የአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ እና የአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ሃገራችን ኢትዮጵያ የዘመነ አሰራርን፣ ዘመናዊ ተቋማትን እና በርካታ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን በገፍ ማስተናገድ የጀመረችባቸው ጊዜያት ናቸው። በዚህ ወቅት ሃገራችን ከተቋደሰቻቸው የስልጣኔ እና የቴክኖሎጂ ፍሬዎች መካከል ዘመናዊ ትምህርት ቤት፣ ሆቴል፣ ፖስታ ቤት፣ ባንክ ቤት እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። ከቴክኖሎጂ ውጤቶች ደግሞ ተሽከርካሪ መኪና፣ የእህል ወፍጮ፣ ስልክ፣ ባቡር፣ የጽሕፈት መኪና እና ሌሎችም ይገኙበታል። በዚህ ዘመን ለታዩ መሰረታዊ ለውጦች ንጉሡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ብጡል የተጫዎቱት የፊታውራሪነት ሚና እና ተራማጅነት የሚዘነጋ አይደለም። ወቅቱ ሃገራችን ኢትዮጵያ የአድዋ ድልን የተቀዳጀችበት ጊዜም እንደነበር ልብ ይሏል።
ለዛሬ ላነሳ የወደድሁት ሃሳብ ከባንክ ቤት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ይኼውን ሃሳብ እያነሳን እንቃኛለን። ከብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በብሪታንያ በቅኝ-ገዥነት ይተዳደር በነበረው የግብፅ ብሔራዊ ባንክ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት፤ አቢሲኒያ ባንክ የሚባል በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ባንክ ተቋቁሞ የካቲት ዘጠኝ ቀን 1898 በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓጼ ሚኒልክ ተመረቆ ተከፈተ:: ንጉሠ ነገሥት ዓጼ ኃይለ ሥላሴ የባንክ ሥርዓቱን በሚያሻሽል አግባብ የአቢሲኒያ ባንክን ድርሻ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያዝ በማድረግና ስሙን የኢትዮጵያ ባንክ በማለት በአፍሪካ አህጉር የመጀመሪያውን ሃገራዊ ባንክ ለመክፈት ችለዋል፡፡ ባንኩም የማዕከላዊ ባንክ እና የንግድ የባንክ አገልግሎቶችን ይሰጥ እንደነበር ይገልጻል።
ይሄን እና መሰል የስልጣኔ ፈር ቀዳጅነት እና ተራማጅነት ስንመለከት ኢትዮጵያ በአፍሪካ የስልጣኔ እና የዘመናዊነት ጉዞ የማይፋቅ አሻራ እንዳስቀመጠች እንገነዘባለን። በዚህም በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ባንክ ቤት በመክፈት ለአህጉሩ አስተዋውቃለች። ኢትዮጵያ በዘመኑ የነፃነት ተምሳሌትነቷን ከማወጅ ባለፈ ከአህጉረ አፍሪካ አልፎ ለመላው የጥቁር ህዝብ ተራማጅነት እና የስልጣኔ ተቋዳሽነት ፈር ቀዳጅ እንደነበረች በቅንነት የመሰከሩ በርካታ ምሁራንን ዋቢ ማድረግ ይቻላል።
ዘመናዊ ተቋማትን ቀድሞ በመክፈት እና በዘመን ሂደት በማሻሻል እንዲሁም ቀጣይነታቸውን በማረጋጉጥ በኩል ለዛሬ መሰረት የሆኑ ስራዎች ተከናውነዋል ማለት ይቻላል። ከነዚህም ሃገራችን ቀድማ ስልጣኔን ከማለደችባቸው ተቋማት መካከል ባንክ ቤት ይጠቀሳል።
ባንክ ቤት በአሰራር ዘምኖ፤ ብዛቱ አድጎ፣ ቅርንጫፉንም ተደራሽ አድርጎ ለዛሬ ደርሷል። በሃገራችን ለበርካቶች የስራ እድል በመፍጠር፣ ማህበረሰቡ የቁጠባ ባህሉን እንዲያሳድግ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በመስራት እና የልማቱ አጋዥ በመሆን ሃገራዊ ግዴታውን የተወጣ ተቋም ነው ማለት ይቻላል። ሰራተኞቹም ከአለባበሳቸው ጀምሮ ስነ-ምግባራቸው ለብዙ ተቋማት አርአያነት ያለው ለመሆኑ የአደባባይ ሃቅ ነው። ይሁን እንጂ በስራ ዘርፉ በርካታ ሙያዊ ግዴታቸውን አክብረው የሚሰሩ ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ በማንኛውም ተቋም ሊያጋጥም እንደሚችለው፤ አንዳንድ የስነ-ምግባር ጉድለት ያለባቸው ባለሙያዎች አልፎ አልፎ ይስተዋላሉ።
ካነሳነው ጉዳይ ጋር የተያያዘ ገጠመኘን ላጋራችሁ ወደድኩ፤ ለስራ ወደ አንድ አካባቢ በሄድኩበት ግብይት ለመፈጸም ፈልጌ ገንዘብ ወጭ ለማድረግ በአቅራቢያዬ ወደ አለ አንድ ባንክ ጎራ አልኩ። ኤቲኤም ለመጠቀም ብፈልግም ማሽኑ መስራት በማቆሙ ወደ ባንኩ ገብቼ በሂሳብ ደብተር ገንዘብ ወጭ ለማድረግ ተገደድኩ። በጊዜው ገንዘብ ወጭ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ሂደቶችን አልፌ አምስት ሺህ ብር እንዲሰጠኝ ባለሙያውን ጠየቅኩ። ባለሙያውም እኔ እና ሌሎች ደንበኞችን እንደ አንድ ደንበኛ የሚገባንን ክብር በመንፈግ ያዋክበን ጀመር። በቦታው የነበርን ሰዎች የባለሙያውን ግልምጫ ለመሸሽ በመሻት ገንዘባችን ተቀብለን ከቦታው ተንቀሳቀስን።
ግብይት ከምፈጽምበት ቦታ ደርሼ ገንዘቡን ስቆጥር አንድ ሺህ ብር ይጎላል። ጉዳዩን ለማስረዳት ወደ ባንኩ ስደርስ የኔ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠማቸው በርካታ ሰዎችን አገኘሁ። ባለሙያው እና አስተባባሪው በጊዜው ቆጥረን እንዳንረከብ ፋታ ነስተው እንዳስወጡን ሳስብ ጉዳዩ አጠራጠረኝ። ጉዳዩን ለማስረዳት ብንጥርም “አውቆ የተኛን ሰው ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲል ብሒሉ ከቀድሞው በባሰ እና እጅግ ክብረ ነክ በሆነ መንገድ ምላሽ ሰጡን። ከመካከላችን የነበረ አንድ ህግ አዋቂ ሰው ከባንኩ ስራ አስኪያጅ ጋር በአግባቡ ተነጋግሮ ሒሳቡ እንዲጣራ አድርጎ ገንዘባችን ተመላሽ ተደረገ።
አንዳንድ ሙያዊ የስነ-ምግባር ጉድለት ያለባቸው ሰዎች ከደንበኞች ሂሳብ በመቀናነስ ባልተገባ መንገድ ጥቅም ለማግኘት እንደሚሞክሩ ከሰማን ሰነባብተናል። በማህበራዊ ሚዲያ ጭምር ማጭበርበር የተፈጸመባቸው ደንበኞች ጉዳዩን ሲያጋሩ ተመልክተናል። ሞኝ ከራሱ ይማራል እንዲሉም እኔም ከራሴ ገጠመኝ ተምሬያለሁ።
“ቆጥረው ይረከቡ” የሚል ሃሳብን እንደ ሽፋን በመጠቀም አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች እየፈጸሙት የሚገኘው ማጭበርበር ልክ አይደለም። መተማመን ከሲስተም፣ ከህግ እና ደንብ በላይ ነው። የሰው ልጅ በብዙ የሃሳብ ማዕበል የሚዋኝ ፍጡር እንደመሆኑ ያንዱን ክፍተት አንዱ በመሸፈን መተባበርና አብሮ ማደግ የሚገባ ነው። መማር እና ሙያዊ ክሂሎትን ማሳደግ ሳይማር ያስተማረን ምስኪን ህዝብ በክፍተቱ ለመጠቀም መሆን የለበትም። ህገ ደንብ ለማስከበር እና ስነ-ስርዓት ለመዘርጋት እንጂ ሰውን በክፍተቱ ለማጥቃት ጥቅም ላይ መዋል የለበትም። ከዚህም በተጨማሪ በአንዳንድ ባንኮች የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ግድፈቶች ሊታረሙ ይገባል። በርግጥ ከተገልጋዩ ማህበረሰብም ቢሆን ለማጭበርበር ሙከራ የሚያደርጉ እንዳሉ ባይዘነጋም ቁጥጥር እና ክትትልን በማሳደግ እንጂ በተመሳሳይ ማጭበርበር ይስተካከላል ተብሎ አይታመንም።
ባንክ ቤቶች ሃገራችን ቀድማ ስልጣኔን ከማለደችባቸው ተቋማት መካከል ተጠቃሽ በመሆናቸው ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ራሳቸውን አዘምነው እና የአገልግሎት ተደራሽነታቸውን አስፍተው ማየት የዬትኛውም ኢትዮጵያዊ ቀና ምኞት ነው። ተቋማቱ አህጉራዊ ቀዳሚነታቸውን እና ጉምቱ የጋራ ታሪካቸውን በማጤን ዓርዓያነታቸውን ሊያስቀጥሉ ይገባል። ከዚህ በተለዬ ሁኔታ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ተግባራት ግን ተቋማቱ ያላቸውን ጉምቱ ታሪክ እና መልካም ስም የሚያጎድፍ እና ማህበረሰባዊ ተቀባይነት በማሳጣት እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ የሚያስኬድ ነው። ሃገራችን በዘርፉ አህጉራዊ የታሪክ ቀዳሚነት እንዳላት በመገንዘብ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ መትጋት ይገባል። ካልሆነ ግን ዙሩን በቀዳሚነት መርቶ በአስራ አንደኛው ሰዓት መሸነፍን ያስከትላል።
(ደረጀ ደርበው)
በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም