት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ኢየሩስ መንግሥቱ “ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይመጡ በማድረግ የሚገኝ ድልም ሆነ ዕድል የለም” ብለዋል።

በሰላም መደፍረስ ምክንያት ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ መመዝገባቸውን ያስታወሱት ወ/ሮ ኢየሩስ ከተመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በክልሉ ለሁለት ዙር የተማሪዎች ምዝገባ የካሄደ ሲሆን ያልተመዘገቡ ተማሪዎችን ለመመዝገብ እስከ የካቲት 30 ቀን 3ኛ ዙር ምዝገባ ይቀጥላል።

ዘግይተው ወደ ትምህርት ተቋማት ለገቡ ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት ይሰጣል። ትምህርት ያልጀመሩ አካባቢዎችን ለማስጀመር በትኩረት ይሠራል። ማስተማር አቁመው የነበሩ ትምህርት ቤቶችም ወደ ማስተማር እየተመለሱ ነው።

በቅርቡ ወደ መማር ማስተማር ከተመለሱት መካከል ታዲያ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ኤልያስ ወረዳ የትግል ፍሬ የመጀመሪያ ደረጃ  ት/ቤት አንዱ ሲሆን በየካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራውን መጀመሩን ከከተማው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በትምህርት አጀማመሩ ላይ የተገኙት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ሀብታሙ እሱባለው በወረዳው ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የፀጥታ ችግር ምክንያት መደበኛ የመማር ማስተማር ስራው  ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሀገር ተረካቢ ህፃናትን ማስተማር ፖለቲካ አለመሆኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው በተለይም ትምህርት የጠማቸው ህፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ  ሕብረተሰቡ ልጆቹን ወደ ት/ቤት ከመላክ ባሻገር  ሌሎችንም  ድጋፎች በማድረግ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ  ጠይቀዋል።

ከሰሞኑ በተካሄደው መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ መማር እያለባቸው በሰላም እጦት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን አንስተዋል። “የልጆች ከትምህርት ገበታ ማቋረጥ ወላጅ የሆነን ሁሉ ሊያሳስብ ይገባል” ብለዋል።

በመሆኑም ሰላምን ማረጋገጥ እና ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት  በሙሉ እንዲማሩ በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የክልሉ መንግሥት በትምህርት ዘርፍ ልዩ ልዩ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን የጠቀሱት ደግሞ ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ናቸው። ለአብነትም የትምህርት ግብዓት ማሟላት እና የመማሪያ ክፍሎችን መገንባትን እና ማደስን ተጠቅሰዋል።

የጸጥታ ችግሩ መጻሕፍትን ለተማሪዎች የማሰራጨት ሂደቱን ጭምር እያወከ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ አረጋ መሰናክሎችን በመቋቋም አብዛኛውን መጻሕፍት እና ሌሎችንም የትምህርት ቁሳቁስ ለማሰራጨት ሰፊ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here