ሽንጠ ረዢሙ ባለክብረ ወሰን

0
101

በ1976 እ.አ.አ ከተሰሩ ስድስት ካዲላክ ሊሞዚን ተገጣጥሞ የተሰራው 30 ሜትር የሚረዝመው ባለ 26 ጐማ ተሽከርካሪ በአዲስ  መልክ ታድሶ ዳግም ለክብረወሰን መብቃቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡

በአሜሪካዊው ጄይ ኦህበርግ የተሰራ 18 ነጥብ 28 ሜትር ወይም 60 ጫማ የተለካ ከፊት እና ከኋላ በተገጠመለት ሞተር የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ በ1986 እ.አ.አ ለክብረ ወሰን በቅቶ ነበር፡፡ በወቅቱ የተሽከርካሪው ምስል በየህትመቶች እና በፊልም ቀረፃዎች ላይም ለእይታ በቅቶ ነበር፡፡

ዝናው ብዙም ሳይቆይ ግን በተቀመጠበት በኒው ጀርሲ ከመጋዘን ጀርባ ተዘንግቶ ዓመታትን አስቆጥራል፡፡

በቅርቡም ለዓመታት ተዘንግቶ በተቀመጠበት ለሽያጭ መቅረቡን በድረ ገጽ የተመለከቱ ማይክል ዲዘር እና ማይክል ማኒንግ የተሰኙ የተሽከርካሪ አድናቂዎች ገዝተው ባደረጉለት እድሳት ወደ ቀደመ ዝናው መመለሳቸው ነው ለንባብ የበቃው፡፡

ከተደረጉለት እድሳቶች መካከል አዲስ ነጭ ቀለም መቀባቱ፣ አዳዲስ ጐማዎች መገጠማቸው እና ቀደም ብሎ ከነበረው ርዝመት ጥቂት ኢንች መጨመሩም ተጠቅሷል፡፡

ረዢሙ ተሽከርካሪ ሙቅ የውኃ ገንዳ መዘፍዘፊያ (ጃኩዚ)፣ ማቀዝቀዣ፣ ቴሌቪዥን፣ የመዋኛ ገንዳ፣ እና አነስተኛ ሂሊኮኘተር ማረፊያም እንዲኖረው አድረገዋል- ያደሱት ባለሙያዎች፡፡

ሽንጠረዢሙ ባለክብረወሰን ተሽከርካሪ 75 ሰዎችን የመያዝ አቅምም አለው፡፡ ተሽከርካሪው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ይችላል፤ ሆኖም አንድ ነገር አሳሳቢ እና እንቅፋት ሆኖበታል- የማይተጣጠፍ ሰላሳ ሜትር ርዝመቱ፡፡ ተሽከርካሪው አሁን ያለበት ቦታ ለማድረስ ተቆራርጦ መጓጓዙም ነው የተጠቀሰው፡፡ ምነው ቢሉ ቀጥ ካለ አውራ ጐዳና ውጪ መሽከርከር ባለመቻሉ ነው፡፡

በአዲስ መልኩ ያሳደሱት የተሽከርካሪው ባለቤቶች 250 ሺህ ዶላር ወጪ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ተሽከርካሪው በፍሎሪዳ ዴዘር ላንድ ፓርክ – ኦርላንዶ የተሽከርካሪዎች ሙዝዬም እንደሚገኝ ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here