ቁጥሮች ምን ይናገራሉ?

0
150

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው በትጥቅ የታገዘ ግጭት አንድ ዓመቱን ሊደፍን እየተንደረደረ ባለበት ወቅት ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችም ተዘግተው ከመማር ማስተማር ውጪ ሆነው መክረማቸውን “ትምህርት ለትውልድ” የተሰኘ ክልላዊ የትምህርት ንቅናቄ በተካሄደበት ወቅት ተገልጿል፡፡ በዚህም ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ ጫና ካሳደረባቸው አካባቢዎች መካከል አንደኛው የምስራቅ ጎጃም ዞን ነው፡፡ በዞኑ 996 የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ በ2016 ዓ.ም በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ለማስተማር ዕቅድ ተይዞ የነበረው 539 ሺህ 996 ተማሪዎችን ነው፡፡

በዓመቱ የመማር ማስተማር ሥራቸውን ያስቀጠሉት 32 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ ሲሆኑ በትምህርት ላይ የተገኙት ተማሪዎች ቁጥርም ከ13 ሺህ የበለጠ አይደለም፡፡

በአሁኑ ወቅት የዓመቱ ትምህርት ተጠናቆ ፈተናዎች እየተሰጡ ነው፡፡ የስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው መፈተን ከነበረባቸው 41 ሺህ 944 ተማሪዎች ውስጥ ፈተናውን መውሰድ ይችላሉ የተባሉት  506 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ በ12 ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩት እነዚህ ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ የተባሉት በሁለት ዙር ነው፡፡ 779 ትምህርት ቤቶች በጸጥታው ችግር ምክንያት ተማሪዎችን ተቀብለው ባለማስተማራቸው በዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን ፈተና አይሰጡም፡፡

የምስራቅ ጎጃም ዞን በ2016 ዓ.ም በ593 ትምህርት ቤቶች ደግሞ 38 ሺህ 203 የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈትናሉ የሚል ሐሳብ ነበረ፡፡ ይሁን እንጂ በዓመቱ መጨረሻ በተጨባጭ ማስፈተን የቻለው በ10 ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 431 ተማሪዎች ብቻ ነው፡፡ በ583 ትምህርት ቤቶች፣ 37 ሺህ 772 ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው መክረማቸውን ተከትሎ በዓመቱ መጨረሻ የተሰጠውን ፈተና አልወሰዱም፡፡

በዞኑ ከሚገኙ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 65 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚያስፈትኑ ዕጩ የትምህርት ተቋማት ነበሩ፡፡ በእነዚህም ትምህርት ቤቶች 19 ሺህ 657 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የዓመቱን ትምህርት አጠናቀው  የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ይወስዳሉ ተብሎ ቢታቀድም 60 ትምህርት ቤቶች እንደማያስፈትኑ፣ 19 ሺህ 80 ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው መክረማቸውን ተከትሎ ፈተናውን እንደማይወስዱ የዞኑ ትምህርት መምሪያ መረጃ ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ እንደ ክልል የተቀሰቀሰው በትጥቅ የታገዘ ግጭት በዞኑ የትምህርት ተቋማት ላይ ያደረሰው ጉዳት ምን ይመስላል? የሚለውም ሊመለስ ይገባል፡፡ የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ከትምህርት መምሪያው አገኘሁት ብሎ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያሰፈረው መረጃ እንደሚያሳየው ግጭቱ ከ407 በላይ ትምህርት ቤቶች እንዲወድሙ እና ለመማር ማስተማር ምቹ እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡ በትምህርት ተቋማቱ በሚገኙ አጠቃላይ ሐብት እና ንብረት የደረሰው የጉዳት መጠንም ከ290 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡

የጸጥታ ችግሩ በሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ሥር የሚገኙ የትምህርት ተቋማት፣ ተማሪዎች እና ሠራተኞች ላይ ያሳደረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ በዞን 503 ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ውጪ ሆነው ከርመዋል፡፡ ይህም 400 ሺህ 987 ተማሪዎች ከቤታቸው እንዲከርሙ አድርጓል፤ ከአሥር ሺህ በላይ መምህራን እና ሠራተኞች ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያጋራው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው በዓመቱ በ115 ትምህርት ቤቶች 38 ሺህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ገብተው ነበረ፡፡ ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ በተፈጠሩ ግጭቶች ባሕር ዳር ከተማ ከሚገኘው ፊታውራሪ ሐብተ ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውጪ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሥራ አቁመዋል፡፡

የተፈጠረው የሰላም ችግር በባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር በሚገኙ የትምህርት ተቋማት እና ተማሪዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩም ተመላክቷል፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ ከሚገኙ ከመቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁለት የሁለተኛ ደረጃ እና 22 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ውጪ መሆናቸውን ያስታወቁት የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ኀይለማርያም እሸቴ ናቸው፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቀጣይ የትምህርት ሥራዎች ዙሪያ ከሚዲያ  መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ምክክር አካሂዷል። የቢሮዉ ምክትል ኃላፊ መኳንንት አደመ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ አንድ ዓመት ሊያስቆጥር ወራት በቀሩት የሰላም እጦት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ምንም በማያውቁት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፡፡ የትምህርት ተቋማትን የፖለቲካ ማዕከል አድርጎ የመንቀሳቀስ አስተሳሰብ እንደ ሕዝብ ለዘመናት የማንወጣው አዘቅት ውስጥ የሚከት ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የተፈጠረው ችግር በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ መጥፎ ታሪክ እንዲጻፍ የሚያደርግ እኩይ ድርጊት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ያለ ሰላም ትምህርት የማይታሰብ በመሆኑ ችግሩ እንዳይደገም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለሰላም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) በበኩላቸው ትምህርት ላይ ያልሠራ ሀገር እና ሕዝብ ከችግሩ መውጣት የማይችል እና የትውልድ ቅብብሎሹም ባልተለወጠ ትውልድ መካከል እንደሚሆን መግለጻቸውን ከቢሮው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here