ስውሩ የዓየር ንብረት ለውጥ 

0
55

በዓየር ንብረት ለውጥ መንስሄነት እየተከሰተ ያለው የሙቀት መጨመር በሰብል አበቃቀል ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ ጐመን፣ አበባ ጐመን፣ ቆስጣ እና የመሳሰሉ ለምግብነት የሚውሉ ቅጠላ ቅጠሎች የሚይዙት ንጥረ ነገር መጠኑ ያነሰ እንዲሆን ማድረጉን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ  ለንባብ አብቅቶታል፡፡

በያዝነው 2025 እ.አ.አ  ሀምሌ ወር ቤልጀም ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ “ሶሳይቲ ፎር ኤክስፐርመንታል ሶሳይቲ” በተሰኘ ድርጅት በቀረበው የጥናት ውጤት የሙቀት  መጠን መጨመር በሰብሎች አበቃቀል ላይ ብቻ ሳይሆን የሚይዙት ንጥረ ነገር እንዲያሽቆለቁል ማድረጉ ተገልጿል።

 

አብዛኛዎቹ እስከአሁን የተካሄዱ ምርምሮች የዓየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርት  መጠን ላይ በሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ላይ ያተኮሩ ነበር።  ስለሆነም ከምርት መጠን ባሻገር የሰብልም ሆነ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት የሚይዙት ንጥረ ነገር ማሽቆልቆል ዋነኛው ያልታየ፣ ትኩረት ያልተደረገበት ችግር መሆኑን ነው የምርምር ውጤቱ ያመላከተው፡፡

 

በምርምሩ ከፍተኛ አስተዋፆኦ ያደረጉት በእንግሊዝ የሊቨርፑል ጆን ሙሬስ ዩኒቪርስቲ የዶክትሬት ተማሪዋ ጂያታ ኡጋዋ ኤኬል ምርምሩ ከምግብ ጥራት በላይ መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡ ይህንኑ ሲያብራሩም ለምግብነት የሚውለው ምርት በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገር ያነሰ ከሆነ በጤና ላይ የሚያሳድረው ጫና በጊዜ ሂደት ሊስተካከል የሚችል እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

 

ተመራማሪዋ ጂያታ ኡጋዋ ኤኬል ያደረጉት ምርምር በምክንያት እና ውጤት የተሳሰረ ነው፡፡ በዚህም የዓየር ንብረት ለውጥ በአዝርእት አበቃቀል፣ ከዚያም  “በፎቶሲንተሲስ” የፀሀይ ብርሃንን በመጠቀም ለፍሬ የመብቃቱ፣   በንጥረ ነገር ይዘት መጠኑ ማነስ ተፅእኖው የጐላ መሆኑን ነው የደረሱበት፡፡

 

እንደ ተመራማሪዋ ከመጀመሪያው ከሰብል አበቃቀል እስከ ምርት፣ አልፎም የምርቱን የንጥረ ነገር ይዘት መገንዘብ አስፈላጊነቱ ሰዎች የሚበሉት የምግብ ውጤት፤ የአካል ግንባታም ሆነ የጤናቸው መሰረት አዝርእት፣ ተክሎች በመሆናቸው ነው።

ምርምሩ በሊቨርፑል ጆንሙር ዩኒቨርሲቲ ቁጥጥር እና ክትትል ሊደረግበት በሚችል ቀጣና ነው የተካሄደው፡፡

የሙቀት መጨመር ሰብሎች ፈጥነው እንዲያድጉ ቢያስችልም ለጤና ቁልፍ የሆኑ “ካልሼየም”ን የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮችን በሚፈለገው መጠን አለመያዙን ነው ተመራማሪዋ የገለፁት።

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሐምሌ 21  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here