ስፖርት እና የስፖርተኞች ጉዳት በሀገራችን

0
218

ስፖርተኞች ከጉዳት ርቀው ራሳቸውን ጠብቀው፣ ጉዳት ቢያጋጥማቸው እንኳን በቶሎ አገግመው በሚፈልጉት ደረጃ ውጤታማ እንዲሆኑ የስፖርት ህክምና የላቀ አስተዋጽኦ አለው። የስፖርት ህክምና እንደየ ዘመኑ ትኩረት ተሰጥቶት ባይሰራም በግሪካውያን የስልጣኔ ዘመን ስፖርተኞቹ ጉዳት ሲደርስባቸው ህክምና ያገኙ እንደነበረ የቢቢሲ ጆርናል ኦፍ ሜዲስን መረጃ ያሳያል።
በዓለማችን በመዝናኛው ዓለም ከፊልም ኢንዱስትሪው ቀጥሎ ቢሊዮን ገንዘቦች በሚንቀሳቀሱበት በስፖርት ኢንዱስትሪው ዘርፍ ስፖርተኞቹን ውጤታማ ለማድረግ በብቃታቸው እንዲቆዩ እና የብቃታቸው ጫፍ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ የስፖርት ህክምና ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በሀገራችን ግን ችግሩ አሁን ላይም ሳይሻሻል ዓመታትን እያስቆጠረ ዘመናትን እየተሻገረ ነው።
ለመሆኑ የስፖርት ህክምና ስንል ምን ማለታችን ነው?
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ የትምህርት ክፍል የአናቶሚ መምህር ከሆኑት አቶ ኦሪዮን አየለ ጋር የበኩር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ቆይታ አድርጓል።እንደ አቶ ኦሪዮን ገለፃ በአጠቃላይ በስፖርቱ ማንኛውም ጉዳቶች ወይም ስፖርተኞች ከሚሰሩት እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉላቸውን ህመሞች የሚያክም የህክምና ዘርፍ ነው፡፡ በሀገራችን ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ እስካሁን ባለው አብዛኞቹ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች በእውቀት ሳይሆን በልምድ ብቻ በሥራው ላይ መሰማራታቸውን ጭምር አቶ ኦሪዮን ያነሳሉ።
ነገር ግን በቀደሙት ጊዜያት ይስሀቅ ሽፈራውን የመሳሰሉ የሀገር ባለውለታ የነበሩ የስፖርት ሀኪሞችም እንደነበሩ አይዘነጋም። ለዘርፉ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ በየስፖርት ዓይነቱ በርካታ ተጫዋቾች ጉዳት ሲገጥማቸው በቶሎ አገግመው ወደ ቀድሞ አቋማቸው ለመመለስ ይቸግራቸዋል።
የስፖርት ጉዳት በማንኛውም ጊዜ በስልጠና ክፍለ ጊዜ ወይም በውድድር ወቅት ሊከሰት ይችላል።ጉዳቶች ንክኪ ባለው እና በሌላቸው ስፖርቶች የሚከሰቱበት መጠን የተለያየ መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ። ከማሟሟቅ ጀምሮ እስከ ማቀዝቀዝ ያሉትን ስፖርታዊ ሂደቶችን አለመጠበቅ ለጉዳት ከሚያጋልጡ ዋነኛ ምክንያቶች ቀዳሚው ነው። በእነዚህ ምክንያቶች የሚከሰቱ ጉዳቶች ደግሞ የጡንቻ መሸማቀቅ ፣ የመገጣጠሚያ ውልቃት እና የአጥን ስብራት ናቸው ።
ከላይ ያነሳናቸው እነዚህ ጉዳቶችም ንክኪ ባላቸው እግር ኳስ ፣ እጅ ኳስ እና ቅርጫት ኳስን በመሳሰሉ ስፖርቶች የጉዳት መጠኑ ይጨምራል። ቮሊቦል እና አትሌቲክስን በመሳሰሉት ንክኪ በሌላቸው ስፖርቶች የጉዳት መጠኑ ቢቀንስም ስፖርተኞቹ የስፖርት ሂደቱን ባለመጠበቃቸው ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል።
ጉዳት የሚደርስባቸው ስፖርተኞች ወደ ትክክለኛው ሀኪም ጋር ለመድረስ ብዙ ጊዜ ስለሚወስድባቸው የጉዳት መጠኑን ያከፋዋል። ስፖርተኞቹ ጉዳት ሲገጥማቸው የተሻለ ህክምና ለማግኘት ውጪ ሀገር ተጉዘው የሚታከሙ በጣም ጥቂቶቹ በመሆናቸው አብዛኞቹ በወቅቱ ከጉዳታቸው ካላገገሙ ከስፖርቱ እንደሚርቁ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ ወጣቶቹ በዚህ ምክንያት የሚፈልጉበት የስኬት ደረጃ እና ጫፉ ላይ ሳይደርሱ በጉዳት ምክንያት ህልማቸው ቅዠት ሆኖ ይቀራል።
በእግር ኳሱ እንኳን ብንመለከት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አብዛኞቹ ክለቦች በጤና ሚኒስቴር ህጋዊ የሙያ ፈቃድ ያለው የስፖርት ሀኪም ስለመቅጠራቸው ያጠያይቃል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የህክምና ባለሙያ እንዲኖራቸው አስገዳጅ ሕግ ቢያወጣም የትምህርት ዝግጅታቸው ግን ምን መምሰል እንዳለበት በግልፅ አልተቀመጠም።
በእግር ኳስ የክለብ ወጌሻዎች የተሟላ የህክምና ቁሳቁስ ሳይዙ ውኃ ብቻ ይዘው ሜዳ ውስጥ ብዙ ጊዜ በየ ጨዋታው ሲሮጡ ማየት እንግዳ አይደለም። ይህ ደግሞ ለተጫዋቹ ጤና እና ለስፖርቱ በርካታ ገንዘብ ለሚያወጡ ክለቦችም አደገኛ አሠራር እንደሆነ በተደጋጋሚ ባለሙያዎች አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል።
ምን መደረግ አለበት?
ከዚህ በኋላ ግን ሁሉም ክለቦች ቢያንስ አንድ የህክምና ባለሙያ እንዲኖራቸው በሕግ ማዕቀፍ መቀመጥ አለበት።የትምህርት ዝግጅታቸውም ጥርት ባለ መንገድ በሕጉ ላይ መካተት አለበት የባለሙያው አቶ ኦሪዮን ምክረ ሀሳብ ነው።
ሜዳ ውስጥ ተጎድቶ የወደቀን አንድ ተጫዋቾ የጉዳት መጠኑን በቅርበት የሚከታተለው የስፖርት ሀኪሙ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ የህክምና ባለሙያ ግን ሙያውን በደንብ ካላወቀው እና ሳይንሱን ካልተረዳው በቀላሉ መዳን የሚችለውን ጉዳት እንዲባባስም ሊያደርገው ይችላል እና ለዘርፉ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አቶ ኦሪዮን አየለ ይናገራሉ።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የስፖርት ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት በመሆኑ የስፖርት ህክምናውን ለማዘመን ብዙ አስቸጋሪ እንደማይሆን ይገመታል። የስፖርት ህክምናን በሀገራችን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማስቀመጥ እና ስፖርተኞቹ የሚፈልጉት ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ የስፖርት ህክምናን ማዘመን ይገባል። ዘርፉ በእውቀትና በሙያው በሰለጠነ ሰው መመራት ይኖርበታል። የአቶ ኦሪዮን ምክረ ሀሳብ ነው።
በጥናት ላይ የተመረኮዘ ባይሆንም አሁን ላይ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ብቁ የሆነ የስፖርት ሀኪም እንደሌላቸው እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ያምናል። በልምድ የሚሰሩትን እነዚህን ባለሙያዎችም ስልጠና ሰጥቶ ብቁ ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው።
አለበለዚያ ደግሞ ሳይንሱን በደንብ ለተረዱት ባለሙያዎች ዕድሉን ሰጥቶ ልምድ እንዲያገኙ ማስቻል እንደሚገባም አቶ ኦሪዮን ጠቁመዋል። ይህ ካልሆነ ግን አሁን ባለው የስፖርት ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ሩቅ የሚጓዙ እና ትልቅ ደረጃ የሚደርሱ ስፖርተኞች በአጭሩ ሊቀጩ ይችላሉ። ስፖርተኞቹ የተሻለ የህክምና አገልግሎት አለማግኝታቸው ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ጉዳቱን እና የጉዳት መጠኑ አለመታወቁም በስፖርት ህይወታቸው ላይ አደጋ ይፈጥራል። ለአብነት በማርሻል አርት ስፖርት አንድ ስፖርተኛ በጨዋታ ወቅት ጉዳት ካጋጠመው የመጫወት ዕጣ ፈንታው በሀኪሙ ነው የሚወሰነው።ከስፖርቱ ባህሪ አንፃር ይህ ደግሞ ከውጤቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኖረዋል።ያለ ዘመናዊ የስፖርት ህክምና ክለቦቹም ውጤታማ መሆን አይችሉም እና የህክምና ክፍላቸውን ማዘመን አለባቸው የአቶ ኦሪዮን አየለ አስተያየት ነው፡፡
የስፖርት ህክምና ስልጠናን ማዘጋጀት ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ከማሰልጠኛ ተቋማት፣ ከክለቦች ጋር በትብብር መሥራት የስፖርት ፌደሬሽኖቹ እና የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ተግባር ነው። በዚህ ዘርፍ ብቁ ከሆኑ ከሌሎች ሀገራት ጋርም መሥራት ያስፈልጋል። በሙያው የበቁ እና የሰለጠኑ ግለሰቦችም ቢሆኑ የስፖርት ህክምና እንዲስፋፋ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የዘርፉ ባለሙያ አቶ ኦሪዮን አየለ ያሳስባሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ እና የአትሌቲክስ ቡድኖች ጤናማ ስፖርተኞችን የሚያገኙት ከክለቦች በመሆኑ በጤናው ረገድ ክለቦች ላይ ጠንካራ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡ይህ ካልሆነ ግን በየስፖርቱ የታመመው ውጤታችን ይበልጥ መታመሙ አይቀሬ ነው፡፡
ባለሙያው አቶ ኦሪዮን አየለም በልምድ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎችን ከሳይንሱ ጋር ማስተዋወቅ ወይም በሙያው የሰለጠኑ ሰዎችን ወደ ስፖርቱ መቀላቀል አዋጭ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡የሀገራችን ስፖርት እና ስፖርተኞች መታመማቸው እንዳይቀጥል ስፖርቱ በሳይንሳዊ መገድ ይመራ።በሌላው ዓለም የምናየው እውነታም ይሄው ነውና!

(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here