ናይጀሪያዊቷ በሀምሳ አምስት ሰዓታት ለዘጠና ሰዎች ቃለ መጠይቅ በማቅረብ ቀደም ብሎ በሰላሳ ሰባት ሰዓታት ከአርባ አራት ደቂቃ ተይዞ የነበረውን ረዢም ቃለመጠይቅ የማቅረብ የጊዜ ምጣኔን በማሻሻል ለክብረ ወሰን መብቃቷን ዩፒአይ ድረ ገጽ አስነብቧል::
ናይጄሪያዊቷ ክላራ ቺዞቦ ክሮንቦርግ በዩቲዩብ የሴቶች ዓለም ትርኢት አዘጋጅ ናት:: አዘጋጇ የተለያየ ሙያ፣ የኑሮ ደረጃ ፣ እድሜ ፣ ፆታ ወዘተ ያላቸው ሰዎችን በቃለመጠይቋ አካታለች::
ናይጄሪያዊቷ ለዓለም አቀፉ የክብረ ወሰን ባለሙያዎች በክብረ ወሰን ሙከራዋ የተለያዩ ግለሰቦችን በማሰባሰብ፣ አነቃቂ ትረካዎችን እንዲያካፍሉ በማድረግ ትርጉም ያለው ግንኙነት መፍጠርን ዓልማ መከወኗንም ተናግራለች::
ክላራ በሀገሯ ናይጄሪያ በችግር ተፈትና ማደጓ መነሻ እንደሆናት ጠቁማለች:: በትሪኢቱ ከሚቀርቡ የተምሳሌቶች ድምጽ ሌሎች ተምረው፣ የአሸናፊነት ስነልቦናን ተላብሰው ውጤታማ እንዲሆኑ ማነሳሳት ዋነኛ ግቧ መሆኑንም ነው ያሰመረችበት::
ክሮንቦርግ ቃለ መጠይቁን በስፔን ማርቤላ መልህቋን በጣለች ጀልባ ላይ ነበር ያካሄደችው:: ቃለ መጠይቋን ስታደረግ በየአንድ ሰዓት ልዩነት የአምስት ደቂቃ ረፍት ተፈቅዶላትም ነበር::
ጋዜጠኛዋ የአንገት እና የጀርባ ህመም ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የተለያዩ ለጆሮ የማይመቹ ሸካራ ድምፆችን መስማት ከገጠሟት ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑ ነው የተገለጸው።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም