ቁንጅናን በ80 ዓመት

0
148

የ80 ዓመቷ ቾይ ሶን ህዋ በቅርቡ በደቡብ ኮሪያ በተካሄደ የወይዘሪት ዩኒቨርስ የቁንጅና ውድድር ሃገራቸውን ለመወከል ለመጨረሻ ማጣሪያ መድረሳቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል፡፡

በሚቀጥለው ወር 81ኛ ዓመታቸውን የሚይዙት የሶስት ልጆች አያት የሆኑት ወይዘሮዋ ሃገራቸውን ወክለው በቁንጅና ውድድር የመሳተፍ ህልም እንዳልነበራቸው ነው የተናገሩት፡፡ ሆኖም ቀደም ብሎ በነበረው የውድድር የምርጫ ተሣታፊነት ህግ ላይ የተደረገው ለውጥ ለመወዳደር እንዳነሳሳቸው ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ብሎ በቁንጅና ውድድር ለመካፈል እድሜያቸው በ18 እና 28 ዓመት መካከል መሆንን ግድ ይል ነበር፡፡ በሚስ ዩኒቨርስ ለመካፈል ህጉ አካታች መሆን እንደሚኖርበት ጠያቂዎች እየተበራከቱ ጫና በማሳደራቸውም የእድሜ ገደቡ መነሳት ችሏል፡፡

ከእድሜው ገደብ ባሻገርም ነፍሰጡር እናቶች፣ ልጆች ያሏቸው ባለትዳሮችም እንዲወዳደሩ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ይህንን መሠረት አድርገውም ቾይ ጤናማነት እና ጥንካሬን እስከ እርጅና መጠበቅ እንደሚቻል ለማሳየት እና ሌሎችን ለማነሳሳት በውድድሩ መካፈላቸውን አስረድተዋል፡፡

የ80 ዓመቷ የቁንጅና ውድድር ተካፋይ ቀደም ባሉ ዓመታት በሃገራቸው ደቡብ ኮሪያ እንደ “ሃርፐር ባዛር “እና “ኢሌ” በመሳሰሉ መጽሄቶች እንዲሁም የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ምርቶችን አስተዋዋቂ ሞዴል ሆነው ሰርተዋል፡፡

በጐልማሳነት የነበራቸውን አስተሳሰብ እና እምነት የለወጠው ቅፅበት የተከሰተው ግን በ72 ዓመታቻው ነበር፡፡ በነርስነት በሚያገለግሉበት ሆስፒታል ከሚንከባከቧቸው ታካሚዎች አንዱ የሞዴሊንግ ሞያን እንዲሞክሩ የለገሳቸውን ምክር መቼም ቢሆን እንደማይረሱት ነው የተናገሩት፡፡

እንደ አዛውንቷ አገላለጽ ታካሚያቸው የሞዴሊንግ ሞያን እንዲሞክሩ ሲነገራቸው የማይሆን  ሃሳብ መስሏቸው ነበር፡፡ ሆኖም ኃላ ላይ ቀደም ብሎ በውስጣቸው የነበረውን ምኞት እንደቀሰቀስባቸው ነው ያብራሩት፡፡

በውስጣቸው የነበረውን ህልም ቀስቅሶ በውስጣቸው ያቀጣጠለውን ምክር ሰንቀውም የተለያዩ ልብሶችን በመልበስ ፎቶግራፍ እየተነሱ ተመለከቱት በቃ “መሞከር አለብኝ!” አሉ፡፡

አዛውንቷ ለሲኤን ኤን ዜና ማሰራጫ እንደተናገሩት የውስጣቸውን ጥሪ አድምጠው ምላሽ ለመስጠት ወደ ሙያው መግባታቸውን እና በስኬታማነት ለማጠናቀቅ ጠንክረው መቀጠላቸውን ነው የገለጹት።

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here