ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሕገ ወጥ መንገድ ዜጎችን ከሀገር ማሻገር የተለያዩ የወንጀል ዓይነቶች መሆናቸውን በ2007 ዓ.ም የወጣው አዋጅ ቁጥር 909/2009 ያመላክታል:: በጉዳዩ ዙሪያ የአማራ ሚዲያ ኮርፓሬሽን የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዬ ካሣሁን በሰጡን ማብራሪያ ዜጎችን በሕገወጥ መንገድ ከሀገር አስወጥቶ እና ከድንበር አሻግሮ ወደ ሌላ ሀገር የሚልኩ አካላት በወንጀል ተጠያቂ ናቸው::
አሁን ባለው ሉዓላዊነት (ግሎባላይዜሽን) የዓለም ሀገራት አንድ መንደር ሲሆኑ የንብረት እና የሰዎች ዝውውር ያለገደብ እንዲከናወን እና የሀገራት ሉዓላዊ ድንበሮች እንዲላሉ ሆኗል የሚሉት አቶ አብዬ፤ ይህን ተከትሎም ከመንግሥታት እና ከሀገራት እውቅና እና ቁጥጥር ውጭ ብዙ ነገሮች የሚንቀሳቀሱበት ሆኗል:: ይህን ተከትሎ ደግሞ ሰዎች በቀላሉ የሚከብሩበት ሕገወጥ መንገድ አደንዛዥ እፅ፣ መሣሪያ እና የሰዎች ዝውውር ሆኗል::
ሕጋዊ ሥርአትን ተከትለው ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ድንበር መሻገር የሚገባቸው ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ለማግኘት በተሰማሩ አሻጋሪዎች እጅ እንዲወድቁ አድርጓል:: ይሄ እየሰፋ ሲሄድ ዘመናዊ ባርነትን እያስከተለ መሆኑን በተግባር የሚያሳይ ድርጊት እየመጣ በመሆኑ ዓለም ተሰብስቦ የተለያዩ የሕግ ማእቀፎችን አውጥቷል:: ይህን ተከትሎም በሰዎች ላይ የሚፈፀመውን ሕገወጥ ዝውውር ለመከላከል የሚያስችል የጋራ/ኘሮቶኮል/ ስምምነትም ተደርጓል:: ሀገራችንም በየበረሃው የሚቀሩ፣ ባህር የሚበላቸው እና የአካል ክፍላቸው ተሸጦ የሚቀሩበት ሰዎች ብዙ በመሆናቸው በአዋጅ ቁጥር 909/2007 ላይ ሰፍሯል:: አዋጁ ሁለቱንም ወንጀሎች ራሳቸውን አስችሎ ትንተና ሰጥቷል::
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ማለት ሰዎችን በማስፈራራት፣ በኀይል ወይም በማሳሳት፣ ወይም የተለያዩ መደለያዎችን ሰጥቶ በመመልመል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በማዘዋወር የሚፈፀም ሕገወጥ ድርጊት መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል:: በዚህም በሕገወጥ መንገድ አካባቢያቸውን እና ሀገራቸውን ትተው ለስደት የሚዳረጉ ወገኖች ሕይወት ማጣት፣ የአካል ጉድለት፣ የጉልበት ብዝበዛ፣ የሥነ ልቦና ጫና ይደርስባቸዋል::
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባሩ የተጎጅን ምልመላ፣ ማጓጓዝ፣ ማሻገር፣ ማረካከብን ያካተተ ነው:: የዚህ ድርጊት ዓላማ ደግሞ ለአደገኛ ብዝበዛ በተለይ ሴቶችን ለሴተኛ አዳሪነት የሚዳርግ ነው:: ለአብነት በሀገር ውሰጥ ከአንድ ቀበሌ፣ ዞን እና ክልል መልምሎ በሌሎች ከተሞች አካባቢ እና ከሀገር ውጭም ይከናወናል:: ይሄ ደግሞ በአዋጅ 909/2007 አንቀፅ 3 ላይ በዝርዝር ተመልክቷል::
ሌላው በአዋጅ 909/2007 አንቀፅ 5(አምስት) ላይ የተደነገገው ሰዎችን ከአንድ ሉዓላዊ ሀገር ወደ ሌላ ሉአላዊ ሀገር በማሸጋገር የሚሠራ ነው:: ይህ ድርጊት የማስገድ ሁኔታ የለውም፤ ተዘዋዋሪው ሰው ተሰማምቶ ክፍያ ከፍሎ ለመጓዝ በሚያደርገው ሂደት የሚገኘው ለአጓጓዦች ክፍያ ነው:: በፍቃደኝነት የሚፈፀም ነው። ነገር ግን ሁለቱም ወንጀሎቹ እርስ በእርስ የሚያያዙበት ሁኔታ አለ፤ ሰዎችን ለማዘዋወር (ለማሻገር) ተብሎ ዜጎች በኀይል ታግተው ተጨማሪ ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚደረግበት የብዝበዛ ሁኔታ ነው::
ሀገራችን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን አስመልክቶ ያፀደቀችው 909/2007 አዋጅ ተፈፅሟል ማለት የሚቻለው ማንኛውም ሰው በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥ የሆነ እና ከውጭም ቢሆን ለብዝበዛ ዓላማ ወደ ውጭ መላክ፣ በጉዲፈቻ ሽፋን፣ ዛቻን በተጠቀመ መንገድ… በማገት፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም የተስፋ ቃል በመስጠትም ይሁን ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም ሰዎችን ለጥቃት ተጋላጭነት በመጠቀም የመለመለ፣ ያጓጓዘ፣ ያዘዋወረ፣ ያስጠለለ ወይም የተቀበለ ሁሉ በሂደቱ የተሳተፉት ሁሉ ወንጀለኛ ሆነው እንደሚቀጡ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል::
ይሄን ያደረጉ ሰዎች ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት እስራት እና ከ150 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር ይቀጣሉ:: ይህ ቅጣት መነሻው ነው የሚሉት አቶ አብዬ፤ ማክበጃ ምክንያቶች ደግሞ ወንጀሉ የተፈፀመው በአካል ጉዳተኛ እና ሕፃናት ላይ ከሆነ ደግሞ ጠንከር ብሎ ከ25 ዓመት ያላነሰ ወይም የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እና ከ200 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ የገንዘብ መቀጫ ይደርሳል::
በዚህ ወንጀል መደገፍ እና ማመቻቸት የተሳተፈ ሰው ከ15 እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እና ከ150 ሺህ እስከ 300 ሺህ የገንዘብ መቀጫ ይቀጣል:: ድርጊቱ ሰዎች በሰዎች መብት ላይ ጉዳት እያደረሱ በቀላሉ ገንዘብ የሚያገኙበት በመሆኑ አዋጁ ሰው በአደገኛነት ስለፈፀመው ወንጀል እንዲቀጣ ጠንከር ብሎ የወጣ ሕግ ነው ብለዋል::
በሕገ ወጥ መንገድ ዜጎችን ድንበር ማሻገር በተመለከተ ያለው ተጠያቂነት አንቀፅ 5 (አምስት) ላይ ማንኛውም ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የገንዘብ ጥቅም ወይም ቁሳዊ የሆነ ነገር ለማግኘት፣ ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ለማስገባትም ሆነ ከኢትዮጵያ ግዛት ለማስወጣት ድንበር ካሻገረ፣ ለማሻገር ከሞከረ ወይም ለማሻገር በዝግጅት ላይ ከሆነ ወንጀል ፈፀመ ተብሎ ከ15 ዓመት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት እና በብር ከ150 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር ይቀጣል:: ድንበር ያሻገረም፣ ለማሻገር የሞከረም ዝግጅት ላይ ያለም ሁሉም ይቀጣል:: ድርጊቱ በተለይ በሕፃናት፣ ሴቶች እና አካል ጉዳቶኛች ላይ የተፈፀመ ከሆነ ከ20 ዓመት ያላነሰ ፅኑ እስራት እና ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ የሚደርስ ገንዘብ ያስቀጣል::
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በጣም ከባድ የሚባለው ደግሞ ድንበር በሚሻገሩ ሰዎች ላይ ሞት ከተከሰተ፣ አካል ጉዳት ከደረሰ እና በቡድን የተፈፀመ ከሆነ ብዛቱን እያየ ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት ድረስ ሊያስቀጣ ይችላል:: በዚህ ሂደት ላይ የሚሳተፉ፣ የሚያሸጋግሩ፣ የተዘጋጁ ቅጣቱን ይቀጣሉ::
ወንጀሎቹ ሲፈፀሙ ሁለቱም ላይ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር አለ የሚሉት አቶ አብዬ፤ የጉዞ መረጃ፣ መታወቂያ፣ ሰነድ የማሟላት ሂደት (ማመቻቸት) ሥራ የሚሰሩት ሁሉ፣ ሕጋዊ ሰንዶችንም በሕገወጥ መንገድ አደራጀተው ስለሚሠሩ እነዚህ ድጋፍ ሰጭዎች ሀሉ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት ይቀጣል::
ከሀገር ሀገር የሚሻገሩ ሰዎችን እያየ ዝም ያለ፣ እንዲቆዩ የተባበረ የአካባቢው አመራር ጭምር በትብብር ይቀጣል:: ሕጉ በተቻለ መጠን የወንጀል ድርጊቱ እንዳይስፋፋ ሁሉንም በሮች ዝግ ያደረገ ነው:: ነገር ግን ድርጊቱ ከፍተኛ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ጥቅም ያለው በመሆኑ ወንጀሉን መከላከል በወንጀል ሕጉ ላይም የተቀመጠ ነው:: ችግሩ እየተባባሰ ሲሂድ በሀገር ደህንነት ለሰዎች መብት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ እያደገ ስለሚሄድ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየተተገበረ ይገኛል:: ምንም እንኳን ጠቅላላ ውጤቱ በኅብረተሰቡ ጠቅላላ ውጤት ላይ የሚያወጣው ተፅዕኖ ከፍተኛ እና ጉዳዩ የግለሰብ ብቻ ስላልሆነ ያየ የተመለከተ ሁሉ ማስረጃ መሆን መቻል እንዳለበት ነው አቶ አብዬ ያስገነዘቡት:: ወንጀሉ ከመሠራቱ በፊት መቆጣጠር እና መከላከል ላይ መሥራት ሲቻል ደግሞ በርካታ ሰዎችን ማዳን የሚቻልበት እድልም እንዳለ ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል::
የህግ አንቀጽ
ሰው የማይደፈርና የማይገሰስ የአካል ደህንነትና ነጻነት እንዳለው በሕገ መንግሥቱ ሰፍሯል
• አንቀጽ14፡- በሕይወት የመኖር መብት የማንኛውም ሰው መብት መኖሩን
• አንቀጽ16፡- ጭካኔ ከተሞላበት ኢሰባዊ ከሆነ አያያዝና ክብሩን ከሚያዋርድ አያየዝ የተጠበቀ መሆኑ
• አንቀጽ18/1/፡- ማንኛውም ሰው በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ አይችልም፡፡
በማንኛውም ዓላማ በሰው የመነገድ ተግባር በሕግ የተከለከለ ነው፡፡
• አንቀጽ 18/2/፡-የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ በሰው የመነገድ ወንጀልን ክልክል ያደረገው እድሜንና ጾታን ሳይለይ ማንኛውንም ሰው በተመለከተ ነው፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም