ስፖርት እና ሰላም

0
114

በስድስተኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች አማራ ክልል ሶስተኛ ደረጃን ይዞ  ማጠናቀቁ አይዘነጋም። በአጠቃላይ 66 ወርቅ 70 ብር እና  88 ነሃስ በድምሩ 224 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ነው ሦስተኛ ደረጃን ይዞ የጨረሰው። ክልሉ በግጭት ወስጥ ሆኖ ደረጃ ውስጥ ገብቶ መጨረሱ የሚደነቅ ነው፡፡ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ፣ ስፖርተኞች ያለምንም ስጋት ስፖርታዊ ወድድሮችን ለማከናወን፣ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት እና የስፖርት ኢንቨስትመንትን ለማበረታት ግን ክልሉ ወደ ቀድሞው ሰላሙ መመለስ እንደሚጠበቅበት- ብዙዎችን የሚያስማማ ሀቅ ነው፡፡ ታዲያ ሰላምን ለማስፈን ደግሞ ስፖርቱን እንደ ትልቅ መሳሪያ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የገለጽት ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋረ ቆይታ ያደረጉት በባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ መምህር የሆኑት ዳንኤል ጌትነት (ዶ.ር)  ናቸው፡፡

ስፖርት በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ሕዝብን አንድ የሚያደርግ ጠቃሚ መሳሪያ ነው። በምድራችን ጦርነት እና ግጭቶች በተበራከቱበት በዚህ ዘመን ስፖርት የተለያዩትን አንድ አድርጓቸዋል። የዓለም ታላላቅ መሪዎችም ዲፕሎማሲያዊ ውይይትን ለመክፈት ስፖርትን እንደ መሳሪያ ተጠቅመዋል። በአጠቃላይ ማኀበረሰቡን አንድ ላይ ለማሰባሰብ፣ ግጭቶችን ለመፍታት እና ሰላምን ለመገንባት ስፖርት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ እያደርገም ይገኛል።

 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስፖርት ሰላም እና ልማትን ለማምጣት አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ይጠቁማል። ሀገራት የ2030 አጀንዳን ሲፈርሙ በ16ኛው አንቀጽ በዓለም ላይ ሰላምን ለማምጣት እንደሚስሩ ተስማምተው ነው። የኦሎምፒክ ግብም ስፖርትን ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት እና ሰላማዊ ማኅብረሰብን መፍጠር መሆኑን የኦሎምፒክ ዶት ኮም መረጃ አመልክቷል።

በየትኛውም የስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ እና ስፖርቱ የሚሰጠውን ጥቅም ለማግኘት ሰላማዊ የሆነ ከባቢ እንደሚያስፈልግ በባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ መምህር የሆኑት ዳንኤል ጌትነት (ዶ.ር) ይናገራሉ።  በስፖርቱ ዘርፍ ማህበራዊ አንድነትን ወይም መስተጋብርን ለማሳደግ እና የባህል ልውውጥ ለማድረግ ሰላም አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል- ዳንኤል ጌትነት (ዶ.ር)።

 

በተደጋጋሚ በፕላኔታችን ሰላምን እና ልማትን ለማምጣት የኦሎምፒክ ውድድር እንደ መሳሪያ አገልግሏል፤ እያገለገለም ይገኛል። ስፖርት ብሄራዊ ማንነትን እና ኩራትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ስፖርት በባህሪው በጋራ ለመሥራት፣ ለመከባበር፣ ፍትሐዊ ጨዋታን ለማሳደግ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው። በተለይ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ወጣቶችን የሰላም አምባሳደር በማድረግ እና በማሳተፍ ሰላምን ለማስፈን ይረዳል፡፡ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያ የስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማበረታት ከገቡበት የጭንቀት እና  የፍርሀት ቆፈን እንዲወጡ እና ጤናማ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩም ያስችላል።

 

ስፖርት በሕዝብ መካከል ያለውን አለመተማመን ይቀርፋል። ስፖርትን ተጠቅመው  ሀገራዊ መግባባት (National dialogue) ላይ እንዲደርሱም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ስፖርት የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎችን መተሳሰብን እና መከባበርን በማሳደግ  የጋራ መግባባት ላይ በማድረስ ሰላም እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት-የስፖርት ሳይንስ መምህሩ። “ሰላም ካለ ውድድሮች፣ ስልጠናዎች እና የስፖርት ዝግጅቶችን ያለፍርሀት እና ስጋት ይካሄዳሉ። ተመልካች፣ ደጋፊዎችም እና ስፖርተኞችም ያለስጋት በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው በስፖርቱ መሳተፍ ይችላሉ፡፡ ሰላም ካለ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ይገነባሉ። የስፖርት ኢንቨስትመንትም ይጨምራል፤ ስፖርቱም ይነቃቃል” ብለዋል ዳንኤል (ዶ.ር)።

 

ስፖርት እና ሰላም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል፤ ስፖርት ለሰላም ግንባታ ዋነኛ መሳሪያ ሲሆን ሰላም ለስፖርት እድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የስፖርት ሀብትን ለመሰብሰብ ሰላም ያስፈልጋል። ስፖርተኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ ያለምንም ስጋት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወንም የሰላም አስፈላጊነት ወሳኝ ነው። በአንድ ሀገር ግጭቶች ከበዙ በዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅብረሰብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ይቀንሳል። ስፖርት ግጭቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ዋነኛ መሳሪያ መሆኑን የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል፡፡ ኮትዲቫራዊው የቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ በሀገሩ የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት እግር ኳስ ስፖርትን ተጠቅሞ በዘላቂነት ማስቆሙን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

 

ሌላው በዓለም አቀፍ ደረጃ ስፖርት እርቅን በማውረድ ሰላምን ካሰፈነባቸው አጋጣሚዎች መካከል በ1970ዎች በአሜሪካ እና በቻይና መካከል የነበረው የፒንግ- ፖንግ ዲፕሎማሲ ነው። ጃፓን በተካሄደው በዓለም የጠረጴዛ ቴንስ ሻምፒዮና የሁለቱ ሀገራት ስፖርተኞች የሀገራቸውን አለመግባባት እና ጥላቻ ወደ ጎን በመተው ሰላምታ ተለዋውጠዋል። የስፖርተኞች መልካም ተግባርም በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ውጥረት እንዲረግብ አድርጓል።

 

ስፖርቱ በፈጠረው ዲፕሎማሲ አማካኝነት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ቻይናን በመጎብኘት ግንኙነታቸውን አሻሽለዋል። ይህም ስፖርት በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ ያለው ኃይል የተረጋገጠበት መሆኑን የሪሰርች ጌት መረጃ ያስነብባል።

ስፖርት ዓለማቀፋዊ ቋንቋ በመሆኑ ሰላም በስፖርት የሀገር ገጽታን ለመገንባት ትልቅ በር ይከፍታል። የተለያዩ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ የስፖርት ዝግጅቶችን ለማካሄድ ታዲያ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ዳንኤል ጌትነት (ዶ.ር) ያብራራሉ። ስፖርተኞችም ቢሆኑ በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች መሳተፍ የሚችሉት በአካባቢያቸው ሰላም ሲኖር ጭምር መሆኑን ነግረውናል። ሰላም የአዕምሮ እረፍት እና መረጋጋትን ያስገኛል፤  ታዲያ በአካል ብቃት እና በአዕምሮ የዳበረ ስፖርተኛ ለማፍራት የሰላም ፋይዳው የጎላ እንደነ ተጠቁሟል።

 

ባለፉት አምስት ዓመታት በክልላችን ብሎም በሀገራችን ሰላም ባለመኖሩ ስፖርተኞች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ተሰደዋል፣ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ተዘግተዋል፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችም ቀንሰዋል፤ ተቋርጠዋል። ታዲያ የሀገራችንን ሰላም አስጠብቆ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ያለምንም ስጋት ለማከናወን ወጣቶች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ላይ በስፋት እንዲሳተፉ በማድረግ ሰላምን ከሚያውኩ ድርጊቶች ማራቅ እንደሚቻል የስፖርት ሳይንስ መመህሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ስፖርት ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ባይ ናቸው።

ሰላም ካለ በየአካባቢው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ውድድሮች፣ የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታዎች እና የመሳሰሉት እንደሚከናወኑ ይታመናል። ታዲያ ስፖርት ከእንቅስቃሴነቱ ባሻገር በሀገራችን የሥራ ዕድል ፈጠራ በመሆን ይጠቅማል። ሰላምን ለማስጠብቅ የሚውለው እና የሚባክነው ከፍተኛ ገንዘብም ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ እና ለስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ይውላል። ይህም ሀገራዊ አንድነትን ይጨምራል ተብሏል።

ስፖርታዊ ውድድሮች  ካልተቋረጡ  በየደረጃው ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞች ይፈሩበታል። በአንጻሩ የሀገር ሰላም ከደፈረሰ ግን የስፖርት ስልጠናዎች፣ ውድድሮች እና ስፖርተኞችም እንደማይኖሩ ዳንኤል ጌትነት (ዶ.ር) ተናግረዋል ። እናም ሰላምን ሊያሰፍኑ የሚችሉ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤ አሰልጣኞች፣ ስፖርተኞች እና በአጠቃላይ የስፖርት ባለሙያዎች ሰላምን ሊሰብኩ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት እና ማስገንዘብ ይገባል ነው የተባለው።

 

ሰላምን የሚሰብኩ የስፖርት ዝግጅቶችን ማዘጋጀት፣ የስፖርት የሰላም አምባሳደሮችን በማዘጋጀት የሰላምን አስፈላጊነት የሚያንጸባርቁ መልዕክቶችን እንዲያስተጋቡ ማድረግ በስፖርት ሰላምን ለማስፈን ሁነኛ መፍትሄ ነው። የሰላም አምባሳደሮችን በማዘጋጀት በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሰላም እንዲቀነቀን ማድረግ ሌላኛው በስፖርት ሰላምን ለማስፍን የሚረዳ መፍትሔ መሆኑ ተጠቁሟል። ይህ ማለት ግን ስፖርት ብቻውን ሰላም ያመጣል ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት እንደሚገባ በባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ አካዳሚ መምህር የሆኑት ዳንኤል ጌትነት (ዶ.ር)  አጽንኦት ሰጥተውታል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here