ሻደይን ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተጠቆመ

0
93

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሻደይ በዓልን ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በአብሮነት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ እዮብ ዘውዱ ለአሚኮ  እንደተናገሩት የአብሮነት፣ የአንድነት እና የመተባበር እሴት መገለጫ የሆነውን የሻደይ በዓል ለማክበር ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በዓሉ በአደባባይ በሰቆጣ ከተማ እና በብሔረሰብ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ ከተሞች ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ እንደሚከበር ገልጸዋል።

በዓሉ ጥንታዊነቱን እና ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በመንደር፣ በቀበሌ እና በወረዳ ደረጃ ልጃገረዶች በባህላዊ አልባሳት እና ጌጣጌጦች ተውበው  ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።  የዘንድሮው የሻደይ በዓል በባህል ፌስቲቫል እና በሌሎች ዝግጅቶችም ታጅቦ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል። ሻደይን ለመታደም ለሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ምቹ የሆቴል እና የመዝናኛ ስፍራዎች መዘጋጀታቸውንም አቶ እዮብ አንስተዋል።

በሰቆጣ ወረዳ የሽመድር ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አለምናት ቢበይን በሰጠችው አስተያየት  ”የሻደይ በዓል በጉጉትና በፍቅር የምንጠብቀው ታላቁ ባህላችን ነው፤ የዘንድሮውን የሻደይ በዓል እንደወትሮው ሁሉ በደመቀ መልኩ ለማክበርም የሻደይ ቀሚስ፣ ድሪ ፣ማርዳ፣ መስቀል እና የመሳሰሉ ጌጣጌጦችን ገዝተን አዘጋጅተናል” በማለት ተናግራለች።

”ሻደይ ከነፃነት ባለፈ የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የመተባበር እና የመተጋገዝ እሴት ያለው በመሆኑ የምናፍቀው በዓል ነው” ያለችው ደግሞ በወረዳው የቲያ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት መቅደስ ሞላ ናት። የዘንድሮውን የሻደይ በዓል በደመቀ መልኩ ለማክበር ከሌሎች የአካባቢው ሴቶች ጋር ቡድን መስርተው ለበዓሉ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቁማለች።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here