ከጠቅላላ ሰውነት ሁለት በመቶ ብቻ የሚመዝነው አዕምሮ በሰውነት ውስጥ ካለው ጠቅላላ የደም አቅርቦት ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን ይወስዳል። በዚህም የደም ዝውውር አማካኝነት አዕምሮ ኦክስጅንን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ያገኛል። ይህ ሂደት ለአፍታም ቢሆን እንዲቋረጥበት አያስፈልግም። ደም ሲቋረጥ የአዕምሮ ተግባርም አብሮ ቀጥ ይላልና።
በተለያዩ ምክንያቶች በአዕምሮ ድንገት (ድንገተኛ) ችግር ሲፈጠር ስትሮክ ይከሰታል። ስትሮክ ሁለት ዓይነት ሲሆን አንዱ የደም ስር ሙሉ በሙሉ መዘጋት ሲሆን ሁለተኛው በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ አደጋ ካጋጠመ ነው:: ይህ ማለት ወደ አዕምሮ የሚሄደው ደም እንዲስተጓጎል ስለሚያደርግ እንደሆነ በፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እና የማህበረሰብ ጤና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሸጋው ማሩ ይገልፃሉ::
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃም እንደሚለው ስትሮክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለተኛው ገዳይ በሽታ ነው። ድርጅቱ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 15 ሚሊዮን ሰዎች በስትሮክ እንደሚያዙ፣ አምስት ሚሊዮን ሰዎች በዚሁ ሰበብ እንደሚሞቱ እና ሌሎች አምስት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ለቋሚ የአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ማሳወቁን ቢቢሲ ዘግቧል::
በባሕር ዳር የፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል በውስጥ ደዌ ህክምና ከፍተኛውን ቁጥር እየያዘ የመጣ እና ከፍተኛ የሞት መጠንንም እየጨመረ መሆኑን ስፔሻሊስቱ ተናግረዋል:: ስትሮክ በሀገራችን ተላላፊ ካልሆኑ 10 በሽታዎች አንዱ መሆኑንም ዶ/ር ሸጋው ማሩ አስረድተዋል::
ቀደም ባሉት ዓመታት ስለበሽታው ግንዛቤ ስላልነበር ሰዎች ግማሽ ሰውነታቸው ሲሰንፍ ወደ ተለያዩ የአምልኮ ቦታዎች ይሄዱ ነበር:: አሁን ላይ ግን ህብረተሰቡ የበሽታውን መስፋፋት ተረድቶ ወደ ህክምና መምጣት ጀምሯል ያሉት ዶ/ር ሸጋው ስትሮክ ቀድሞ ክትትል ከተደረገ መከላከል የሚቻል በሽታ እንደሆነም ጠቁመዋል::
በአብዛኛው ስትሮክ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ይህም ዕድሜ 60 እና ከዛ በላይ ሲሆን፣ ደም ግፊት፣ ስኳር በሽታ፣ ኮሌስትሮል፣ የልብ ምት መዛባት፣ የደም ሥር መቁሰል ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ ችግር፣ ከፍተኛ ውፍረት፣ ሲጋራ ማጨስ እና አደንዛዥ እፅ መጠቀም ለስትሮክ የመጋለጥ አጋጣሚን ከፍ ያደርጋል። ይላሉ ዶ/ር ሸጋው
ችግሩ በብዛት እድሜያቸው ከፍ ያሉ ሰዎች ላይ ቢከሰትም ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች (አጋላጭ ምክንያቶች) ያለባቸው ሰዎች ላይም በማንኛውም እድሜ ሊከሰት እንደሚችል ስፔሻሊስቱ አስገንዝበዋል::
ደም መፍሰስ የከፋው የስትሮክ ዓይነት እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ሸጋው ይህም ራስ መሳት ለሕይወት አስጊ ነው ብለዋል:: የትልቁ የደም ስር መዘጋት ካልሆነ ግን ጊዜ የሚሰጥ ፣ ለከፋ ጉዳት የማይዳርግ እና በአጭር ጊዜ ህክምና ሊመለስ የሚችል መሆኑንም ጠቁመዋል::
ስትሮክ ቀድሞ መከላከል የሚቻል በሽታ ነው የሚሉት ዶ/ር ሸጋው፤ በሽታው በተከሰተበት ወቅት ድንገተኛ የፊት መቀየር ፣ ልሳን መቆለፍ ፣ራስ ምታት ፣ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ድንገተኛ የጎን አለመታዝ እና መፍዘዝ ምልክቶች ናቸው:: እነዚህ ምልክቶች ወዲያው ሊለቁ ይችላሉ፤ ነገር ግን ይሄ ከስትሮክ በፊት የሚመጣ ማስጠንቀቂያ ስለሆነ በዚህ ወቅት ካልታከመ ስትሮክ ሊከሰት ይችላል::
እንደ ስፔሻሊስቱ ማብራሪያ ግፊት እንዳለባቸው እያወቁ መድኃኒት ያልጀመሩ፣ ስኳር እያለባቸው ክትትል ያላደረጉና በምግብ እቆጣጠራለሁ የሚሉ፣ የኮሌስትሮል ክምችት ኖሮባቸው ያልታከሙ ሰዎች ብዙ ጊዜ ለስትሮክ ይጋለጣሉ:: እድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ ሆነው ሰውነታቸውን ለማስተካከል ስትሮጂን ቴራፒ የሚባል ሆርሞን ትሪትመንት የሚወስዱ ሴቶችም ለስትሮክ የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው::
ስትሮክ በህክምና ለመዳን ሰዓቱ ሳይዘገይ ሲታከም ይገባል ያሉት ዶ/ር ሸጋው በመጀመሪያ ምልክቶቹ እንደታዩ በሦስት እና አራት ሰዓታት ውስጥ መታከም ወሳኝ የሚባሉት ጊዜያት እንደሆኑም ጠቁመዋል:: ስለሆነም በነዚህ ሰዓታት ላይ ህክምና ከተደረገ የአካል ስንፈት (ፓራላይዝ) የሆነው አካል ነርቩ የመመለስ እድሉ ሰፊ ይሆናል ። የጉዳት መጠኑም ሊቀንስ ይችላል። ሰዓታት ባለፉ ቁጥር ግን ነርቭ የመመለስ እድሉ እየቀነሰ ይሄዳል:: ሰዎች መጀመሪያ ወደ ህክምና ጣቢያ ሲመጡ የትኛው አይነት ስትሮክ /መፍሰሱ ወይስ መዘጋቱ/ የሚለው ተለይቶ የተለያየ ህክምና እንደሚሰጥ ነው የገለፁት::
ማህበረሰቡ እድሜ እየጨመረ ሲሄድ በተለይ ከ40 ዓመት በኋላ የስኳር ፣የግፊት…. በሽታዎች ምልክት ባይኖርም የህክምና ክትትል ማድረግ እንደሚገባው ስፔሻሊስቱ መክረዋል:: መድኃኒት ካስፈለገም በጊዜ መጀመር እንዳለባቸው አሳስበዋል::
በማንኛውም እድሜ ጮማና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች ማዘውተር በደም ስር ውስጥ ስብ እንዲከማች እና የደም ስሮች እንዲዘጉ ወይም እንዲጠቡ በማድረግ ስትሮክ እንዲከሰት እንደሚያደርግም ባለሙያው ጠቁመዋል:: የደም ስር ጥበቱ ከፍተኛ በሆነ ቁጥር ጉዳቱም ከፍተኛ ይሆናል። የስብ ክምችቱ በራሱ ጥበትን ያመጣ፤ ደም እንዲረጋም ያደርጋል:: ስለዚህ ጤናማ አመጋገብ ስለሚፈልግ ከመጠጥ ፣ ከአደንዛዥ እፅ …መራቅ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ሸጋው ምክራቸውን ለግሰዋል::
አሁን ያለው አኗኗራችን ቢሮ ውስጥ እና በቤት ውስጥ ቴሌቪዢን ለማየት ረጅም ሰዓት መቀመጥ ፣ በመኪና ብቻ መጓዝ፣ ጤናማ አመጋገብ እና እንቅስቃሴ (ስፖርት) አለመሥራት እንዲሁም በየጊዜው የጤና ምርመራ አለማድረግ በሽታውን ቀድሞ ለመከላከል አዳጋች እንደሚያደርገው ዶ/ር ሸጋው ጠቁመዋል:: ስትሮክ ድጋሚ የመከሰት አጋጣሚ ስላለው መጠንቀቅ፣ እንደ ተከሰተም በሀኪም መታገዘም እንደ ሚገባ መክረዋል::
መድኃኒት ያለማቋረጥ መውሰድ ይገባል፤ ስትሮክ የተከሰተበት ሰው የተወሰነ የአንጎል ክፍሉ በሚደርስበት ጉዳት ሥራ ስለሚያቆም ማስታወሱ ይቀንሳል፣ ባሕሪው ሊቀየር ይችላል፣ የአስተሳሰብ መዛባትም ስለሚኖር ከአካላቸው ባልተናነሰ የሥነ ልቦና ድጋፍ እና መርዳትን ይጠይቃልና አድካሚ ቢሆንም አስታማሚ ቤተሰብ ችግሩን ተረድቶ መድኃኒቱን ሳያቋርጥ እንዲወስድ ማገዝ እንዳለበትም መክረዋል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም