ባለፈው ሳምንት እትማችን አስገመገመ ክረቱ በሚል ርዕስ ቀዳሚውን ክፍል ማስነበባችን ይታወሳል። በዚያ ቀዳሚ ክፍል “በ2004 ዓ.ም ክረምት አጎቴ ቤት ሳለሁ” ብሎ የጀመረው ትረካ በርከት ያሉ አዝናኝ ገጠመኞችን አስነብቦናል።
ይህ ቀጣይ ክፍል ደግሞ ቀንሲጥል በሚል ርዕስ እንደሚከተለው ተሰናድቶ ቀርቧል፤ መልካም ንባብ እንዲሆንላችሁ ምኞታችን ነው።
ወደ መስፍን በቀለ ሙዚቃ ተመልሰን ዛሬም ቀጥለናል። የክረምት ወር በተለይ ሐምሌ እና ነሀሴ ወራት ብቻውን ለተቀመጠ፣ ሌላውን ሰው ማየት አስጠልቶት ፍቅረኛውን ብቻ እያስታወሰ ለሚቆዝም ወጣት ከባድ ነው።ሲበርደው፣ስትናፍቀው፣ዝናቡ ሲመጣ፣በረዶው ሽው ሲል ፣ቅዝቃዜው ሲበረታ ብቸኝነቱ ከባድ ነው።ትራሱን አቅፎ በብርድ እና ፍቅር የሚናፍቅ ልጅ አለሁህ ባይ የለውም።ትመጣለች ብሎ በናፍቆት ሰቀቀን እንቅልፍ ያጣል፤ እሷ ግን የለችም። ቀኑ በጽልመት ሲወረስ፤ ብርድ አካባቢውን ሲሞላው፤ ጉም እና ደመና ሰፈሩን ሲጋርደው ለሰው የጭንቀት ስሜትን ይፈጥራል። መስፍን ክረምት እና ፍቅር ምን ያህል የተባበሩ የናፍቆት መሳሪያዎች እንደሆኑ በግጥሞቹ ይናገራል። ለዚህም ይህንን ናፍቆት ብቻውን እንደማይወጣው አውቆ ፍቅረኛውን “ነይ” ይላል።
“ነይ እንዲሞቅ አንሶላው ነይ እንዲሞቅ ትራሱ
አቀዝቅዞታል ቤቴን በረዶ እና ነፋሱ
ነይ በክረምት ነይ በብርድ
ሰው አይችልም ሆዱ”
በክረምት ወራት ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴ ነይልኝ እና የግሌ ላድርግሽ ሲል ይለምናታል።የመምጣት ግብዣ አይደለም። ነይልኝ አልቻልሁም የሚል ቅዝቃዜ ውስጥ ሆኖ ሙቀት እንደሚፈልግ ፤ወደ እናቱ ጉያ ለመሸጎጥ እንደሚሳግ ጫጩት የመለመን እንጂ። መስፍን እኔን አታዩኝም ወይ ክረምት እና ፍቅር እንዴት እንደከበዱኝ ሲል በተከታዩ ግጥም የጋራ ሰዋዊ ችግር መሆኑን ይገልጻል ።
“ሰው ያጣማ እንጃለት
ብቻውን ሆኖ በክረምት፤
ሐሳቡንም አይችለው
አፍቅሮ ያጣ ሰው”
የበጋውን ወራት ያንቺን ፍቅር ፍለጋ ስባዝን ባጅቼ፤ ደግሞ በክረምቱ እንዳልደግም እባክሽ ባይሆን በመስከረም አለሁልህ የሚል ተስፋ ስጪኝ ሲል እንሰማዋለን። ከመስፍን በቀለ በተመሳሳይ ዘመን የተሰራው የአህመድ ተሾመ ተጠየቂ ናዝሬት ሙዚቃ የክረምቱን የረፍት ጊዜ ያስታውሳል። ምሽት ላይ የእግር ጉዞ ሲወጣ የሚያገኛትን ቆንጆ እያስታወሰ ያዜማል። የት ሄዳ ጠፋችብኝ ብሎ ናዝሬትን በጥያቄ ያጣድፋታል።
“ክረምቱን በናዝሬት በአዳማ ከተማ
ምሽት ለእግር ጉዞ የምትወጣው ቀድማ፤
ምነው ዘንድሮ ላይ ለዓይን ተከለለች
ተጠየቂ ናዝሬት ያቺ ልጅ የት አለች”
ክረምቱ ለአርሶ አደሮች በሥራ ብዛት የሚጠመዱበት ቢሆንም እንኳን በከተሞች የረፍት ጊዜ ነው። በልዩነትም መምህራን እና ተማሪዎች የረፍት ጊዜያቸውን የሚያጣጥሙበት ነው።በትምህርት ተወጣጥሮ የነበረ አዕምሮን በማዝናናት የሚያሳልፉበትም ነው። አህመድ ተሾመም በዚህ የረፍት ጊዜ ነው፤ ማምሻውን የእግር ጉዞ ሲያደርግ የሚያያትን ወጣት አፍቅሮ፤ሁልጊዜም እሷን አገኛለሁ ብሎ በመገኛዋ ዝናብ እና ብርዱን ችሎ ቢጠብቃት ያጣት።አምና እና ታች አምና በክረምቱ ያያት ነበር። “ዘንድሮ የት ሄደች?” እያለ ናዝሬት የት ደበቅሻት ሲል ይጠይቃል።ፍቅሩ የዓይን ነበር፤ አላናገራትም፤አድራሻዋን አያውቅም። ዛሬ ሲያጣት ግን ናፍቆት እና ብቸኝነት በርትቶበታል። ያሳደግሽኝ ናዝሬት ፍረጂኝ ያቺን ልጅ የት ደበቅሽብኝ ይላል።
በግሌ መረዳት የአበበ ተካ ሙዚቃዎች ክረምት አካባቢ በስፋት ሲደመጡ አያለሁ። ምናልባትም አበበ ተካ ብዙዎቹን ዘፈኖቹን ለፍቅረኛው የዘፈነላት በመሆኑ እውነተኛ ታሪክ ላይ መመስረታቸው ሊሆን ይችላል። አበበ ተካ “ሰው ጥሩ” የሚለውን አልበም ፍቅረኛው ጥላው አሜሪካን ሀገር በመሄዷ ምክንያት በናፍቆት እና ጽኑ ፍቅር የተሰራ ነበር። አንዳንድ ቀን አለ። ኃይለኛ ዝናብ መጣ ተብሎ መብረቅ ብልጭ ሲል ፍጥረት ሁሉ ጥጉን ይዞ፤ ወፍ አራዊቱ ወደ መመሸጊያው ከቶ፤ ጉርምራሙ ልብን በፍርሀት አስደንግጦ የት ልግባ የሚያሰኝ። ነፋሱ የሰፈሩን ሳር ቅጠል ተሸክሞ፤ በመንገድ ላይ ያገኘውን ሁሉ ጠራርጎ የመጣ ቀን አይጣል የሚያሰኝ። በዚህ ዕለት የሚመጣን ዝናብ የሚመስል ናፍቆት እና ፍቅር ነው አበበ ተካን የገጠመው።
“እንደ ሰኔ ሰማይ እያጉረመረመ
ናፍቆቷ እንደ መብረቅ እያስገመገመ
ቀረች ብሎ ልቤ በስጋት ከረመ”
አንዳንድ ቀን አለ ዝናብ ሰፈር መንደሩን አተራምሶ፣ ግርግር ፈጥሮ፣ በመብረቅ እና ወጀብ አራግቦ ውኃ ጠብ ሳይል ተመልሶ የሚሰወር። አበበ ተካም የፈራው ይህንን ነው። ናፍቆቷ መጣሁ ብሎ እንዳይቀርበት። ቢጠብቀው የለም። ማጉረምረም እና ማስገምገም ብቻ። አበበ በሐሳቡ “ከአድማስ ተፈንጥቃ ስትገባ በበሬ፤ ቤት ለእንቦሳ ስትል ታየችኝ ጀንበሬ” ይላል። ፍቅሩ ግን አልመጣችም፤ቅዠት ነው። ምኞት ነው::
አስቴር አወቀ “እትቱ በረደኝ ቀዘቀዘኝሳ
ፍቅርዬን በማሰብ ከእንቅልፌ ስነሳ
ስሜቴን ቀዝቅዞ አካሌን በርዶታል
መውደድህን ቢያገኝ በአንተ ይሞቃል” ስትል ፍቅር ቅዝቃዜ ውስጥ እንደከተታት ታዜማለች። በሌላ ሙዚቃዋ እንዲሁ ብርዱ አልተስማማኝም ትላለች። በዚህ ሙዚቃ አስቴር በጥር ወር ባለው ብርድ ነው የተቸገረችው።
“አልቻልሁትም ወሩን ለመጨረስ
የኔ አካላት ሰውነቴ ድረስ፤
