ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? ልጆች በዚህ ጽሑፍ ስለ ቀይ ባሕር የተወሰኑ ዕውነታዎችን ልናካፍላችሁ ወደናል:: መልካም ንባብ!
ቀይ ባሕር ከግብጽ የስዊዝ ቦይ እስከ ባብ ኤል መንደብ 1,930 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ጠባብ የውኃ አካል ነው። ቀይ ባሕር በእስያ እና በአውሮፓ መካከል ሸቀጥ የሚያጓጉዙ ግዙፍ መርከቦች መተላለፊያ በመሆኑ የዓለም ኃያላንን ትኩረት ይስባል:: ከዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ12 እስከ 15 በመቶው እንዲሁም ከኮንቴይነር ጭነቶች መካከል 30 በመቶውን በየዓመቱ የሚያስተናግደው ቀይ ባሕር፣ በእስያ እና በአውሮፓ አህጉራት መካከል የሚደረግ የመርከብ ጉዞን ወጪ እና ጊዜን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እና የኮንቴይነር ጭነቶች የሚያልፍበት በመሆኑ የዓለማችን ንግድ እና የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ኬላ በመባል ይታወቃል። በእስያ፣ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ መካከል በቀይ ባሕር በኩል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ምርቶች በዓመት አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጡ እንደሆነ ይታመናል። ከእስያ የተነሳ አንድ የጭነት መርከብ በሱዩስ ካናል (የግብጽ መተላለፊያ ሰው ሰራሽ የባሕር ላይ መንገድ) በኩል በአጭሩ አውሮፓ ለመድረስ ቀይ ባሕርን አቋርጦ ሜዲትራኒያን መድረስ አለበት። ካልሆነ ግን በደቡብ አፍሪካ ጫፍ በኩል ዞሮ መጓዝ ይጠበቅበታል።
በደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ይህ ጉዞ ደግሞ በቀይ ባሕር በኩል ካለው አቋራጭ መንገድ የሰባት ሺህ ኪሎ ሜትሮች ጭማሪ መንገድ አለው። በቀን ሲሰላ ደግሞ ከስምነት አስከ 12 ተጨማሪ ቀናት የባሕር ላይ ጉዞ ስለሚጠይቅ ወጪው ከፍ ይላል።
ቀይ ባሕር የሕንድ ውቅያኖስን እና ሜዲትራኒያን ባሕርን በማገናኘት በተለይም በዓለም ዙሪያ ተፈላጊ የሆነውን ነዳጅ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ለማጓጓዝ አጭር መንገድ በመሆኑ በዓለም ንግድ እና ፖለቲካ ላይ ወሳኝ ቦታ አለው። በዚህም የተነሳ ባሕሩን ከሚጎራበቱት ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኤርትራ፣ የመን፣ ጂቡቲ እና ሶማሊያ በተጨማሪ ከአካባቢው ርቀው በሌሎች አህጉራት የሚገኙ በርካታ አገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አካባቢ ይገኛሉ። እንዲሁም ከአውስትራሊያ፣ ከጃፓን፣ ከቻይና፣ ከሕንድ እና ከሌሎችም ሀገራት የሚገኙ ወሳኝ የቴክኖሎጂ ምርቶች እና ሸቀጦችን የጫኑ ግዙፍ መርከቦች የሚያቋርጡት ወሳኝ የባሕር መስመር ነው።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የዓለማችንን አንድ ጫፍ ከሌላኛው ጋር በሰከንዶች ውስጥ ለማገናኘት እና መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችሉ የመረጃ ማስተላለፊያ ግዙፍ ገመዶች በቀይ ባሕር ወለል ላይ ተዘርግተው ይገኛሉ።
ተረት
የበቅሎዋ መንገድ
እጅግ አድርገው ቀልድ ወዳጅ የነበሩ አንድ ሀብታም ጌታ ነበሩ:: እንደ ጌታው ቀልድ ወዳጅ የሆነ አንድ አጋፋሪም ነበራቸው:: አንድ ቀን ጌታው አንዲት ያልተገራች በቅሎ ይገዛሉ:: በቅሎይቱ ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ናት:: ስለዚህም ጌትዬው አጋፋሪውን ይጠሩና “እቺን በቅሎ ጫንና መንገድ አሳያት” ብለው አዘዙት:: አጋፋሪውም ትዕዛዙን ተቀብሎ፣ በቅሎዋን ጭኖ፣ ተቀምጦባት መጭ አለ:: አንድ መንታ መንገድ ላይ ሲደርስ፣ ዱብ አለና በቅሎዋን፤
“በቅሎ ሆይ፤ ያውልሽ እንግዲህ:: የሸዋ መንገድ ይህ ነው:: የጎጃም መንገድ ይህ ነው:: የጎንደርም መንገድ ይህ ነው:: የትግሬም መንገድ ይህ ነው:: ጌታሽ መንገድ አሳያት ብለውኛልና የወደድሺውን መንገድ ይዘሽ ሂጂ” ብሎ እንደተጫነች ለቀቃትና እሱ ወደ ቅልውጡ ሄዶ አምሽቶ ወደ ጌታው ተመለሰ:: ጌታውም፡- “ለበቅሎዋ መንገድ አሳየሃት? ሲሉ ጠየቁት::
“አዎን ጌታዬ የአራቱንም ሀገር መንገድ አሳይቼአት ሳበቃ የወደድሺውን ያዥና ሂጅ ብዬ ለቀቅኋት ብሎ መለሰ:: ጌትየው በጣም ተናደዱ:: በነጋታው “ተነሱ ፍለጋ እንሂድ” ብለው አሽከሮቻቸውን ሁሉ አስከትለው ፍለጋ ተሰማሩ:: በቅሎዋ ድራሿ ጠፋ:: በመጨረሻ ያ የጣላት አጋፋሪ ራሱ መልሶ አገኛት:: ዳሩ ግን ገሚስ ጎንዋን ጅብ ተጋብዟት ነው ያገኛት:: አጋፋሪው በሌላ አቅጣጫ ወደሄዱት ወደ ጌታው ዘንድ አመራ::
ጌትየው፡- “እህስ ምንም ፍንጭ የለም?” አሉና ጠየቁት ገና ሲያዩት::
“እንዴት ፍንጭ አይኖርም፤ አለ እንጂ ጌታዬ! ግማሿን በቅሎ አግኝቻታለሁ:: ግማሿን ለጅብ አካፍላዋለች” ሲል መለሰላቸው::
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ
ይሞክሩ
ማንም ባመቸው ጊዜ እና ቦታ ለማንም የማይነግረኝ የተወደድሁ ነኝ?
አንገት ኖሮኝ ያለጭንቅላት የተፈጠርኩ ማነኝ?
በአማርኛ መዝገበ ቃላት ስህተት ሆኖ የተፃፈው ቃል ማነው?
መልስ
ራሱ “ስህተት” ነው
ምስጢር
ጠርሙስ
ነገር በምሳሌ
ለመስማት የፈጠንህ፣ ለመናገር የዘገየህ ሁን
ብዙ ከመናገር ጥቂት ማዳመጥ የበለጠ ነው ለማለት ነው::
መርፌ ውጦ ማረሻ መትፋት
የማይሆን እና የማይታመን ነገርን ለመግለፅ የምንጠቀመው ነው::
ለራሱ ጥላ፣ ለእግሩ ከለላ አለኝታ፣ ጋሻና መከታ፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


