ወ/ሮ ትብለጥ ለሥራ በነበሩበት ምዕራብ ጎጃም ዞን ከተዋወቁት ግለሰብ ጋር ትዳር መመሥረታቸውን ያስታውሳሉ። ሁለት ልጆችን ያፈሩበት ትዳር በመተሳሰብ ሲመራ ቢቆይም ባለቤታቸው ለተሻለ ሥራ ወደ አዲስ አበባ ከተጓዙ በኋላ ግን ለሰባት ዓመታት የቆየ ትዳራቸው በነበረ ፍቅሩ መቆየት አልቻለም :: መራራቁ የፈጠረው ክፍተት ደስ ስላላሰኛቸው ትዳሩን በሥምምነት ሲያፈርሱ ልጆቻቸው ህፃናት በመሆናቸው እናታቸው ጋር ሊያድጉ ባል ለልጆቻቸው ተቆራጭ ለመሥጠት ተስማምተው ትዳሩ ቢፈርስም የልጆች ተቆራጭ ደስ ባላቸው ወቅት ወይም በበዓል ቀናት ብቻ ማድረጉ ቅሬታን በመፍጠሩ በፍርድ ቤት እንዲወሠን ሆነ::
ባለቤታቸው የሰባት ሺህ ብር ደሞዝ ተከፋይ ስለነበሩ በወር ለሁለቱ ልጆች 1 ሺህ 500 ብር ሊከፍሉ በፍርድ ቤት ተወስኖ ተስማሙ። ይሁንና ልጆቹ እድሜያቸው ለትምህርት ቤት ሲደርስ ወጭአቸው ቢጨምርም አባት ግን ፍርድ ቤት የተወሰነው ይሄው ነው በሚል ተጨማሪ ብር ቢከለክሏቸውም ድጋሜ ከመካሰስ በሚል ተቸግረው እንደሚኖሩ በመግለፅ ፍርድ ቤት የወላጅ ገቢ ሲሻሻል ተወስኖ በነበረው ተቆራጭ ላይ ተጨማሪ እንደሚያደርግ የሚያመለክት አሰራር ቢኖር መልካም እንደነበር ያነሳሉ::
ለመሆኑ ስለ ልጆች የቀለብ መብት ሕጉ ምን ይላል? ስንል ጠበቃና የሕግ አማካሪ አፀደ አለባቸውን ጠየቅን::
ጠበቃዋ እንደሚገልፁት ቀለብ ማለት ቀለብ ከፋዩ ለቀለብ ተቀባዩ የሚከፍለው ለልጁ እንክብካቤ፣ ጥበቃ እና ጥቅም የሚውል በጥሬ ገንዘብ ወይም በልዩ ሁኔታዎች በአይነት የሚከፈል ክፍያ ነው። ኢትዮጵያ የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽንን በአዋጅ ቁጥር 10/1984፣ የአፍሪካ የህጻናት መብቶችንና ደህንነት ቻርተርን ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 283/1994 ማጽደቋ ይታወቃል:: ሕጉ ዳኞች ቀለብ ሲቆርጡ መነሻ ማድረግ ያለባቸውን ነጥቦች የሚያመላክት እንደመሆኑ መጠን፣ ዳኞች መጠኑን ሲወስኑ ጥንቃቄ ካላደረጉ የሕጉ ዓላማ ተግባራዊ ላይደረግ ይችላል:: እንዲህ በሆነ ጊዜ ሕጉና ተግባሩ የተለያዩ ይሆናሉ::
ቀለብን የሚመለከተው ሕግ ተግባራዊ ባልተደረገ መጠን ወይም ለአፈጻጸሙ ጠንካራ ሥርዓት ካልተበጀለት ልጁን የማሳደግ ግዴታ የወሰደችው ወላጅ በቀለብ ማነስ ሕፃኑን የማሳደግ መብቷን አሳልፋ ልትሰጥ ትችላለች::
በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን የሕፃናትን ቀለብ የማግኘት መብት የተመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኛሉ:: የሰነዱ አንቀጽ ሰባት ሕፃናት በተቻለ መጠን ወላጆቻቸውን የማወቅና እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል::
አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ አራት ደግሞ ፈራሚ መንግሥታት ሕፃናት ከወላጆቻቸው ወይም ኃላፊነት ካለበት ሌላ ሰው ቀለብ የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያስከብር ተገቢ የሆኑ ዕርምጃዎች እንዲወስዱ ግዴታ ይጥላል::
የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደኅንነት ቻርተርም የማንኛውም ሕፃን ቀለብ የማግኘት መብት በወላጆች የትዳር ሁኔታ ምክንያት ሊነፈግ እንደማይገባ ይደነግጋል::
በተጨማሪ እነዚህ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች
ቀለብን ጨምሮ ለሕፃናት የሚሰጡ መብቶች የሕፃኑን የፍላጐት ቀዳሚነት መሠረት ያደረጉ ሊሆን እንደሚገባ ይገልጻሉ::
ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ የተገለጹትን ዓለም አቀፋዊ እና አኅጉራዊ ስምምነቶች ከመፈረም ባለፈ የሕፃናትን መብት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ደንግጋለች:: ሕገ መንግሥቱ ሕፃናትን በተመለከተ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች የሕፃናት ደኅንነት በቀዳሚነት ሊታሰብ እንደሚገባ ደንግጓል:: ቀለብን በተመለከተ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ለብዙ ዘመናት ገዥ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን፣ ከተወሰኑ በስተቀር በክልሎችም የቤተሰብ ሕጎች ከፌዴራሉ ጋር በተመሳሳይነት ተሻሽለዋል::
የተሻሻሉት የቤተሰብ ሕጎች በመግቢያቸው ላይ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ለመሻሻላቸው መነሻ እንደሆኗቸው ከመግለጻቸው በስተቀር በይዘታቸው የሕፃናት ፍላጐት ተቀዳሚ ቦታ ከመስጠት ውጭ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ከተደነገጉት አንቀፆች ጋር ተመሳሳይ ናቸው:: የቀለብ መቁረጥ ግዴታ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 197 እስከ 214 በዝርዝር የተደነገገ ሲሆን የልጆች ቀለብ በአንቀጽ 113 ተመልክቷል::
ቀለብ አለመቁረጥ ወይም ማቋረጥ በአገራችን የወንጀል ሕግ ወንጀል ሆኖ ያስቀጣል:: የወንጀል ሕግ አንቀጽ 658 ይመለከቷል:: በፍቺ ጊዜ ባል እና ሚስት የሕፃናት ቀለብን በተመለከተ ተስማምተው በፍርድ ቤቶች ሊያፀድቁ ይችላሉ:: ስምምነት በሌለበት ጊዜ ግን የልጆችን ቀለብ መወሰን የፍርድ ቤቶች ሥልጣን ነው::
የአወሳሰኑ ዘዴ በጋብቻም ሆነ ከጋብቻ ውጭ ለተወለዱትም ልጆች ተመሳሳይ ነው:: ፍርድ ቤቶች መጠኑን የሚወስኑበት መመሪያ፣ ማኑዋል ወይም ቀመር ስለሌላቸው በተግባር ለልጆች የሚቆረጠው ቀለብ ከፍርድ ቤት ፍርድ ቤት ይለያያል:: አንዳንድ ጥናቶች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አካባቢ ቀለብ ለመወሰን የሚረዳ ፎርም እንዳለ ቢያመለክቱም፣ በተግባር ወጥነት ባለው መልኩ እንደማይሠራበት ይገልጻሉ::
ስለዚህ ቀለብ እንዲሻሻል የገቢ መጠን መጨመር መቀነስ ቀለብ እንዲሻሻል ወደ ፍርድ ቤት ማቅርብ እንዳለበት የቤተሰብ ሕጋችን አንቀፅ 203 ገቢ መጨመር የታወቀን ገቢ ፍርድ ቤቱ አጣርቶ መወሰን አለበት። ይሁን እንጅ ድንጋጌዎቹ ዝርዝር እና አመላካች ባለመሆናቸው በህጻናት ቀለብ ውሳኔዎች ላይ በተግባር የሚታዩ የወላጆችን ገቢ ወይም አቅም ማጣራት ላይ የሚታዩ ልዩነቶች የልጆች ቀለብ ውሳኔዎች ፍትሃዊነት ፣ ወጥነት እና ተገማችነት የሌላቸው እንዲሆኑ አድርጓል።
ጠበቃ አፀደ እንደሚገልፁት የልጆችን የቀለብ መብት ሲወሰን የልጆቹን እና የወላጆቻቸውን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው ከቤተሰብ ሕጉ መረዳት ስለሚቻል በአንድ በኩል የልጆችን ሁኔታ እና ጥቅም በሌላ በኩል የወላጆችን ገቢ፣ እድሜ፣ ጤና እና የኑሮ ሁኔታ ያማከለ የህጻናት ቀለብ የማግኙት መብት ቀለብ ለልጆች አስተዳደግ መሰረታዊ ፍላጎት ልዩ ወጭ የልጅን ጥቅም ፍላጎት ያማከለ መሆን አለበት
የልጅ ቀለብ መክፈል ግዴታ የወላጅ በጋብቻ መሆን አይጠበቅም። የቀለብ ጥያቄ በቀረበ ጊዜ የሚፈፀም ነው::
ዳኞች የልጅ ቀለብ በሚወስኑበት ወቅት መሰረታዊ ፍላጎት ማለትም ምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳት፣ ጤና አጠባበቅ ፣ ትምህርት እና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ወጪዎች እንዲሁም የልጁን ልዩ ፍላጎት ከግምት ማስገባት አለባቸው::
ለአብነት ትክክለኛ ገቢ አለመታወቁ ገቢን መደበቅ እንዲሁም አንዴ ወደ ፍርድ ቤት ሄደው ከአስወሰኑ በኋላ የቀለብ ከፋዩ ገቢ ሲያድግ እንዲሻሻል ባለማቅረብ ልጅን በተናጥል የሚያሳድግ ወላጅ እናት ወይም አባት የቀለብ ይሻሻልልኝ ጥያቄን በፍርድ ቤት ቀርበው አለማስወሰናቸው በርካታ ሕፃናት በዚህ መልኩ የሚገባቸውን ቀለብ ሳያገኙ ለልመና እና ለችግር የሚዳረጉ መኖራቸው እውነት ነው::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም