በምድራችን ለሚከሰተው የማያባራ ግጭት መንስኤው የፖለቲካ ልዩነት፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ኢፍትሐዊነት፣ የዘር እና የሃይማኖት ልዩነት እንዲሁም ድህነት እንደሆነ ሪሰርች ጌት ዶት ኮም (Research Gate.com) የተባለ የጥናት ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በሰው ልጆች ላይ መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥፋቶች ያስከተሉ ግጭቶች ተከስተዋል። በሩዋንዳ፣ በናይጀሪያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በሶማሊያ እና በሀገራችን በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል ትግራይን፣ አማራን እና አፋርን ያካለለው ጦርነት ከፍተኛ የሕይወት እና የንብረት ጥፋት ካደረሱት መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።
በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት የተቀሰቀሱ ግጭቶች ከባድ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳቶችን አስከትለዋል። በዚህም ሕፃናት ያለ ወላጅ፣ አዛውንቶች ያለ ጧሪ ቀባሪ ቀርተዋል፤ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ንብረት ወድሟል። ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ በአማራ ክልል የተፈጠረው በትጥቅ የታገዘ ግጭት አሁንም መፍትሔ አልተገኘለትም::
በአማራ ክልል አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀረው በትጥቅ የታገዘ ግጭት አድማሱን አስፍቶ ክልሉን ብሎም ኢትዮጵያን ለከፋ ጉዳት ሳይዳርግ በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም ሰላም ሊመጣ አልቻለም፤ እንዲያውም እየተባባሰ ቀጥሏል፡፡
በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች የቀጠለው ግጭት የምግብ እጥረት አስከትሏል። በየጊዜው መጓጓዣዎች በመቋረጣቸው የንግድ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ለአቅርቦት እጥረት እና ለዋጋ ንረት ምክንያት ሆኗል።
ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሠረት የሆነው የግብርናውን ዘርፍም በእጅጉ ፈትኖታል። ይህም እየናረ ለመጣው የኑሮ ውድነት ሌላው ምክንያት ነው። አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀረው የአማራ ክልል የእርስ በእርስ ግጭት እስካሁን ከ12 እስከ 13 ቢሊዮን የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡ እገታ ተስፋፍቷል፤ ዜጎች ያለከልካይ በጠራራ ጸሃይ ተዘርፈዋል፤ ተገድለዋል፤ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተስተጓጉለዋል፡፡ ህሙማን እና ነፍሰጡር እናቶች ህክምና እና መድኃኒት ባለማግኘታቸው ህይወታቸው አልፏል ።
ግጭቱ በክልሉ አብዛኛዎቹ ቦታዎች የመማር ማስተማሩን ሂደትም አስተጓጉሏል። በክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ መሰረት በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ከሦስት ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡
በቅርቡ በተሰጠው የስምንተኛ እና የስድስተኛ ክልል አቀፍ ፈተና ተማሪዎቻቸውን ያስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም ዝቅተኛ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጸጋዬ እንግዳወርቅ እንዳሉትም በዞኑ 245 ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን የትምህርት መሠረተ ልማቶችም ጉዳት እና ውድመት ገጥሟቸዋል፡፡
የመማር ማስተማር ሥራ በተካሄደባቸው ትምህርት ቤቶችም ቢሆን ሕጻናት በእርስ በእርስ ግጭቱ ምክንያት በቂ ዕውቀት ማግኘት አለመቻላቸውን የቢሮው መረጃ ያስረዳል፡፡
ታዲያ የተፈጠረውን የእርስ በእርስ ግጭት እልባት ለመስጠት በቅርቡ የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ ሰላም ለማስፈን ይረዳሉ የተባሉ ተከታታይ ኮንፈረንሶች በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሐሳብ ተካሂዷል፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ወሎ ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እና በምስራቅ ጎጃም ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሰላም ኮንፈረንሶች ተደርገዋል፡፡ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን የሚጠይቁ ድምፆች በጉልህ ተስተጋብተዋል፡፡ ክልሉን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት በቸኛው መንገድ ውይይት እና ድርድር ነውም ተብሏል።
በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሰላም ኮንፈረንስ በመሐል ሜዳ ተካሂዷል። በኮንፈረንሱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአርሶ አደር ተወካዮች፣ የቀበሌ መሪዎች፣ የእድር መሪዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። የሰላም ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የሰላምን ጉዳት እና ጥቅም የተረዳነው ስናጣው ነው ብለዋል፡፡
ጫካ የገቡት ኀይሎች የእኛው ልጆች እና የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ስለሆኑ መመለስም ሆነ፤ ቀርበን ማወያየት የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች በመኖራቸው ልንጠቀምባቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የተወሰኑ አካላት ብቻ አይደሉም ያሉት ተወያዮቹ በተደራጀ መንገድ በውስጥ ያለውን ጥርጣሬ በመተው ጥያቄዎችን ለመንግሥት ማቅረብ እና ምላሽ ማግኘት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡ ሰላም እንዲሰፍን እና የልማት ሥራዎች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲሠሩ የበኩላቸውን እንደሚወጡም የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡
የመሐል ሜዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን እንደገለጸው በውይይቱ መጨረሻ ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማዘጋጀት፣ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ እና 11 አባላት ያሉት የሰላም መማክርት (ካውንስል) በማቋቋም ውይይታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ”ሠላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሠላም” በሚል መሪ ሐሳብ በደቡብ ጎንደር ዞን ሁሉም ወረዳዎች ሕዝባዊ የሠላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። በከተማው የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሰላም ኮንፈረንሱ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
በክልል ደረጃም ሆነ በከተማ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ወጥ የሆነ ለሕዝብ የሚጠቅም አመለካከት በመያዝ የከተማውን ብሎም የክልሉን ሕዝብ በሁለንተናዊ መንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ ኮንፈረንሱ ጠቀሜታው የጎላ ነውም ተብሏል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ ተከስቶ የነበረውን የሰላም እጦት ወደነበረበት ለመመለስ ምክክር ተደርጓል። በኮንፈረንሱ በከተማው የሚኖሩ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ተሳትፈዋል። ተሳታፊዎቹ ሰላምን ለማስፈን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ እና እርስ በእርስ በመገዳደል ሰላም እንደማይረጋገጥ ገልጸዋል። የአካባቢውን እና የአማራ ክልል ጥያቄዎችን በውይይት እና በምክክር ለመፍታት የታጠቁ ወገኖች ወደ ንግግር እንዲመጡም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳም የመንግሥት ሠራተኞች የሰላም ኮንፍረንስ ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ወረዳውን ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ የመንግሥት ሠራተኛው ከፍተኛውን ድርሻ መውሰድ እንደሚገባ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
የኅብረተሰቡ ጥያቄዎች እንዲፈቱ፣ ግጭት እንዲቆም፣ ሰላም እንዲመጣ፣ የኑሮ ውድነት እንዲስተካከል እንዲሁም ሌሎች የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
አሁን ባለው የኑሮ ውድነት የመንግሥት ሠራተኛው በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ በመሆኑ መንግሥት ይህን ችግር መሠረት ያደረገ መፍትሄ እንዲያመጣ መጠየቃቸውን ከዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ዓለማችን ላይ የተከሰቱ አብዛኞቹ ግጭቶች እና አለመግባባቶች መቋጫቸው ንግግር እና ድርድር ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ሪሰረች ጌት ዶት ኮም (Research Gate.com) የተባለ የጥናት መረጃ ያመለክታሉ። ግጭቶችን በሰላማዊ ንግግር እና ድርድር መፍታት ዘለቄታ ያለው ሰላም ለማግኝት ያግዛል። በአማራ ክልል ይህ ሳይሆን በመቅረቱ በሰላማዊ ንግግር መፍታት የሚችሉ ቅራኔዎች ለንፁሀን እልቂት እና መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል። አሁን ላይ ግን ችግሩን በንግግር እና በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከዚህ በፊት ሩዋንዳን እና ጋናን የመሳሰሉ ሀገራት ደግሞ የሰላም ምክር ቤት (ካውንስል) በማቋቋም ችግሮቻቸውን መፍታታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ መቶ ቀናት የዘለቀው የሩዋንዳ የእርስ በእርስ ጦርነት በ20ኛው ክፍለ ዘመን የታየ እጅግ አሰቃቂ ሰብዓዊ ጥፋት ያደረሰ እልቂት ነው፡፡
በመቶ ሺዎች የሚቆጥሩት ንጹሀን ዜጎች ሞተዋል፣ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች ተሰደዋል፡፡ በመጨረሻም እ.አ.አ በ2001 በሀገር አቀፍ ደረጃ የአንድነት እና የእርቅ ምክክር በማድረግ ሰላም አውርደዋል፡፡ አሁን ላይ ሩዋንዳ በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ ሆናለች፡፡
ለዐሥርት ዓመታት ያህል በጋና የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነትም የተቋጨው በምክክር መሆኑን የዘ አፍሪካ ሪፖርት መረጃ ያሳያል፡፡ ግጭቱን ለመቆጣጠር እና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በ2011 እ.አ.አ የሰላም ካውንስል በማቋቋም ወደ ሥራ መግባታቸውን የሪሰርች ጌት መረጃ ያስነብባል፡፡
የሰላም ምክር ቤት (ካውንስሉ) ግጭቱን ለማስቆም እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሽምግልና እና ሌሎች የሀገር በቀል የግጭት አፈታት እና የሰላም ግንባታ ዘዴዎችን አመቻችቷል። የብዝኃነት፣ የመተማመን፣ የመቻቻል፣ የድርድር፣ የውይይት እና የእርቅ እሴቶችን በመጠቀም ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል፡፡ አሁን ላይ ጋና ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባት እና የተረጋጋች ሀገር መሆኗን የዘ አፍሪካ ሪፖርት መረጃ ያመለክታል።
ሰላም የግለሰብ፣ የአርሶ አደሩ እና የአርብቶ አደሩ፣ የተማሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የባለሃቶች፣ የአንድ ክልል ሕዝብ፣ የመንግሥት ኃይሎች ወይም ጭካ የገቡ የፋኖ አባላት የብቻ ጉዳይ አለመሆኑን የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል መግለጹ የሚታወስ ነው። የሰላም ካውንስሉ ሰላም የሁሉም ከሁሉም በመሆኑ በየደረጃው ጥሪ የተደረገላችው አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፏል::“የሰላም ጥሪው በአዎንታዊ መልኩ ታይቶ የሀገራችንን ሰላም በጋራ እናምጣ፤ የወንድማማቾች መገዳደል ይብቃ” በማለት የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ጥሪውን ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም