ከሰሞኑ ሶሪያዊያን የኣል-አሳድ መንግሥት የተገረሰሰበትን አንደኛ ዓመት ለማክበር በደማስቆ ጎዳናዎች ላይ ወጥተው ነበር:: ከ14 ዓመታት ጦርነት በኋላ አዲሱ የሶሪያዉ ፕሬዝዳንት አህመድ ኣል-ሻራአ በደማስቆ ደስታቸውን ለመግለጽ ለተሰበሰቡ በርካታ ሰዎች “ሀገሪቱ ገጿን ከጨለማ ምዕራፍ ወደ ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ ቀይራለች” ሲሉ ተናግረዋል::
አልጀዚራ የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት የበሻር ኣላ-ሳድን መወገድ አንደኛ ዓመት ተከትሎ በሀገሪቱ ሕዝቡ ደስታውን ለመግለጽ በአደባባዮች በወጣበት ጊዜ አንዳንዶችን አነጋግሮ ነበር:: ለክብረ በዓሉ ከወጡት መካከልም ሊና አል-ማሳሪ ለተባሉ ግለሰብ ዛሬ በእውነት እንደ ክብረ በዓል ይሰማዎታል? በማለት አልጀዚራ ላቀረበላቸው ጥያቄ “ሶሪያ ነፃ ነች! በደኅንነት ነው የምንኖረው! ይህ በሶሪያዊያን ዘንድ ለዘመናት ያላየነው ደስታ ነው!”፤ በማለት ነበር የመለሱለት::
“ወጣቶቻችን እና ወንድ ልጆቻችን በታጣቂዎች ሲወሰዱ ላይመለሱ ይችላሉ ወይም ይሞታሉ ብለን እንጨነቅ ነበር:: አሁን ግን ጐዳናዎቻችን በወጣቶች ተሞልተዋል:: የእኛ ሰዎች ያለ ምንም ፍርሃት በነፃነት እና በደኅንነት እየተጓዙ ነውም!” ብለዋል::
እ.አ.አ. በ2011 የፀደይ ወቅት የተቀሰቀሰው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት የሶሪያን ገጽታ በጥልቀት እና ሰፊውን መካከለኛው ምሥራቅንም ጭምር በማይቀለበስ ሁኔታ ለውጦታል:: በተጨማሪም እ.አ.አ በ2015 የበጋ ወቅት በግዙፉ የስደተኞች ማዕበል እና ከዚያ በኋላ በአውሮፓ በተከሰቱት የአሸባሪዎች ጥቃቶች በግልጽ እንደታየው ደም አፋሳሹ ግጭት በዓለም ላይ ዘላቂ ተጽእኖ አሳድሯል::
ሶሪያ ከጦርነቱ በፊት
ምንም እንኳን ዛሬ ሶሪያ በዓለም ላይ እጅግ የተመሰቃቀለች ሀገር ብትሆንም ከ15 ዓመታት በፊት ግን በጣም የተለየ ቦታ ላይ ነበረች:: የሶሪያ አረብ ሪፐብሊክ ምንም እንኳን ፈላጭ ቆራጭ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ቢኖራትም በአንፃራዊነት የተሻሻለች እና በአካባቢው ላሉ ለሌሎች ሀገራትም አርአያ መሆን ትችል ነበር::አክቹዋሊቲካ (Actualitica.com ) እንደሚያትተው እ.አ.አ ከ2011 በፊት ሀገሪቱ ሰላም ነበረች፤ ምንም አይነት ከፍተኛ ተቃውሞ፣ የሥራ ማቆም አድማ እና አመጽ አልነበረባትም::
የእርስ በርስ ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት አብዛኛዎቹ ሶሪያዊያን ባደጉት የምዕራባዊያን ሀገራት ደረጃ ይኖሩ ነበር:: ሙዚቃ፣ ፋሽን እና ስፖርት ለሶሪያዊያን በጣም ተወዳጅ ከሆኑ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች መካከል ነበሩ:: የደማስቆ እና የአሌፖ የተጨናነቁ ገበያዎች አስደሳች ነበሩ፤ ምዕራባዊያን የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ቢጥሉም ሀገሪቱ እያደገች እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ እየበለጸገች ነበር::
ሶሪያ የተለያዩ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች (ካቶሊኮች፣ ግሪክ ካቶሊኮች፣ ኦርቶዶክሶች፣ ፕሮቴስታንቶች)፣ የእስልምና (ሱኒዎች፣ ሺዓዎች፣ አላውያን)፣ አይሁዶች እና ሌሎች ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች ለዘመናት በሰላም አብረው የኖሩባት የመድብለ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ማሕበረሰብ እውነተኛ ምሳሌ ነበረች:: ለአብነትም ከጦርነቱ በፊት በደማስቆ በብዛት ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች በሚኖሩባቸው ሰፈሮች ምንም ዓይነት ግጭት ሳይገጥም መጓዝ ቀላል ነበር:: የቤተክርስቲያን ግንቦች እና የመስጊድ ሚናራዎች (በአካባቢው መስጊድ መኖሩን የሚያመለክት) ጎን ለጎን ቆመው ነበር::ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ ኩርዶች እና አረቦች ምንም የሚታይ የጎሳ ወይም የሃይማኖት መለያየት ሳይኖርባቸው ካፌዎችን፣ ሬስቶራንቶችን እና የጥበብ ጋለሪዎችን ይጋሩ ነበር::
ሶሪያ የሌሎች ሀገራትን ባሕል ለመቀበል በጎ አመለካከት ያላቸው ማሕበረሰብ ባለቤት ነበረች:: ሀገሪቷ ሴኩላር ነበረች ( መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ አይገባም):: የሶሪያ ሴቶች እንደ ወንዶች እኩል የጤና እንክብካቤ የማግኘት፣ የመማር እና የመሥራት መብት ነበራቸው::
ሶሪያ ከጦርነቱ በፊት በቀጣናው (በመካከለኛው ምሥራቅ) ውስጥ ያለ ውስጣዊ አመጽ እና የጎሳ ግጭት የሌለባት ብቸኛ ሀገር ነበረች:: ክርስቲያኖች ከጠቅላላው ሕዝብ 10 በመቶ ያህሉ ሲሆኑ መሬት የመግዛት እና ቤተ ክርስቲያን የመገንባት መብትም ነበራቸው:: ይህም የሃይማኖት እኩልነት የምታንጸባርቅ ሀገር መሆኗን ማሳያ ነው::
የኢኮኖሚ ሁኔታ
( ከጦርነቱ በፊት )
ከጦርነት በፊት እ.አ.አ. በ2000 እና 2010 መካከል የሶሪያ አጠቃላይ ምርት በሦስት እጥፍ አድጎ ነበር:: ሶሪያ በጣም የተረጋጋች ሀገር ስለነበረች እ.አ.አ. በ2003 አሜሪካ ኢራቅን ከወረረች በኋላ ጦርነቱን ለሸሹ የኢራቅ ስደተኞች መዳረሻም ሆናለች:: እ.አ.አ. በ2010 ሶሪያ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የኢራቅ ስደተኞችን ተቀብላ ማስተናገዷን ልብ ይሏል::
ከጦርነቱ በፊት ሶሪያ የምትመካበት በፍጥነት እያደገ የሚሄድ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ነበራት:: ምንም እንኳን እንደ ግብፅ፣ ቱኒዚያ፣ ቱርክ እና ቆጵሮስ ባሉ የሜዲትራኒያን ቱሪዝም ግዙፍ ኩባንያዎች ተሸፍኖ የነበረ ቢሆንም ለብዙ ቱሪስቶች ተወዳጅ መዳረሻ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ደኅንነቷ የተጠበቀ እና በጣም ነፃ የሆነች ሀገር ነበረች::
እ.አ.አ በ 2010 ኒውዮርክ ታይምስ ሶሪያን በዓለም ላይ ከሚገኙ ተመራጭ የጉዞ መዳረሻ መካከል 7ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧት ነበር:: ሶሪያ በታርቱስ እና በላታኪያ ውብ የባሕር ዳርቻዎችን ብቻ ሳይሆን የጥንት ከተሞችን ሀብት፣ በርካታ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ቦታዎችን ጨምሮ ብዙ ታሪክ ያላት ሀገር ናት:: ዋና ከተማዋ ደማስቆ በቀላሉ አረብኛ የሚማሩባት ሕያው ከተማ ተብላም ትታወቅ ነበር:: ደማስቆ እ.እ.አ በ2008 የአረብ የባሕል ዋና ከተማም የሚል ስያሜም ተሰጥቷት ነበር::
የሶሪያ ምግብ በተለይም የጥንቷ አሌፖ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ምርጥ ተብሎ ይታሰብ ነበር:: ቱሪስቶች የሮማዊያን ሕንጻ ፍርስራሾችን፣ ሰፊ በረሃዎችን፣ የተጨናነቁ የከተማ ገበያዎችን፣ ጥንታዊ የባሕር ዳርቻዎችን እና መስጊዶችን ለማየት ወደ ሀገሪቱ ይመጡ ነበር:: ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የኪነ-ጥበብ እና የባሕል ማዕከል ነበረች፤ እንደ ግሪክ፣ ሮማን፣ ባይዛንታይን፣ ኦቶማን እና እስላማዊ ስልጣኔዎች ነበሯት::
ቱሪዝም የሶሪያን የመንግሥት በጀት ብቻ ሳይሆን የግል ሬስቶራንቶችን እና የእጅ ባለሙያዎችን ካዝና የሚሞላ ነበር:: የሶሪያ የቱሪዝም ሚኒስቴር እንደገለጸው እ.አ.አ በ2010 ወደ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ሶሪያን ጎብኝተዋል:: እ.አ.አ ከ2009 ጋር ሲነፃፀር 40 በመቶ የቱሪዝም ገቢ ጭማሪ አሳይቷል:: በእርግጥ በዚያ ዓመት አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ቱሪስቶች ሶሪያን ጎብኝተዋል:: በመሆኑም በ2010(እ.አ.አ) ሶሪያዊያን ወደ ስምንት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ አግኝተዋል:: ቱሪዝም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 13 ነጥብ አምስት በመቶ እና በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ሥራዎች 13 በመቶውን ይይዛል:: ጦርነቱ ሲፈነዳ ግን(እ.አ.አ በ2011) ሶሪያ ያገኘችው አንድ ነጠብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነበር::
አክቹዋሊቲካ ድረ ገጽ እንደሚያስረዳው ከጦርነቱ በፊት በነበሩት ዓመታት በርካታ የምዕራባዊያን ሹማምንት ሶርያን ጎብኝተዋል፤ ለአብነትም የሮማው ጳጳስ ጆን ፖል ሁለተኛ፣ የቀድሞው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒሥትር ቶኒ ብሌየር እና ሌሎችም ይገኙበታል::
ሶሪያ እና ምዕራባዊያን
ሶሪያ ማዕከላዊ ባንካቸው በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከነበሩት ጥቂት ሀገራት አንዷ ነበረች:: በሌላ አነጋገር ሶሪያ በኒውዮርክ፣ በለንደን፣ በፍራንክፈርት፣ በቴል አቪቭ… ገንዘቧን አታስቀምጥምም፤ አታሳትምም:: ይህ ማለት በማዕከላዊ ባንክ የታተመው የገንዘብ መጠን ከኢኮኖሚው፣ ከጉልበት እና ከአምራችነቱ ትክክለኛ ፍላጎት ጋር ተጣጥሞ የሶሪያን ሕዝብ ተጠቃሚ አድርጓል:: በተጨማሪም ሶሪያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና ከዓለም ባንክ ምንም አይነት እዳ አልነበራትም:: የአሳድ ሶሪያ እና የጋዳፊ ሊቢያ እንዲህ ያሉትን ድርጊቶች ከሥነ ምግባር የራቁ ናቸው በማለት ውድቅ አድርገዋል::
ሶሪያ በሳይንሳዊ መንገድ የተሻሻለ የእሕል ዘር (ጂኤምኦ) በሕጋዊ መንገድ ከከለከሉት ጥቂት ሀገራት አንዷ ነበረች:: አሳድ ጂኤምኦዎች የሰውን ጤና ይጎዳል በሚል በሶሪያ ተግባራዊ እንዳይሆን ከልክለዋል:: ሶሪያ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች ሀገር ነች:: የነዳጅ ክምችቷም እ.አ.አ.በ2011 ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን በርሜል እንዲሁም እ.አ.አ 2011 የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቷ ደግሞ ስምንት ነጥብ አምስት ትሪሊየን ኪዩቢክ ጫማ ተገምቷል:: እነዚህን ሀብቶቿን እንዲጠቀሙ የተፈቀደችላቸውም የሀገሪቱ የመንግሥት ኩባንያዎች ብቻ ናቸው:: አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እነዚህን እውነታዎች በሶሪያ የሥርዓት ለውጥ ውስጥ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ የገቡበት ምክንያቶች አድርገው ያስባሉ::
ሶሪያ ዛሬ
አልጀዚራ እንደዘገበው ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ሩሲያ የሸሸውን የኣል-አሳድ ውድቀትን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው:: በጦርነቱ ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሶሪያዊያን ከሕዝቧ አንድ ሦስተኛ ያህሉ ለስደት ተዳርጎ ነበር:: ባለፈው ዓመት ከ782 ሺህ በላይ ሶሪያዊያን ከሌሎች ሀገራት ወደ ሶሪያ መመለሳቸውን የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አስታውቋል::
ኣል-ሻራአ በኣል-አሳድ መንግሥት ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች ፍትሕ ለመስጠት እና ሁሉንም ያካተተች ሶሪያን ለመገንባት ቃል ገብተዋል::
መንግሥታቸው የውጭ ግንኙነቱን መቀየር እና ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን ማስነሳት ችሏል:: ለአብነትም የሶሪያዉ ፕሬዝዳንት አህመድ አል-ሻራአ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው አሜሪካን የጎበኙ የሶርያ መሪ ሆነዋል::
በአሁኑ ወቅት ሶሪያዊያን ብዙ ሃይማኖታዊ ብጥብጥ፣ ተደጋጋሚ የእስራኤል ጥቃቶች እና ጥልቅ የኢኮኖሚ ፈተናዎች ቢኖሩባቸውም አብዛኛዎቹ ግፍ እና ጭቆና ከሶሪያ ዜጎች ጫንቃ ላይ ተነስቷል ብለው ያምናሉ:: ዛሬ ሶሪያዊያን ሀገራቸው በጦርነት ብትፈራርስም፣ የነበራቸው እንዳልነበረ ቢሆንም ለስደት እና መከራ ተዳርገው የነበረ ቢሆንም ከያሉበት ተጠራርተው ሀገራቸውን እንደገና ለመገንባት ተስፋን ሰንቀው ወደ ትውልድ መንደራቸው እየተመሙ ነው::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የታህሣስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


