በስዊዘርላንድ ደቡብ ምስራቅ በአልፕስ ተራሮች ቀጣና ነው የሚገኘው:: የሀገሪቱ መንግሥት እና የተፈጥሮ ጥበቃ ተቋማት በ1909 እ.አ.አ ከባለይዞታዎች መሬት በመግዛት ነበር ቀጣናውን አስከብረው ያስከለሉት:: ፓርኩ በውስጡ የሚገኙ ዕፅዋትን እና የዱር እንስሳትን መጠበቅ ዋነኛ ዓላማ አድርጐ ነው በ1914 እ.አ.አ ድንበሩ ተከልሎ የተመሰረተው:: ጠቅላላ ስፋቱም 170 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል::
የስዊስ ብሔራዊ ፓርክ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በ1979 እ.አ.አ የመጀመሪያው ፓርክ ሆኖ እውቅና አግኝቷል:: ፓርኩ በርካታ የዱር እንስሳት መገኛ ነው:: ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡ በተደረገላቸው ጥበቃ ቁጥራቸው መበራከት ችሏል::
ፓርኩ የተራራ ላይ ሜዳዎች ቀጣና ነው:: በመሆኑም ከ20 በላይ መጠነኛ ስፋት ያላቸው ኃይቆችን ይዟል:: በጣሊያን ድንበር በኩልም ቀጥ ያለ አቀበታማ በሳር የተሸፈነ ቀጣና ይገኝበታል:: በፓርኩ ሸለቆዎች – አጋዘን፣ “ማርሞት” ፣ወርቃማ ንስር አሞራ፣ “ውድፒከር” እና “አይቤክስ” የመሳሰሉት መገኘታቸውም ተረጋግጧል:: በፓርኩ ለማረፊያነት ሻልኩሎዛ እና ቻሞን ኩሎዛ የተባሉ ብቻ ናቸው ያሉት:: በክረምት የፓርኩ ቀጣና ለጐብኚዎች ዝግ ነው- ምነው ቢሉ ወቅቱ በረዶ የሚወርድበት የዓየር ንብረቱም አስቸጋሪ በመሆኑ ነው::
ወደ ፓርኩ ለመድረስ በባቡር እና አውቶቡስ “ዘርኔዝ፣ ስኩሎ፣ ላቪን፣ ዙዎዝ” ወደ ተሰኙ ቀጣናዎች ያቃርባሉ::
ፓርኩ በአጠቃላይ በአውሮፓ በደንብ የተጠበቀ ከተመሠረተበት ጊዜ አንፃርም ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የተለያየ ብዝሃ ህይወት መገኛ፣ ለሳይንሳዊ ምርምር ተመራጭ ቀጣና መሆኑም ነው በማጠቃለያነት ለንባብ ያበቃው::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ሎንሊ ፕላኔት፣ ሰስቴይንኢሮፕ እና ትሪፕ አድቫይዘር ድረገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