ብርዱ አልተስማማኝም የጥምቀቱ
ካንተው ቀርቷል የጎኔ ሙቀቱ”
ኬኔዲ መንገሻ ደግሞ ቅምጥል ነሽ በሚል ሙዚቃው እንዲሁ ፍቅር፣ ብርድ፣ክረምት፣ ቅዝቃዜው ያላቸውን መስተጋብር በሚከተለው መልኩ ገልጾት እናስተውላለን። ክረምት ከግንቦት ወደ ሐምሌ እና ነሐሴ ሲሸጋገር ፍቅሩም አብሮ ሲጨምርበት፣ ቤቱ የበለጠ ጸጥታ እና ሰው ማጣት ሲወረው እንመለከታለን።
“እኔማ ባንቺ ሳዘጋግም
ክረምቱም አብሮ ሲያገመግም፤
ግንቦት ሰኔን ሲከተለው
ሙላት ዝናብን ሲቀበለው፤
ብርድ በረታ ውሽንፍሩ
ቤት ሰው አይለምደው ጓዳ በሩ”
በቴዎድሮስ ታደሰ “የዓባይ ማዶ” የምናስተውለው ፍቅረኛን ዛሬ ነገ ትመጣለች በሚል በጉጉት መጠበቅን ነው። አካሏን ናፍቆት ሊያያት ቢፈልግም፤ባለችበት ቢመላለስም አልሆነለትም። ‘የእሱ ፍቅረኛ ናት’ በሚል መታማቱ ባይቀርለትም ስም ብቻ ተርፎት ሳያገኛት ቀርቷል። ነይ አብሬሽ ልክረም ይላል። የዓባይ ማዶን ልጅ አፍቅሮ ወራትን በፍቅሯ ተይዞ ጠብቋታል።
“በሰኔም፣ በሐምሌም፣ በነሀሴም አልሆነም
ነይ በመስከረም እቴ አብሬሽ ልክረም”
ክረምት በኤፍሬም ታምሩ ሙዚቃ ውስጥ ነፍስ ዘርቶ፤ እንደሰው ነገሮችን ሲከውን ይታየኛል። ቀንሲጥል ብሎታል ርዕሱን። ሙዚቃው ውስጥ እውነትም ብርድ እና ቅዝቃዜ አለ። ብቻውን ቤት ውስጥ ኩርምት ብሎ ተቀምጦ ፍቅረኛውን በመጠበቅ፤ በመናፈቅ የሚብሰለሰል አንድ ወንድ ይታየኛል። ናፍቆት እና ፍቅር በብቸኝነት ውስጥ የበለጠ ጉልበት ያገኛል። ከሰው ጋር ሲሆኑ፤ ሲጨዋወቱ እና ሲያወጉ አዕምሮ ከናፍቆት እስራት ለመላቀቅ ትንሽ ፋታ ያገኛል። ቀን ከሰው ጋር ሲጫዎቱ ቀለል ይላል። ኤፍሬም ብቻውን በቀዝቃዛ ቤት ውስጥ ሆኖ፤ሌሊት የሚያብሰለስላትን በቀን መርሳት ነበረበት። ግን አልሆነም ቀኑ በዝናብ እና ብርድ ሌሊት ሆኖበታል።
“አስታውሸሻለሁ ትናንትናም ዛሬ
አነሳሳሻለሁ ትናንትናም ዛሬ፤
ጭብጥ ኩርምት አልሁኝ ናፍቆትሽን አዝዬ
ማለፉ አይቀር ብዬ፤
ቀኑ እንደመጨለም በእኔ ላይ አለብኝ
አድማስ ዳመናውን በእኔ ላይ ጣለብኝ
ደጉን ቀን ያምጣልኝ
እንኳን ጊዜው መሽቶ ሌቱም አይነጋልኝ
ብራ ባረገልኝ
እንኳን ቀን ታክሎ ሌቱም አይነጋልኝ”
ኤፍሬም ቀዝቃዛ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ሰማዩ ቀኑም ሙሉ ሲያለቅስ ውሎ ደግሞ ለማታ ዝናብ እና ብርድ ደግሷል ይላል። ገና በአመሻሽ ጉሙ ሲበረታ፤ መኝታው ሲቀዘቅዝ፤ በትዝታዋ ሲንሰፈሰፍ፤ ናፍቆቷ መንፈሱን በጦር ሲወጋው ዘፈኑ ውስጥ ይታያል። ኤፍሬም ዕለቱን አይቶ ታዝቦታል።እንደሰው እየየው ሲልም አድምጦታል።
