በደብረማርቆስ ከተማ ሽዋ በር በተባለ አካባቢ ነው የተወለደች::በወላጅ አባቷ ሳይሆን በአያቷ ሥም አደይ ሕብስቱ በመባል የምትጠራው የያኔዋ ታዳጊ የመንግሥት ሠራተኛ እናቷ ወደ ባሕር ዳር በመዘዋወራቸው እርሷም አብራ ወደዚሁ መጣች።
ታዳጊዋ አደይ ደብረ ማርቆስ የጀመረችውን ትምህርት በፋሲሎ እና በሌሎች ትምህርት ቤቶች መከታተል ጀመረች::አደይ በተለያዩ ምክንያቶች በባሕር ዳር ብዙም ሳትቆይ ተመልሳ ወዳደገችበት ደብረማርቆስ በመሄድ ከአክስቷ ጋር መኖር ጀመረች::
ጠንካራ የሥራ ሰው እና አሁን ላላት ጥንካሬ መሠረት እንደሆነችላት የምትመሰክርላት አክስቷ ቡና ከወለጋ እያመጣች በመሸጥ ቤተሰቡን ታስተዳድር እንደነበር አደይ ታስታውሳለች::እርሷም ከትምህርት ሰዓት ውጭ ቡና፣ ጨው… የመሳሰሉትን ሸቀጣ ሸቀጦች በመሸጥ አክስቷን ታግዝ ነበር፡፡
በወላጆቿ መለያየት ተረጋግታ መኖር ያልቻለችው ታዳጊዋ ለአቅመ ሄዋን ሳትደርስ ትዳር መስርታ የራሷ ቤተሰብ እንዲኖራት ተመኘች::ህልሟም ዕውን ሆኖ በ14 ዓመቷ ትዳር መሰረተች::ኑሮዋም ትታት ወደ ሄደቻት እናቷ ወዳለችበት ባሕር ዳር መለሳት፡፡
ይሁን እንጅ የአደይ ትዳር እንዳሰበችው ስኬታማ አልነበረም፤ ባለቤቷ ሥራ በመተው ኑሮ ከበዳት::ይሁንና ከአክስቷ እጅን ለችግር መስጠት ሳይሆን ድል ማድረግን ስለተማረች በተከራዩት ግቢ ቤት ውስጥ እንጀራ እየጋገረች በ60 ሣንቲም በመሸጥ የዘመመውን ጎጆ ከመውደቅ ታደገችው፡፡
ከሥራዋ ጎን ለጎን በችግር ውስጥ ሆና የጀመረችውን ትምህርት ሳታቋርጥ 12ኛ ክፍል በመድረስ የሀገር አቀፍ ፈተናን ለመውሰድ በቃች::ባገኘችው ውጤትም በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ የመጀመሪያ ሳይክል መምህርነት (TTI) ስልጠናን አጠናቃ ተመረቀች፡፡
ባለቤቷም የጤና ባለሙያ ነበርና ያቋረጠውን ሥራ እንደገና ጀመረ፤ የቀዘቀዘው ቤታቸው ሞቀ:: ጥንዶች በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ደግሞ አቶ ይፍረድ ዘላለም የተባሉ “ባለውለታዬ” የምትላቸው ግለሰብ የባለቤቷን ሙያ ያውቁ ስለነበር “ ‘በወር 341 ብር ደመወዝ ይዞ ከመኖር በቀን 341 ብር ማግኘት የምትችሉበትን ሥራ ብትቀጥሉ ይሻላል’ በሚል መከሩን” በማለት ታስታውሳለች::ግለሰቡ ከምክር ባለፈ ቤት እና የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ (ወረት) ሰጧቸው::ወ/ሮ አደይ እና ባለቤቷም የተሰጣቸውን ምክር ሰንቅ ገንዘባቸውን ምርኩዝ አድርገው ለሥራ ወደመረጡት ጃዊ አቀኑ፡፡
በግል የህክምና አገልግሎት መስጫ በመክፈት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ባለሙያዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ቻሉ::
ወ/ሮ አደይም ከባለቤቷ ጋር በሙያው ለመሰማራት ወደ ባሕር ዳር በመመለስ በአልካን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለሦስት ዓመታት ክሊኒካል ነርስ በመማር ወደ ጃዊ ተመለሰች::ከህክምናው በተጓዳኝ ጥንዶች በጃዊ ፈንድቃ ከተማ መድኃኒት ቤት በመክፈት ሥራቸውን ማሥፋፋት እና ገቢያቸውን ማሳደግ ቻሉ:: ወ/ሮ አደይ በልጅነቷ ስትናፍቀው የነበረውን ሁሉ ማሟላት ጀመረች፤ መኖሪያ ቤት ሠራች፡፡
ከጤናው ዘርፍ በተጨማሪ በግ ገዝተው በማርባት ለቤትም ሆነ ለሽያጭ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ወ/ሮ አደይ ታስታውሳለች::
“ሥራ እና ገንዘብ ቢኖርም ሁል ጊዜ በረሃ አይኖርም” የምትለው ወ/ሮ አደይ በ1999 ዓ.ም በ250 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 ቤት በመሥራት ከሰባት ዓመታት በኋላ ያፈሩትን ሃብት እና ንብረት ይዘው እንደተመለሡ ታስታውሳለች::
ባሕር ዳር ከተማ ከቤቷ በገባች በዓመቱ ግን ወላጅ እናቷ በድንገት ሕይወቷ በማለፋ ሃዘን ላይ ወደቀች ፤ በዛ የሃዘን ስሜት ላይ እያለች ደግሞ በትዳሯ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ለመለያየት በቃች::ሕይወት ለወ/ሮ አደይ እንደገና ተመሰቃቀለች:: “እየሠራሁ ሥላደግሁ ማግኘትም ማጣትም እንደሚኖር ስለማስብ ማጣቴ፣ ምንም አለመኖሬ… ብዙ አልጎዳኝም::ነገር ግን ከመኖር ወዳለመኖር ሲመጣ በወቅቱ በዙሪያዬ የነበሩ ሠዎች ሲሸሹ መመልከት ግን ይጎዳ ነበር፡፡” በማለት ያን ወቅት ወ/ሮ አደይ ታስታውሰዋለች::
ወ/ሮ አደይ ከገጠማት ችግር ወጥታ ስትረጋጋ የጃዊ ቤት ተሽጦ የደረሳትን ብር በመያዝ ከእናቷ ቤት ግቢ አንድ ክፍል ቤት ገነባች:: ሕይወትን በአዲስ ለመጀመር የቀደመውን ሙያዋን ትታ መንጃ ፈቃድ አውጥታ ባጃጅ በመግዛት ሥራዋን በአዲስ ሙያ ጀመረች::
ከነበራት ሀብት እና ደረጃ ስለወረደች በወቅቱ ታላቅ ወንድሟ “ ሕይወት ከቆመበት ይቀጥላል ወደ ኋላ ተመልሰሽ እንዳታይ” በማለት ወደ ፊት ብቻ እንድትመለከት ስለመከራት ሥራው በወቅቱ አጥጋቢ የሚባል ባይሆንም በሁለት ዓመት ወዳሰበችው ሥራ ለመቀየር መንገድ እንደከፈተላት ዛሬ ትናገራለች:: በአገልግሎት ሥራ ላይ ከገቢው በላይ በትሕትና አገልግሎት ከተሰጠ የሚመሠረተው ወዳጅነት ፣ ምክር እና አስተያየት ገንቢ እንደነበረም ነው የምትገልፀው::
በሁለት ዓመት ውስጥ ባጃጇን በመሸጥ የተረፈውን የቤት ሽያጭ ብር እና እቁብ በመጣል ቢጫ ታክሲ (የኤርፓርት) የሚባሉትን በመግዛት ዛሬ በሙያው ከተሰማሩ በጣት ከሚቆጠሩ ሴቶች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡
ስለመኪና ያላት እውቀት አነስተኛ በመሆኑ የገዛቻት መኪና በጣም ያገለገለች ስለነበረች አንድ ሳምንት ሠርታ በሌላኛው ጋራጅ ገብታ ትቆም ነበር:: ይሁንና አንድ ዓመት ብትቸገርም ሥራው እየገባት፣ ደንበኞችም እያፈራች ለስምንት ዓመታት በዚሁ ሥራ በማገልገል መኪናዋን ወደ ሁለት አሳደገች፡፡
“ሴትነት እንደ ድክመት ሳይሆን ዕድልም ነው” የምትለው ወ/ሮ አደይ ሰዎች በቀላሉ እምነት የሚጥሉባት በመሆኑ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻለች ነው የምትገልፀው:: በአሁኑ ወቅት አየር መንገድ ለደንበኞች አገልግሎት የምትሰጠውን ታክሲዋን በሹፌር እንደምታሠራ የምትገልፀው አደይ፤ እርሷ ደግሞ ሌላ መኪናዋን በመያዝ ለከተማ አገልግሎት፣ ለወላድ ፣ለሰርግ እና ለመጓጓዝ በማከራየት ተጠቃሚ ሆናለች፡፡
ወይዘሮዋ ዳግም ትዳር በመመስረት የመኖሪያ ቤት ለመሥራትም ጥረት እያደረገች እንደሆነ ተናግራለች:: “ስኬት የሕይወት መንገድ እንጅ መዳረሻ አይደለም” የሚል እምነት ያላት ባለታሪካችን የዛሬ ማግኘቷ ለነገ ማጣቷ ዋስትና ስለማይሆን ሥራን በአግባቡ አሸንፎ የመሄድ ሂደት ሥኬት እንደሆነ ትመክራለች::
የወ/ሮ አደይ ህብስቱ ባለቤት አቶ ጥላሁን ስንታየሁ አደይ ሥራዋን ጥንቅቅ አድርጋ ከመሥራት ባሻገር ደንበኞቿን የምትይዝበት መንገድ አክብሮት የተሞላበት እንደሆነ ይመሰክራል:: ሌሎችን ለመርዳት የሊስትሮ እቃ እየገዛች የምትሰጣቸው በርካታ ልጆች አሉ፣ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በበርካታ በጎ አድራጎት ውስጥ በመሳተፍ አርዓያ የምትሆን፣ ጽኑ ፣ በቀላሉ ተስፋ የማይቆርጥ ባህሪ… አላት::“ሥራዋ ብዙ ጊዜዋን የሚፈልግ ቢሆንም የፍቅር ሰው፣ ባለሙያ እና ቤት አያያዝ የምትችል በመሆኑ እሷን በማግባቴ እራሴን እድለኛ አድርጌ እቆጥረዋለሁ!” በማለት ይገልፃታል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም