በልደቱ – አንዳንድ ነገሮች

0
150

ከባህል የተነጠለ እምነት የለም። የሰዎች አኗኗር ትውፊትን ፈጥሮ ከሃይማኖታቸው ጋር የተቀላቀለ እንዲሆን አድርጎታል። የመላው ዓለም ክርስትና እምነት ተከታይ ሀገራት  በፈረንጆች አቆጣጠር ታኅሳስ  25 ቀን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ያከብሩታል። የኢትዮጵያም የልደት በዓል ታኅሳስ 28 እና 29 ቀናት በየአራት ዓመቱ እየተፈራረቀ ይከበራል። በሀገራችን አብሮ ከመብላት፣ መጠያየቅ፣ ቅርጫ እና ሌሎች ማህበራዊ ክዋኔዎች በተጨማሪ የገና ጨዋታ ልዩ የልደት በዓል ድምቀት ነው። በርግጥ አሁን የገና ጨዋታ ወደ ታሪክነት እየተቀየረ ነው። ፈረንጆች ይህን የገና ጨዋታ ሆኪ ብለው ዘመናዊ ስፖርት አድርገውታል። የገና ጨዋታም በኢትዮጵያ ከባህል ስፖርቶች አንዱ ሆኗል።

የገና በዓል የኢየሱስ  ክርስቶስን ልደት ተከትሎ የሚቀርብ የብዙዎች ትዝታ ነው። “አሲና ገናዬ” ዘፈን ደግሞ በዓሉን ለማክበር ድምቀት ከሚሰጡት ክዋኔዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ ዘፈን ቀደምት ታሪክ ያለው ሀገረሰባዊ ዘፈን ነው። በዚህ ዘፈን ብዙ ቀደምት ዘፋኞች ቢታወቁበትም እንኳን በ1966 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት ባልደረቦች አጃቢነት እና ፍሬው ኃይሉ ዘፋኝነት ተሰርቷል። ይህን ዘፈን ከፍሬው ኀይሉ በኋላ የተለያዩ ድምጻዊያን በየዘመኑ መንፈስ አቅርበውታል።

ፍሬው ኃይሉ በነገራችን ላይ በታኅሳስ 26 ቀን 1933 ዓ.ም በትግራይ ተምቤን ነው የተወለደው። በልጅነቱ በአጥቢያው ደብር በዲቁና አገልግሏል። በ14 ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት ተቀጠረ። ዘመኑም 1947 ዓ.ም ነበር። ግጥም፣ ዜማ  ደራሲ እና የሙዚቃ መሳሪያም ተጫዋች ነው። ከአሰለፈች አሽኔ ጋር በመሆን “አልማዝ ምን እዳ ነው” የሚለውን ዘፈን በቀጭን ድምጹ በጋራ አቅርቧል። ፍሬው በጊዜው ድምጹ ቀጭን ስለነበር ሲዘፍን ብዙዎችን “ሴት ናት” በሚል ያወዛግብ ነበር። ጥር 7 ቀን 1981 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ተለይቷል። ፍሬው ኀይሉ ዳዊት የሚባል የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ልጅ ተክቶ ያለፈ ቢሆንም ዳዊት ፍሬውም በጣሊያን ሀገር በ2015 ዓ.ም  ሕይወቱ አልፏል።

የፍሬው አሲና ገናዬ ዛሬም አዲስ የበዓል ስሜት የሚፈጥር ገና የተጫዎትን ሰዎችን ከልጅነት ትዝታዎቻችን ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ነው ታሪኩን ያነሳሁት። የፍሬውን ሙዚቃ የቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ጣቢያዎች የፕሮግራሞቻቸው ማድመቂያ በማድረግ ሁልጊዜም በየዓመቱ ይጠቀሙበታል። የገና ሐሳቦችን ወዲያ ወዲህ እያልን እንመልከት።

የገና ጨዋታ መሰረቱ ሀገራዊ ነው። ፍሬው ኀይሉ ወደ መድረክ አመጣው እንጂ በገጠር ጎረምሶች ከገና በዓል በፊት ሳምንታትን ቀድመው ሩር ሰርተው፣ ገና እንጨት አዘጋጅተው፣ መጫዎቻ ሜዳቸውን ምቹ አድርገው የሚጠብቁት በዓል ነው። ወጣቶች ለሁለት ተከፍለው በቡድን የሚጫዎቱት ጉልበት የሚጠይቅ፣ መቁሰል፣ መድማት እና ከዚህም ያለፈ ጉዳት ሊያጋጥም የሚችልበት ባህላዊ ክዋኔ ነው። አሸናፊ እና ተሸናፊ አለበት፣ ፉገራ እና መተራረብ በዘፈኖች እና ቀንዶች ይቀርባል። አሸናፊው ይወደሳል፤ ተሸናፊው ይናቃል። በዓሉ ነጻነትን ይሰጣል። አሸናፊው ተሸናፊውን በግጥም ቢሸነቁጠው፣ በሩር ወይም በበትር ቢመታው “ለምን” አይባልም። ቂም አይያዝም፣ በቀል አይታሰብም። ለምን ጨዋታው “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” ብሏልና። ለምሳሌ አንዱ እንዲህ ብሎ ሊዘፍን ይችላል፤

“ሲሄድ ቅትር ቅትር ሲበላ እንደ አንበጣ

ወዘና የሌለው የጨጓራ ቋንጣ”

ይህ ሰው ቀጭን በመሆኑ ተረብ ቀርቦበታል። እሱም በግሉ ግጥም አዘጋጅቶ ከመተረብ ውጪ ምንም ምርጫ የለውም። ጨዋታው ገና፤ ሕጉ መቆጣት አይቻልም የሚል ነው። ምናልባት ሌላው ቀን ቢሆን በትንሽ ነገር ጸብ ቢፈጠር ሽመሉን ሳብ አድርጎ ተሳዳቢውን በፈነከተው ነበር። የገና ቀን ግን ይህን ማድረግ በፍጹም አይቻልም – ሕጉ ነጻነት ነውና። ይህ ሕግ ከሜዳ የታፈሰ አይደለም። ከኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ እና የአዳምን በደል በይቅርታ ከማዳን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው። የክርስቶስ ልደት የሰው ልጆች ሁሉ ከበደል ነጻ የወጡበት በመሆኑ የገና ጨዋታው ነጻነትን ወርሶ ቀጥሏል።  የገና ጨዋታ አሁን ተዳክሟል። ምክንያቱ ደግሞ የከተሞች መስፋፋት፣ በገጠርም የሚጫወቱ ወጣቶች ወደ ትምህርት እና  ሌሎች ነገሮች ማዘንበላቸው ሳይሆን አይቀርም። ከተሞች ላይ ለመጫዎትም በቂ ቦታ የለም። በከተሞች የተያዘው ገናን መሳይ እንጨት ሰርቶ በየመንገዱ እና ቤቱ እየገቡ ብር  መቀበል ነው። በተጨማሪም በከተሞች የገና ዛፍ እና የገና አባት የሚሉ የበዓል ማክበሪያ ልማዶች መስፋፋት ጀምረዋል። የገና በዓል የስጦታ በዓል ነው የሚል ልምምድ እየተዘወተረ ነው። የገና አባት ማን ነው? ዛፉስ ከየት መጣ?

ዓለም ዛሬ ወደ አንድ ማህበረሰብነት የመለወጡ ማሳያዎች ብዙ ናቸው። የፈረንጆችን አዲስ ዓመት እና የገና በዓል ሁለት ጊዜ የሚያከብሩ የሀገራችን ሰዎች እየበዙ ነው። ጎዳናዎች፣ አደባባዮች፣ ሕንጻዎች፣ መንደሮች እና ቤቶች በብልጭልጭ መብራቶች እና ጌጣጌጦች ያሸበርቃሉ። በሰው ሰራሽ ጽድ ዛፎች ያሸበርቃሉ።

ፈረንጆች ገናን ሲያከብሩ ሳንታ ክላውስ (የገና አባት) የሚሉትን ሽማግሌ ሰው ምስል፣ ቅርጽ ይጠቀማሉ። ረጃጅም የጽድ ዛፎችንም በቤታቸው እና ጎዳናዎች ላይ ያስቀምጣሉ። ነጭ እና ቀይ የሳንታ ክላውስን አልባሳት የሚወክሉ ቀለማትን በመጠቀም ይለብሳሉ። ሳንታ  ክላውስ  በፈረንጆች ሀገራት የገና አባት ተብሎም ይጠራል። ሳንታ ክላውስ በፈረንጆቹ ገና ስጦታውን ከወላጆች ይቀበልና ለሕጻናት ይሰጣል። በዚህም ገና ሲደርስ ስጦታ ይዞላቸው የሚመጣ የሸበተ ጺም ያለው ነጭ እና ቀይ ቀለም ልብስ የሚለብስ ሽማግሌ ሰው ነው። ወላጆች ለልጆች ስጦታ ደብቀው ይሰጧቸውና ሳንታ ክላውስ አመጣላችሁ ይሏቸዋል። ለገና ስጦታ የሚያመጣላችሁ የገና አባታችሁ ነውም ይሏቸዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መምህር ብርሃኑ አድማስ፤ ስለ ሳንታ ክላውስ ታሪካዊ ጅማሮ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ቅዱስ ኒቆላዎስ የሚባል በ4ኛው ክፍለ ዘመን ግሪክ ውስጥ  የኖረ ቅዱስ እና ትልቅ ሊቀ ጳጳስ  ነበር ይላሉ። ይህ ሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ስንክሳር ውስጥ ኒቆላዎስ ተብሎ እንደሚታወቅ እናም የተለዬ የመስጠት ታሪክ ያለው ሰው እንደነበር ይናገራሉ።

በግሪክ ሀገር አንድ አባት አራት ሴት ልጆች ነበሩት። ያ ወላጅ ልጆቹን ለመዳር ገንዘብ ያጣል። በመሆኑም ለልጆቹ የጎጆ መመስረቻ ገንዘብ ስለሌለው ልጆቹን የሚያገባለት ሰው አጥቶ ይቸገራል። አባትም ከድህነት የተነሳ ሴት ልጆቹን የመሸታ ቤት ሕይወት እንዲጀምሩ ያደርጋቸዋል። ልጆቹን በዝሙት ስራ እንዲኖሩ የፈቀደው ቢቸግረው ነው ብሎ ያስባል። አዘነለት፣ ራራለትም። ቅዱስ ኒቆላዎስም ለዚህ ደሀ ሰው እየተደበቀ 100 ወቄት ወርቅ አስቀምጦለት ወደ ቤቱ ይመለሳል።

ደሀው አባት ጠዋት ከመኝታው ሲነሳ ከቤቱ ያንን ወርቅ ያገኛል። እግዚአብሔር ሰጠኝ ብሎ ተደስቶም አንዲት ልጁን ለባል ዳራት። ሁለተኛዋንም የሚድርበት ወርቅ ሰጠው። ሦስተኛ እና አራተኛ ልጆችንም ኒቆላዎስ ለደሀው ወርቅ በመስጠት ባል እንዲያገቡ አድርጓል ሲሉ መምህር ብርሃኑ አድማስ ተናግረዋል። ይህም ስጦታ በስውር የመስጠትን የቤተ ክርስቲያንን እምነት የሚያሳይ ነው ይላሉ። ሰጪው እንዳይመጻደቅ፣ ተቀባዩም እንዳይሳቀቅ በድብቅ መስጠትን ቅዱስ ኒቆላዎስ አስተምሯል።

ከዓመታት በኋላ የጀርመን ፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ይህን የቅዱስ ኒቆላዎስን ስም እና ተግባር ሳንታ ክላውስ ብለው እንደተከተሉት መምህሩ ይገልጻሉ። የገና አባት በማለትም መጥራት የተጀመረው ከዚህ በመነሳት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ሁሉ ድህነት የተሰጠ ስጦታ መሆኑን መነሻ በማድረግ  የገና በዓል የስጦታ በዓልነቱን ያጎላዋል። ቅዱስ ኒኮላስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስሙ ቅዱስ ኒቆላዎስ በሚል ይታወቃል። ዘመናዊው ዓለም ይህን ታሪክ ሳንታ  ክላውስን የገና አባት ሲል የስጦታ አባት አድርጎታል። ሳንታ ክላውስን ከባዕድ አምልኮ ጋር አያይዘው የሚተነትኑም ጽሐፊዎች አሉ።

የጽድ ዛፍን ብዙዎች የገና ዛፍ ነው ብለው ይጠሩታል። በተግባርም የገና በዓል ሲከበር የዝግጅት ማድመቂያ ሆኖ ይታያል። በምዕራቡ ዓለም በአስቸጋሪው የክረምት ወቅት ዛፎች ሁሉ ቅጠሎቻቸው ይረግፋሉ፤ ልምላሜ ይርቃቸዋል። ጽድ ዛፍ  ግን በተፈጥሮው ይህን አስቸጋሪ ወቅት ተቋቁሞ የማለፍ ጉልበት አለው። የክረምቱን ዘመን አልፎ ከፈረንጆች አዲስ ዓመት የሚደርሰው የጽድ ዛፍ ብቻ ነው። የፈረንጆች አዲስ ዓመት እና ገና በተቀራራቢ ጊዜያት የሚከበር በመሆናቸው የጽድ ዛፍን አዲስ ዓመትን ለማድመቅ እንጂ ለገና በዓል እንደማይጠቀሙበት የሚናገሩም አሉ። ያም ይባል ይህ በዓለማቀፋዊነት ወጀብ ምክንያት የገና በዓል ዓለም አቀፍ አከባበሮችን በሀገራችን እየተከተልን ቀጥለናል። ትናንት ያጣጣልነው ባዕድ ባህል ዛሬ በየከተሞች ፋሽን ሆኗል። ነገሮችን አውቀን በምክንያት ብንወስድ እንዴት መልካም ነበር፤ ነባሩን ባህል   ገና ጨዋታን ትተን ሌላውን ሆነ እንጂ።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here