ጀንበር ገና በንጋቱ በጉም መሸፈኗ፤ አየሩም ቀዝቅዞ ዳመናውን ይዞ ዙሪያው ማጎምጎሙ፤ በማለዳ አካፍቶ በቀትርም በርትቶ ዶፉን ዝናብ መጣሉ፤ መድረሻ እንደሌለው ሆደባሻ እየየ ሲል መዋሉ ያለአንዳች ምክንያት አይደለም። ቀኑ ጉሙን አቀርዝዞ ያካፋል። ሰማዩ ሰው ይመስል በመከፋት እህ ይላል።
“ዓይን አይለይም እንጂ በሌ’ት በጨለማ
እንዲያው በረዶ ነው ቀን የጣለው’ማ
የሚያዳምነው፤ የሚያጨግገው
ኧረ ነይ ናፍቆትሽ ነው ቀኑን ያጨለመው”
ይልና የዚህ ሁሉ ቁዘማ ምክንያት እሷ መሆኗን፤ ናፍቆቷን ለመቻል መገደዱን፤ የትዝታዋ ሰቀቀን ጦር ግን እየገደለው መሆኑን ይቀጥላል። ቀጥሎ ባሉት ግጥሞች ኤፍሬም የዝናቡን እና የእሱን ሁኔታ ስዕል በሚመስል የግጥም ስንኞች ይነግረናል። ቁልጭ አድርጎም እንድናይ ይጋብዘናል።
“ወሸባው ሲጋረፍ ሽውታው
ደጃፉን ወጨፎ ሲመታው
ብርዱን ሲያሳልፈው ሰው በመኝታው
የ’ኔም ቤት ተብሎ ቀዝቃዛው
ጎኔን ጣል አድርጌው ካጎዛው
ይረግፋል ልቤ ላይ የኔ አሳብ ጤዛው”
የክረምት አጎዛ ቅዝቃዜ ምንኛ ሰውነቱን በረዶ ሆኖ ያሰቅቀው ይሆን? ሰው ሁሉ በየቤቱ አስቸጋሪውን ክረምት ሲያልፈው እሱ በረዶ ቤቱ ውስጥ በናፍቆት እየተሰቃዬ አለ።
“ትላልቅ አዳራሽ አላሰብሁም ጭራሽ
በ’ውኔም አላለምኩኝ
መች ጠበበኝ ፍቅር ይበቃኛል ልብሽ
እዚያው ከከረምኩኝ
እንግዲህ እንደ ሌላው አካሌ
እንዲደላው ካሰብሽልኝ ለእኔ
ኩርማን አንጀት ስጪኝ ከሆድሽ
አኑሪኝ ስፍራ አይፈጅም ጎኔ”
በማለት በልብሽ ማህደር ውስጥ አኑሪኝ፤ ራርተሽልኝ ከጭንቅ ልውጣበት ብሎ ይጠይቃል። እሷ ግን በዚህ የተስማማች አትመስልም። እሱም ችግሩን መዘርዘሩን ይቀጥላል።
“ያሳር ምድር ሆኖ ሲያቀረዝዝ ጤዛ
ያዘለው ጠብ ሲል ሲረግፍ እንደዋዛ
ያን ጊዜ ሲያራርቅ ሰው ከሰው ነጥሎ
ብራ አልሆን እያለ ሲያስጨንቅ ቀን ጥሎ”
እያለ የቀን ክፋት ሰውን ከሰው ከነጠለው ወዲያ ትርፉ ድካም መሆኑን በመከፋት ይገልጻል። ቀን ሲጥል እንዲህ ያለ መከፋት እና አስጠሊታ አጋጣሚ አለ፤ ለካ እንዲህ አለያይቶ ያስቀራል ቀን ሲጥል ብሎ እንጉርጉሮውን ይቋጫል። ኤፍሬም ቀን ሲጥል በሚለው ሙዚቃው ውስጥ ቀኑን ሙሉ ዝናብ ሲጥል ቤት ፍቅረኛውን የሚናፍቅን ወጣት ሰቀቀን አሳይቶናል። ዶፍ፣ ጉሙ፣ ዝናብ፣ ቅዝቃዜ እና ጠፈጠፍ የአፍቃሪውን ልብ በናፍቆት አብሰልስለውት ውለዋል። በፍቅር እና ዝናብ መስሎ ይዞን ስምንት ደቂቃ ከተጓዘ በኋላ፤ በመጨረሻም ጊዜ ሲጥል የሚፈጠርን አስቀያሚ ብሶት ይነግረናል። ሰው በጊዜ ዳኝነት የሚደርስበትን በደል ልብ እንድንል ያደርገናል።
ሐተታ ክረምቴን በዚህ አበቃሁ።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም