ቀብድ ምንድን ነው?

0
159

በኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሕግ ከቁጥር 1883 – 1885 ድረስ ባሉት ሦስት አንቀፆች ቀብድን የሚመለከቱ ሀሳቦች ተካተውበታል፤ ቢሆንም ግን “ቀብድ” ለሚለው ቃል የሚሰጡት ትርጉም የለም፡፡

ለሕግ ቃላት ትርጉም በመስጠት የሚታወቀው ብላክስ ሎው (blacks law dictionary) መዝገበ ቃላት ግን  “ቀብድ ማለት ተዋዋይ ወገኖች ከግዴታቸው እንዳያፈነግጡ ለማድረግ ተብሎ የሚሰጥ የተሸጠ ዕቃ ከፊል ዋጋ እንዲሁም ዕቃው መሸጡን ለማሳየትና ለማፅደቅ ተብሎ አንዱ ተዋዋይ ለሌላው የሚሰጠው የመተማመኛ ገንዘብ ነው” በሚል ተርጉሞታል።

በኢትዮጵያ ቀብድ ከጥንት ጀምሮ ኅብረተሰቡ ሲጠቀምበት የቆየ እንደሆነ ፍትሕ ሚኒሥቴር በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ ከኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1883 ላይ እንደሰፈረው ቀብድ ገዢው ወገን ለሻጩ ወገን በማያከራክር ሁኔታ ውል መደረጉን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በፍትሐ ብሔር ሕግ በውል አፈፃፀም ድንጋጌዎች መሠረት በፅሑፍ ሊደረጉ እና በፍርድ ቤት መዝገብ ወይም ውል የማዋዋል ሥልጣን በተሰጠው አካል ፊት መሆን የሚገባቸው ውሎች በፅሑፍ ሳይደረጉ  ቀብድ መሰጠቱ ብቻ ውል መፈፀሙን እንደማያረጋግጥ አመላክቷል፡፡

በሌላ አባባል የቀብድ ክፍያ ማለት በተዋዋይ ወገኖች መካከል ውል መኖሩ እና ተዋዋይ ወገኖች በውሉ ለመገደድ ወይም ውሉን እስከ መጨረሻው ተከታትሎ ለመጨረስ ያላቸውን ፍላጎት ለማሳየት ሲባል በመያዣነት ቀብድ ሰጪ ለቀብድ ተቀባይ የሚሰጠው ክፍያ ነው፡፡ ይህም በተዋዋይ ወገኖች መካከል የሺያጭ ወይም የአገልግሎት የውል ስምምነት መኖሩን፤  በቀጣይም ሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች በውል ስምምነቱ ለመገደድ ያላቸውን ፍላጎት የሚገልፁበት ነው፡፡

የሚከፈለው የክፍያ መጠን እንደየ አከባቢው ሁኔታ ወይም እንደ ሥራው ዓይነት እና ስምምነት ሊለያይ ይችላል፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1884 ስር እንደተደነገገው ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር ቀብድ ተቀባይ ውሉ ከተፈፀመ በኋላ የቀብዱን ገንዘብ መመለስ ወይም ውሉ ሲፈፀም ከጠቅላላው ክፍያ መቀነስ ያለበት መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ ይህም ለተዋዋይ ወገኖች ምርጫ የተተወ ቢሆንም ሌላ ስምምነት ካላደረጉ ውሉ ሲፈፀም የቀብድ ክፍያ እንደ ቅደመ ክፍያ ይቆጠራል ወይም ቀብድ ተቀባይ ለቀብድ ሰጪ ይመልሳል ማለት ነው፡፡

ቀብድ ሰጪና ቀብድ ተቀባይ ውሉን ለመተው ቢፈልጉ በቀብድ ክፍያው ላይ የሚኖረው ውጤት የተለያየ መሆኑም የፍትሐ ብሔር ሕጉ ድንጋጌ ያስገነዝባል፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1885 ላይ እንደተቀመጠው  ሌላ ስምምነት ከሌለ በስተቀር ቀብድ ሰጪ የሰጠውን የቀብድ ክፍያ በመልቀቅ ውሉን መተው ይችላል፡፡ ይህ ማለት ቀብድ ሰጪ ውሉን የሚያፈርስ ወይም የሚተው ከሆነ የከፈለውን የቀብድ ገንዘብ ከቀብድ ተቀባይ ላይ ላለመቀበል መወሰን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ቀብድ ተቀባይ የተቀበለውን ቀብድ እጥፍ በመክፈል ውሉን  መተው  ወይም  ማፍረስ ይችላል፡፡ ይህም ቀብድ ሰጪና ቀብድ ተቀባይ ውሉን ሲያፈርሱ የሚከፈለው የቀብድ ክፍያ መጠን አንድ አይነት አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ቀብድ ተቀባይ የቀብዱን እጥፍ እንዲከፈል ሕጉ አስገዳጅ ያደረገው ውሉ ባለመፈፀሙ ምክንያት በሌላኛው ወገን (በቀብድ ሰጪ) ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እንደማካካሻ እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡

ለአብነት ገዢ እና ሻጭ አንድን ቤት ሲሻሻጡ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1723 (1) ስር የተመለከተውን መስፈርት /ፎርም/ ባያሟሉም ሻጭ ለዚሁ የሺያጭ ውል ማስፈፀሚያ ቀብድ መቀበሉ ከተረጋገጠ በማያከራክር ሁኔታ ውሉ መደረጉን ያረጋግጣል።

አንድ ውል የሕጉን ፎርም ካላሟላ በሕግ ፊት የማይፀና ይሆናል፤ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ የቀብድ ገንዘብ ክፍያ ካለ ውሉ የሕጉን ፎርም ያላሟላ ቢሆንም የቤት ሺያጭ ውል ስለመኖሩ የማያከራክር ማረጋገጫ ስለሆነ ውሉ የፀና ይሆናል፡፡ ነገር ግን የተከፈለው ክፍያ ቀብድ መሆኑ በውሉ ላይ ካልተገለፀ ቀብድ ነው ተብሎ ሻጭ እጥፍ እንዲከፍል የማያስገድድ ከመሆኑ በላይ ውሉ መኖሩንም ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም።

የቀብድ ክፍያ መኖሩ የውሉን መኖር የሚያረጋግጥ ብቁ ማስረጃ ቢሆንም ተዋዋይ ወገኖች ውሉን ለማፍረስ ተቃራኒ ስምምነት ካላደረጉ በቀር ቀብድ ተቀባዩ የተቀበለውን ገንዘብ እጥፍ አድርጎ በመመለስ፣ ቀብድ ሰጪው ደግሞ ይህንኑ የሰጠውን ገንዘብ ለተቀባዩ በመልቀቅ ያለ ተጨማሪ ሁኔታ ውሉን የማፍረስና በመካከላቸው የተመሠረተውን ግዴታ ለማስቀረት መብት አላቸው።

ፍርድ ቤቶችም በተዋዋይ ወገኖች መካከል ተቃራኒ ስምምነት እስከሌለ ድረስ ሻጩ የቀብዱን እጥፍ ከፍሎ ውሉን በማፍረስ የሸጠው  እንዲመለስለት ከጠየቀ መወሰን የሚገባቸውና ተገዶ እንዲፈፅም ማድረግ የሌለባቸው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

የቀብድ እና የቅድመ ክፍያ ልዩነትም በተዋዋይ ወገኖች  ሌላው የሚነሳው ጉዳይ ነው፡፡  መረጃው እንደሚያመላክተው አንድ ክፍያ ቀብድ ከሆነ ከፋይ ውሉ ቀሪ ቢሆን የሚያስመልሰው የቀብዱን እጥፍ ነው፡፡ ቅድመ ክፍያ ከሆነ ግን ከፋይ ገንዘቡን የሚያስመልሰው በፍርድ ቤት ክስ በመመሥረት ውሉ ባለመፈፀሙ የደረሰበትን ኪሳራ በማስረዳት እና ያወጣውን ወጪ በመጠየቅ ነው፡፡

ከዚህ  መረዳት የሚቻለው ቀብድ በሚሆንበት ወቅት ጉዳት መኖሩን ሳያመለክት ቀብድ ሰጪ ውሉን ካፈረሰው ሰው ላይ የተከፈለውን ገንዘብ  እጥፍ  መቀበል እንደሚችልና ቅድመ ክፍያ ከሆነ ግን ከፋይ የሚቀበለው የተከፈለውን ገንዘብ ያክል ብቻ ሆኖ ተጨማሪ ክፍያዎችን ለመቀበል ጉዳት መኖሩን ማመልከት እንዳለበት ነው፡፡

ቀብድ የከፈለ ሰው ውሉን ላለማፍረስ እንደማሰሪያ (እንደ መያዣ) የሚይዘው ይሆናል፡፡ ውሉን  ለማፍረስ  ሲወስን  ገንዘቡን ለመተው አምኖበታል ማለት ነው፡፡በተጨማሪም ቀብድ ተቀባይ የተቀበለውን ቀብድ እንዲመልስ አይገደድም፡፡

በቅድመ ክፍያ ወቅት ግን ይህ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ለዚሁ ውል ያወጣቸው ወጪዎች ከሌሉ በስቀር የተቀበለው ቅድመ ክፍያ እንዲመልስ ይገደዳል ማለት ነው፡፡

የሁለቱ የክፍያ አይነቶች (ቀብድ እና ቅድሚያ ክፍያ) ጥቅም ሲታይ ቀብድ የፍርድ ቤት እንግልት እና ወጪን የሚቀንስ እና በአብዛኛው በእርግጠኝነት የሚገኝ ነው፡፡ የቅድመ ክፍያ ገንዘብ የሚከፈለው በውሉ ለመገደድ ያለን ፍላጐት ለመግለፅ ሳይሆን ወደ ፊት የሚመጣውን የእዳ መጠን ለመቀነስ ታስቦ የሚፈፀም ክፍያ ነው፡፡ ቀብድ ግን በውሉ ለመታሰር እና ውል ስለመኖሩም ለማስረዳት በማሰብ የሚደረግ የውል አይነት ነው፡፡

መረጃ

“ሕግን አለማወቅ እና የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት አያድንም”

ለሕግ ቃላት ትርጉም በመስጠት የሚታወቀው ብላክስ ሎው የሕግ መዝገበ ቃላት በተሻሻለው ስድስተኛ እትሙ (Black’s Law Dictionary, 6th ed.,) ለሕግ በሰጠው ቃል  ስልጣን ባለው አካል የተደነገገ የተግባር ወይም የምግባር ደንብ እና አስገዳጅ ኀይል ያለው አካል ነው። ይህንንም ዜጎች ሊታዘዙት እና ሊከተሉት የሚገባ ሆኖ ማዕቀብ ወይም ሕጋዊ አስገዳጅነት የሚጥል ሕግ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

በመሆኑም የአንድ ሀገር ሕግ ሰላምን ፣  ነባራዊ ሁኔታውን ፣ የግለሰብ መብቶችን ለማስጠበቅ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን እና ሥርዓት ያለው ማህበራዊ ለውጥ እንዲኖር ለማድረግ እንደሚያገለግል ፍትሕ ሚኒሥቴር በገጹ አስፍሮታል።

በወንጀልም ሆነ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ሕጎቹ ሥልጣን ባለው የሕግ አውጪ አካል ወጥተው ከፀደቁበት ቀን ጀምሮም በሥራ ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ዜጎች የሕጎቹን መኖር ወይም መውጣት የማወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡

ይኸውም “ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም” የሚለው የሕግ መርህ  ሕግን የማያውቅ ሰው ይዘቱን ባለማወቅ ብቻ ሕጉን በመተላለፍ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ እንደማይችል የሚገልጽ የሕግ መርህ ነው።

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የታህሣስ  20  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here