
ሶሪያ በዓለም የጥንታዊ ስልጣኔዎች መገኛ ከሆኑት መካከል አንዷ ስትሆን የኪነ ጥበብ እና የባህል አሻራ ተሸክማለች። በምድራችን ቀደምት የሚባለው የሰው ልጅ ከሰፈረባቸው ሃገራት መካከልም አንዷ ናት።
በሜዲትራንያን የባህር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ሶሪያ በአሁኑ ወቅት አንዷ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገር ናት። ከ700ሺህ ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ስነ ቅሬቶች በሶሪያ ተገኝተዋል። በ3000 ቅ.ዓ አካባቢ እንደኖረች የሚነገርላት ኢልባ የተባለችው አንዷ የሶሪያ ከተማ በቁፋሮ ከተገኙ የጥንት መንደሮች ቀደምት ናት።
በጥንታዊው ዘመን ውስጥ በርካታ ቅኝ ገዥዎች ሶሪያን ወረው እና ገዝተዋት ነበር። ግብፅን ጨምሮ ሂታይቶች፣ ሱመራውያን፣ ሚታኒ፣ አሶራውያን፣ ባቢሎናውያን፣ ከንዓናውያን፣ ፊንቃውያን፣ አረማውያን፣ አሞራውያን፣ ፋርሶች፣ ግሪኮች እና ሮማውያን ተፈራርቀው ገዝተዋታል።
የሮማውያን አገዛዝ በወደቀ ጊዜ ሶሪያ የምሥራቃዊ ወይም የባይዛንታይን ግዛት አካል ሆናለች። በ629 ዓ.ም ሙስሊም ሠራዊት የባይዛንታይንን አገዛዝ አሸፀፈወ ሶሪያን ተቆጣጥረዋል። እስልምና በፍጥነት በአካባቢው ተስፋፋ፤ እናም የተለያዩ አንጃዎች ስልጣን ላይ ወጥተው ነበር።
ደማስቆ በመጨረሻ የእስልምናው ዓለም መናገሻ ሆነች፤ ምንም እንኳ ይህ ክብሯ በ742 ዓ.ም ላይ በኢራቋ ባግዳድ ቢተካም። ይህ ለውጥ በሶሪያ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል አስከተለ። በመሆኑም ለቀጣይ በርካታ ክፍለ ዘመናት ክልሉ በተለያዩ ቡድኖች ተመርቷል።
በ1508 ዓ.ም በወቅቱ በዓለም ላይ ገኖ በነበረው በኦቶማን ቱርክ ግዛተ መንግሥት ተወረረ። ይህ ወቅት በሶሪያ ታሪክ በአንፃራዊነት ሰላማዊ እና የተረጋጋ ዘመን ነበር፤ እንደ ሂስትሪ ዶት ኮም ገለጻ።
ሶሪያ የጥንታዊ ስልጣኔ ምድር
ሶሪያ በክርስትና እምነት ታሪክ ውስጥ ወሳኝ እና ተምሳሌታዊ ሚና ተጫውታለች። የሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ክርስትና እምነቱን የቀየረው ወደ ደማስቆ እየተጓዘ በነበረበት አጋጣሚ መሆኑ በእምነቱ ታሪክ ውስጥ በስፋት ይነሳል። ሶሪያ በርካታ ቤተክርስቲያኖች እና ገዳማት ያሉባት ሀገር ናት።
ፓልሚራ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የንግድ መስመርን ተከትላ የተነሳች የሶሪያ አንዷ ቀደምት ጥንታዊ ስልጣኔ መሠረት ናት። የፋርስን ንጉሥ ያሸነፈ እና አጠቃላዩን የሮማውያንን የምሥራቅ ግዛት የተቆጣጠረ አንድ ፓልሚራዊ ንጉሥ ነበር። ከዚያም እርሱን የተካችው እና ዜኖቢያ የተባለች ደንገጡሩ ግብፅን፣ ሶርያን፣ ፍልስጤምን፣ ጥቂቱን እስያን ክልል፣ ይሁዳን፣ እና ሌባኖስን በቁጥጥር ስር ያደረገውን የፓልሚራ ግዛተ መንግሥት መሰረተች። ይህም በሮማውያን ቁጥጥር ውስጥ ከመግባቱ ከ265 ዓ.ም በፊት ነበር።
ሶሪያ የእስልምና አካል የሆነችው በ632 ዓ.ም ነበር። ዋና መዲናዋ ደማስቆም በ7ኛው ክፍለ ዘመን የሙስሊም ኡምያድ ስርወ መንግሥት አካል እንደ ነበረች የባህል፣ የሀይማኖት እና የጥበብ ማእከል ሆነች። በዚህ ጊዜም ነበር ለታዋቂው የኡምያድ መስጅድ የተገነባው እና ከሁሉም የአዲሱ ግዛተ መንግሥት ክፍሎች በርካታ ምሁራን እና ጎብኝዎችን የሳበችው።
የጦርነት ምድር
ከ1090 ዓ.ም እስከ 1181 ዓ.ም ድረስ በተደረገው የመስቀል ጦርነት ወቅት ታዲያ በርካታ የሶሪያ ክልሎች በጠላት እጅ ወደቁ። ከዚያም በኋላ ሶሪያ የግብፁ አዩቢድ ስርወ መንግሥት አካል ሆነች። በ1400ዎቹ አካባቢ ደማስቆን እና አሌፖን ጨምሮ በርካታ ከተሞቿ ተቆርቁረው እንደነበር ሂስትሪ ዶት ኮም ያስነብባል።
በ1508 ዓ.ም የኦቶማን ግዛተ መንግሥት ሶሪያን በግዛቱ አካተታት። አረብኛ መደበኛ ቋንቋዋ ሆነ። ደማስቆም ወደ መካ ዋነኛ መሸጋገሪያ ሆነች። ሁሉንም የጎሳ ቡድኖች በአንፃራዊ ሠላም እና መስተጋብር መኖር የሚያስችል አንድ ማህበራዊ እና ሕጋዊ ስርዓት ተገንብቷል። ነገር ግን ይህ ሰላም በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወቅት የምእራባውያን ግዛተ መንግሥት መስፋፋትን ተከትሎ ይህ ሰላሟ መበጥበጥ ጀመረ።
የሳይከስ-ፒኮት ስምምነት
የአንደኛው የዓለም ጦርነት ለሶሪያ እና ለመላው የአረቡ ዓለም ሰላም አለመሆን እና አለ መረጋጋት እስከ አሁኑ ዘመን የዘለቀ ጦስ ትቶ አልፏል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ክልል ተንሰራፍቶ የነበረው የኦቶማን ቱርክ ግዛተ መንግሥት በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ እጅ እየወደቀ በመመናመን ላይ ነበር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም የኦቶማን ኢምፓየርን የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ሁለት ዞኖች አድርጎ የሸነሸነ ሚስጢራዊው የሳኮስ-ፒኮት ስምምነት ተፈረመ። በዚህ መሰረት የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ወታደሮች በ1910 ዓ.ም ደማስቆን እና አሌፖን ተቆጣጠሩ። የፈረንሳይ ጦር በ1912 ዓ.ም የአሁኖቹ የሶሪያ እና የሊባኖስ ግዛቶችን ተቆጣጠረ። እነዚህ ክፍፍሎች በግርድፉ ለ400 ዓመታት ያህል በቀጣናው ተንሰራፍቶ የነበረውን የኦቶማን ቱርክ አገዛዝ እንዲያከትም አድርገዋል።
የፈረንሳይ የአገዛዝ ዘመን ሶሪያ በሚኖሩ ሰዎች በኩል በሚነሱ አመፆች እና ነውጦች የተሞላ ነበር። ከ1917 ዓ.ም እስከ 1919 ዓ.ም በሶሪያውያን በፈረንሳይ ወረራ ላይ ተባብረው አሁን ታላቁ የሶሪያ አመፅ እየተባለ የሚታወቀውን ትግል ለማድረግ ተባብረው ተነሱ።
በ1928 ዓ.ም ሶሪያ እና ፈረንሳይ ያደረጉት ስምምነት ሶሪያ ራሷን የቻለች ነፃ ሀገር እንድትሆን የሚፈቅድ ሲሆን ነገር ግን ለፈረንሳይ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስልጣን የሰጠ ነበር።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የእንግሊዝ እና ነፃ የፈረንሳይ ወታደሮች ሶሪያን ተቆጣጥረዋል ። ነገር ግን ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በ1938 ዓ.ም ፈረንሳይ ሶሪያን መልቀቅ ጀመረች እና ሶሪያ ራሷን የቻለች ሀገር ሆና በመንግሥታቱ ድርጅት እውቅና የተሰጣት።
በርካታ ባእዳን ቅኝ ገዥዎች እየተፈራረቁ ለዘመናት የገዟት ታላቋ ሶሪያ በ1940ዎቹ እና 1960ዎቹ መካከል ነበሩት ጊዜያት ፖለቲካዋ በመፈንቅለ መንግሥቶች እና በብጥብጥ የተሞላ ነበር። በ1948 ዓ.ም በስዊዝ ቦይ ቀውስ የተነሳ ሶርያ ከሶቭየት ሕብረት ጋር ስምምነት ፈረመች:: ይህም ሩሲያ በሶሪያ ላይ በወታደራዊ ትብብር እና በንግድ አማካይነት አንዳች ረጅም እና ጥልቅ የሩሲያውያን ተፅእኖ በሶሪያ ላይ እንዲያርፍ አድርጓል።
በ1950 ዓ.ም ሶሪያ ከግብፅ ጋር ተጣመረች እና የተባበሩት የአረብ ሪፐብሊክ ሆኑ። ነገር ግን ሕብረቱ ከአጭር ጊዜ ቆይታቸው በኋላ በ1953 ዓ.ም በኋላ ፈረሰ። በ1950ዎቹ ተጨማሪ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች፣ ረብሻ እና አመፆች አጋጠሙት።
ይቀጥላል
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም