“ሶኖግራፈር”

0
165

ልዩ ስልጠና ወስዶ ብቃቱ በተረጋገጠ ባለሙያ “ሶኖግራፈር” የሚካሄድ የአልትራሳውንድ ምርመራ እንከንየለሽ የማህፀን ካንሰር መለያነቱ 96 በመቶ ውጤታማ መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

የበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ በመረጃ ምንጭነት ለንባብ እንዳበቃው ንፅፅር ከተሰራባቸው ስድስት የማህፀን ምርመራ ሙከራዎች፤ የአልትራሳውንድ ምርመራ 96 በመቶ የማህፀን ካንሰር ያለባቸውን በትክክል እንደሚያሳይ በጥናት አረጋግጧል፡፡

በብሔራዊ የጤና እንክብካቤ ጥናት ምርምር ተቋም /NIHR/ የገንዘብ ድጋፍ በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ ኘሮፌሰር ሱዳ ሱንዳር የተመራው ምርምር ትክክለኛነቱን አረጋግጧል፡፡

በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የማህፀን ካንሰር ኘሮፌሰር እና ባልደረቦቻቸው በሁሉም ዓይነት የማህፀን ካንሰር ምርመራዎች ተመሣሣይ የናሙና ተሳታፊዎች ላይ ምርምር ሲያካሄዱ ይሄኛው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ምርምሩ የበሽታውን ምልክቶች መሠረት አድርጐ ለበሽታው በእጅጉ ተጋላጭ በሆኑት የአረጡ ወይም የወር አበባ ማየት ባቆሙ ላይ የአተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የአልትራሳውንድ ምርመራው በብቃት በሰለጠኑ ባለሙያዎች /ሶኖግራፈር/ መከወኑ የማህፀን ካንሰር ተጠቂዎችን የመለየት ደረጃው ከፍ ያለ እንዲሆን ማስቻሉም ነው የተጠቆመው፡፡

አዲሱ የማህፀን ካንሰር ተጠቂነትን ስልጠና በወሰደ ባለሙያ በአልትራሳውንድ መርምሮ መለየት፤ ከማረጥ በፊትም ሆነ በኃላ ሴቶችን የሚጠቅም መሆኑን ተጠቁሟል።  ተመራማሪዎቹ በአልትራሳውንድ የማህፀን ካንሰርን አስቀድሞ መመርመር አስፈላጊ መሆኑንም በአፅንኦት ገልጸዋል።

በተለይም ህመሙ ስር ሳይሰድ ቀደም ብሎ ከታወቀ ለማከም ቀላል እና የሚፈለገውንም ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ነው ያሰመሩበት ተመራማሪዎቹ፡፡

በአብዛኛው ልዩ ስልጠና በወሰዱ ባለሙያዎች /ሶኖግራፈር/ በአልትራሳውንድ ምርመራ የማህፀን ካንሰርን መለየት ማስቻልን የበለጠ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ለማድረግ በበየነ መረብ  ስልጠና መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡ ስልጠናውን ለሚያጠናቅቁ ባለሙያዎችም የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ ነው በማደማደሚያት የሰፈረው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here