በአሁኑ ወቅት ዓለማችን በታሪኳ አይታው የማታውቀው ከፍተኛ የፍልሰት ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። እንደ ተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ሪፖርት፣ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጦርነት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በኢኮኖሚ መላሸቅ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ሆኖም ይህ መጠነ ሰፊ ፍልሰት በብዙ ሀገራት ዘንድ የሰብአዊነትን በር ከማንኳኳት ይልቅ፣ “የስደተኛ ጠልነት” (Xenophobia) የተሰኘ አደገኛ የፖለቲካና የማሕበራዊ በሽታ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል።
ስካይ ኒውስ እንደዘገበው የስደተኞች ጥላቻ በዘመናዊው ዓለም የተቀጣጠለው በዋነኝነት በደህንነት ስጋት፣ በኢኮኖሚ ተጽዕኖ እና ፖለቲካዊ ትርፍ ፍለጋ ነው። በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ጽንፈኛ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች፣ ስደተኞችን ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ድቀትና ለደህንነት ስጋት እንደ ዋነኛ ተጠያቂ በማድረግ የሕዝብን ድምጽ ለማግኘት ይጥራሉ። ይህ “እኛ እና እነሱ” የሚል ከፋፋይ ትረካ፣ ስደተኞች እንደ ሰብአዊ ፍጡር ሳይሆን እንደ ወራሪ እና የደህንነት ስጋት ሆነው እንዲታዩ አድርጓቸዋል።
በማሕበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችም ስደተኞችን ከወንጀልና ከባሕል መሸርሸር ጋር በማያያዝ ሕዝቡ በስደተኞች ላይ ጥቃቅንና መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን እንዲሰነዝር አነሳስተዋል።
በአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት፣ በተለይም እንደ ሃንጋሪና ጣሊያን ባሉ ሀገራት፣ ስደተኞችን የመከላከል ፖሊሲ አውሮፓን ማጠር ወይም መመሸግ ወደሚል ደረጃ ተሸጋግሯል። የድንበር ጥበቃ ተቋሙ (Frontex) በቢሊዮን የሚቆጠር ዩሮ በጀት ተመድቦለት ስደተኞችን በባሕር ላይ እያደነ እንዲመልስ ስልጣን ተሰጥቶታል።
በተመሳሳይ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ የሚፈጸመው “ከድንበር ይዞ የመመለስ” (Pushbacks) ተግባር ስደተኞች ጥገኝነት የመጠየቅ መብታቸውን ተነፍገው ለሞት እንዲዳረጉ እያደረገ ነው። በሌላ በኩል፣ በአፍሪካ አሕጉር ደቡብ አፍሪካ የስደተኛ ጠልነት ጥቃት በየጊዜው የሚቀሰቀስባት ሀገር ሆናለች። ከጎረቤት ሀገራት የሚመጡ አፍሪካውያን ወንድሞቻቸው የንግድ መደብሮች ሲዘረፉና ህይወታቸው ሲያልፍ ማየት የተለመደ ክስተት ሆኗል።
በመካከለኛው ምሥራቅም በስደተኞች ላይ የሚስተዋለው ጠልነት እየጨመረ ነው፤ ሁኔታው ከጥላቻም ባለፈ ወደ ስልታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተቀየረም ነው። ሳውዲ አረቢያ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዋነኛ መዳረሻ ብትሆንም፣ ጉዞው ግን በሞት የተሞላ ነው።
በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳስነበበው ደግሞ በየመን በኩል የሚያልፈው “የምሥራቅ መስመር” (The Eastern Route) በዓለም ላይ እጅግ አደገኛው የፍልሰት መስመር ነው። ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW) በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በሳውዲና በየመን ድንበር ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በድንበር ጠባቂዎች በጥይትና በከባድ መሣሪያ ተጨፍጭፈዋል። ይህ ድርጊት ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ቢሆንም እስካሁን ተገቢው ተጠያቂነት አልሰፈነም።
ሳውዲ አረቢያ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከገቡ በኋላም ቢሆን እረፍት የላቸውም። የ“ካፋላ” ሥርዓት ሠራተኞችን ከአሰሪዎቻቸው ጋር በማሰር ፓስፖርታቸውን እንዲቀሙ፣ ደመወዛቸው እንዲከለከል እንዲሁም ለተለያዩ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃቶች እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል። በተለይ ሴት የቤት ሠራተኞች ለጾታዊ ጥቃትና ለከፋ እንግልት ይጋለጣሉ። ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ደግሞ በማቆያ ማዕከላት ውስጥ በጠባብ ክፍል ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሆነው እንዲታጎሩ ይደረጋል። በእነዚህ ማዕከላት ውስጥ ያለው የምግብና የሕክምና አቅርቦት እጥረት በስደተኞቹ ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ስብራትና ሞት እያስከተለ ይገኛል።
ይህ ሁሉ መከራ እየደረሰ ያለው ስደተኞች ካለባቸው አማራጭ እጥረት የተነሳ ነው። የስካይ ኒውስ ዘገባ እንደሚለው በሀገር ውስጥ ያለው ድህነት፣ ግጭትና የኑሮ ውድነት ዜጎችን ለአዘዋዋሪዎች እጅ አሳልፎ ይሰጣቸዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ እንዳመላከተው አፍሪካ እና እስያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የሚሰደዱባቸው ናቸው፤ አሕጉራቱም የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ግጭት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስና እና ሌሎች ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች የሚበዙባቸው ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ዜጎች ስደትን እንዲያማትሩ አድርጓቸዋል፡፡
የኮሚሽኑ ሪፖርት እንዳመላከተው በአሁኑ ወቅት የትውልድ ቀየውን በመልቀቅ በሌላ ሀገር በስደት የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል፤ በርካቶችም ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢኮኖሚና ማሕበራዊ ጉዳዮች ክፍል (UNDESA) ባወጣው ሪፖርት እንዳመላከተው በ2016 ዓ.ም (2024/25 እ.አ.አ)የስደተኞች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ304 ሚሊዮን በላይ ሆኗል፤ ይህ ቁጥር ደግሞ ከዓለም ሕዝብ ሦስት ነጥብ ሰባት በመቶ ያህል ነው፡፡
በተመሳሳይ በሕገ ወጥ መንገድ ውቅያኖስ በማቋረጥ ለመሻገር በተደረገ ሙከራ በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የውኃ ሲሳይ መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል፤ ዕድለኛ ሆነው በሕይወት የተረፉትብ መዳረሻ የሚጓቸው ሀገራት በስጋት ይመለከቷቸዋል፤ የፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ በማስገባትም ለስደተኞች ያላቸውን ጥላቻ እያሳዩ ነው፡፡
አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን ለገንዘብ ሲሉ በአደገኛ ጀልባዎች ጭነው ባሕር ላይ ይጥሏቸዋል፤ ወይም ደግሞ በበረሃ ውስጥ ለጥማትና ለረሃብ ይዳርጓቸዋል። በመሆኑም ስደተኞች በአንድ በኩል በገዛ ሀገራቸው ችግር፣ በሌላ በኩል በአሸጋጋሪዎች ግፍ፣ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በሚቀበሏቸው ሀገራት ጥላቻና ግድያ መከራን ይቀበላሉ።
ለዚህ ስር ለሰደደ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ዓለም አቀፍ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ድርጅቱ አመላክቷል። ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን እና ስምምነቶችን ማጠናከር ይገባቸዋል፡፡ ለአብነትም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳውዲ አረቢያና ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር የዜጎችን መብት የሚያስከብሩ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እየተገበረ ይገኛል፤ መሰል ተግባራትን ማጠናከር ደግሞ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ያስቀረዋል።
ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችም ለዜጎች የሚሰጡትን ድጋፍ በማጠናከር፣ ስደተኞች በደል ሲደርስባቸው የሚያመለክቱበትና ፈጣን ምላሽ የሚያገኙበት አሠራር ሊዘረጋ ይገባል። በተጨማሪም፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚቆጣጠር ጠንካራ ሕግና ክትትል ያስፈልጋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደግሞ ስደተኞችን እንደ ችግር ሳይሆን እንደ ሰብአዊ ፍጡር መመልከት ደግሞ ድርጅቱ ያነሳው ተጨማሪ የችግሩ መሻገሪያ ዘዴ ነው። ሀብታም ሀገራት ስደተኞችን በመገፋትና ድንበር በመዝጋት ፈንታ፣ የፍልሰቱን መነሻ የሆኑ ችግሮችን (ድህነትንና ግጭትን) ለመፍታት በትኩረት መሥራት እንዳለባቸውም አመላክቷል።
የ1951ዱ የስደተኞች ድንጋጌና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕጎች በወረቀት ላይ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ በማድረግ ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል። ስደተኞች የሚሰደዱት የተሻለ ህይወት ፍለጋ እንጂ ለጥፋት አለመሆኑን ተገንዝቦ፣ በሰብአዊነትና በፍትሐዊነት የሚያስተናግድ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት መገንባት ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም።
አልጀዚራ፣ ስካይ ኒውስ፣ Human Rights Watch (HRW)፣ Amnesty International፣ UNHCR፣ International Organization for Migration (IOM)፣ European Council on Refugees and Exiles (ECRE) የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


