ቅድሚያ ለሠላም!

0
71

ሠላም የሁሉም ነገር ዋስትና ነው። ሰርቶ ለመለወጥ፣ ተምሮ ለማደግ፣ ነግዶ ለማትረፍ፤ አርሶና ዘርቶ ለመጠቀም፤ ወልዶ ለመሣም እና ለማሣደግ ብሎም የትውልድ ቅብብሎሽን ለማስቀጠል ሠላም በእጅጉ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

ስለነገ የምናስበው እና ለነገ የምናቅደው ሠላም ሲኖር እና በሰላም መኖር ስንችል ብቻ ነው። ሠላም ከፖለቲካ፣ከኢኮኖሚ እና ከማሕበራዊ ጉዳዮች ባሻገር ሰዎች ከተፈጥሮ እና አካባቢያቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እና የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው።

ሠላም ከምንም እና ከማንም በላይ ለሰው ልጆችም ሆነ ለሌሎች ሕይወት ላላቸው ፍጡራን ሁሉ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ስለመሆኑ በርካታ መገለጫዎች ያሉ ሲሆን  ለምሳሌም በሠላም አውለን፤ በሠላም አሳድረን፣ ሠላም ሁኑ፣ ሐገሩን ቀየውን ሠላም ያርገው   ወዘተ እየተባለ በየዕለቱ ስለ ሠላም ይነገራል ይሰበካል በአማኞች ዘንድም በጸሎት መካከል በስፋት ይነሳል።

የሠላም አስፈላጊነቱ የታወቀ ቢሆንም ጠቀሜታው ጎልቶ የሚታወቀዉ ደግሞ ግጭት ሲፈጠር ነው። በክልላችንም ምንም እንኳ ከሰሞኑ በተሰሩ በርካታ ስራዎች በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ሠላም የሠፈነ ቢሆንም ከባለፈው አንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ በቆየው ግጭት ግን ክልሉ  ቀውስ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።

በክልሉ በደረሰው የሠላም እጦት በርካታ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም የክልሉ ህዝብ ከማሕበራዊ ግንኙነቱ እና እንቅስቃሴው እንዲገደብ፣ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ እንዳይጠናቀቁ፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ፣ መምህራንም መደበኛ ስራቸውን እንዳይሰሩ፣ አርሶ አደሮችም ዘወትራዊ ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ፣ ያመረቱትንም ወደ ገበያ አውጥተው እንዳይሸጡ እና እንዳይለውጡ በማድረጉ ህዝቡን ለድህነት እና ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት ዳርጎታል።

በክልሉ በተከሠተው የፀጥታ ችግር የተነሳ የተፈጠረውን ዘርፈ ብዙ ችግር በፍጥነት በመቀልበስ  ክልሉን  ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ ስለ ሠላም መወያየት ለነገ የማይባል ቁልፍ ተግባር ነው።

እናም የወቅቱ ዋነኛ ጥያቄ ክልሉን ወደ ሠላም መመለስ እና ሠላም ከሚያስገኛቸው ገፀ በረከቶች መሣተፍ አሁናዊ ተግባር መሆን እንዳለበት ሁኔታዎች አመላካች ናቸው።

በመሆኑም ስለ ሠላም በመወያየት እና በመነጋገር  ሠላም የሚሰጣቸውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች  ማለትም ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርታቸው ተመልሰው የትውልድ ቅብብሎሹ እንዲቀጥል፣ ትውልድን የሚቀርፁ መምህራን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም፣ ለህዝቡ ሠላም እና ደህንነቱ ተረጋግጦለት በሰላም ወጥቶ በሠላም እንዲገባ፣ ነጋዴው በሠላም እንዲነግድ፣ ሠራተኛው እና አርሶ አደሩ ስራውን ያለስጋት ያከናውን ዘንድ ማድረግ ይቻላል።

ሠላምን ደግሞ ስለፈለግነው ብቻ  የምናገኘው ባለመሆኑ ሠላም እንዲመጣ ስለ ሰላም ሁሉም መወያየት መነጋገር መፍትሔዎችን ማፈላለግ ግድ ይለዋል። ይህንን ማከናወንም ለነገ የማይባል ተግባር በመሆኑ ሁሉም የክልሉ ህዝብ አሁን ላይ የጀመረውን የሠላም ደጀንነት በቀጣይነት መተግበር እና ማስቀጠል ይኖርበታል።

ሠላም ከሌለ በሰዎች ላይ የአካል፣ የሕይዎት፣ የስነ ልቦና  ጫና ከማስከተሉ ባለፈ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ነው።

ጦርነት ለነገ ጥሎት የሚሄደውን ጠባሣና ተፅዕኖ ለመረዳት በጦርነት ያለፉ ሐገራትን የዛሬ ቁመና መመልከት በቂ ማስረጃ ነው። ለሠላም ዘብ መቆም ስለሠላም መወያየቱ አዋጭ ተግባር ነው።

በክልላችን ብሎም በሐገራችን ችግሮች ሲከሠቱ  የሚፈቱባቸው ሐገር በቀል የግጭት ማስወገጃ እሴቶቻችን ያሉን በመሆኑ እሴቶቻችንን በመጠቀም ክልሉን ወደ ሠላም መመለስ የወቅቱ አጀንዳ ነው።

በመሆኑም በክልላችን ከሰሞኑ የተጀመሩ የሠላም ውይይቶች ወደ ሠላም መንገድ እየመሩ በመሆናቸው  ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባቸዋል።

በክልሉ በርካታ አካባቢዎች በተጀመሩ ውይይቶች አማካኝነት የክልሉ የሠላም ሁኔታ አሁን ላይ በእጅጉ መሻሻል ማሣየቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ከሰሞኑ ያስታወቁ ሲሆን ከግጭት እና ከጦርነት የሚገኝ አንዳች ነገር እንደማይኖር ያለፉት ጊዚያቶች አመላክተውናል። በመሆኑም የትኛውንም አለመግባባቶች እና ጥያቄዎችን ለማስመለስ የሚመረጠው በውይይት እና በሠላም ሲሆን ውጤቱ የላቀ  ከብዙ ጉዳቶችም የሚታደግ ነውና ቅድሚያ ለሠላም በመስጠት ሠላምን እንስበክ!

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here