ሁለት ሜትር ከሃያ ስድስት ሴንቲሜትር የምትረዝመው የ25 ዓመቷ ቻይናዊት በዓመት አስር ሴንቲሜትር በሚጨምረው ቁመቷ በየጊዜው ለጫማና ልብስ ወጪ ከመዳረጓ ባሻገር አጣማጅ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት መቸገሯን ኦዲት ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::
ከጥቂት ወራት በፊት ወጣቷ ታኦማይ ራሷ አጭር የቪዲዮ ምስል አቀናብራ በማህበራዊ ድረ ገፆች አስተዋውቃ ነበር:: ወጣቷ የለቀቀችው ምስል በአጭር ጊዜ በርካታ ተመልካች አግኝቷል:: ወጣቷ ይህን ያደረገችው እናቷ ባቀረበችላት ሀሳብ ነበር::
ወጣቷ ገና ትምህርት ቤት ሳለች ከእኩዮቿ ጋር ስትቀመጥ የታጠፈ ጉልበቷ ከጠረጴዛው ይበልጣል:: አልጋዋም ስትተኛ ይጠባታል፤ የተዘጋጁ (readymade) ልብስ ለማግኘት ትቸገራለች:: በአውቶቡስ ስትጓዝም “ወደ ኋላ ወንበር ሂጂ” በሚል መልእክት መጨረሻ ትቀመጣለች:: በዚህ ሁሉ ችግር ትማረር እንደነበር ነው እውነታውን ያስረዳችው::
ወጣቷ ታኦማይ ከእናቷ ጋር በመመካከር የቪዲዮ ምስል በማህበራዊ ድረ ገጽ ከለቀቀችበት ማግስት ጀምሮ በሰፈሯ የሚኖሩ በርካታ ወንዶች ይከተሏት፣ ያወክቧትም ነበር::
ለዚህ ሁሉ መነሻ እውነታው ግን ታኦማያ እንደፈለገችው እናቷ በዘየዱላት መላም ችግሯን የሚፈታ አልነበረም:: ተሰብሳቢዎቹ፣ የሚከቧት ወንዶች በሙሉ ቁመቷን ለማረጋገጥ እና አብራቸው ፎቶ እንድትነሳ የሚጠይቁ ብቻ እንደነበሩ ነው ድረ ገጹ ያስነበበው::
“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ…” ይሏል ይህ ነው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም