በመቃብር  ቁፋሮ አንደኛ የወጣዉ

0
61

በሀንጋሪ በተካሄደው ስምንተኛው  ዓለም አቀፍ የመቃብር ቁፋሮ ውድድር “ፓራክላቶዝ” የተሰኘው አዘጋጇን ሀገር የወከለው የአለፈው ዓመት አሸናፊ ዳግም በአንደኛነት ማጠናቀቁን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል፡፡

ዓለም አቀፍ የመቃብር ቁፋሮ ውድድር በሀንጋሪ ከ2016 እ.አ.አ ጀምሮ በተከታታይ ከ2020 እና 2021 ዓመታት በስተቀር ተካሂዷል፡፡ በውድድር ዓመቶቹ ከአውሮፓ ሀገራት ሁለት ሁለት ዓባላት ያሉት ቡድኖች ወደ አዘጋጇ ሀገር ሀንጋሪ በመላክ ተሳትፈዋል፡፡

በውድድሩ ህግ መሰረት ሁለት ቆፋሪዎች ሁለት ሜትር ርዝመት፣ ሰማኒያ  ሴንቲ ሜትር ስፋት እና አንድ ሜትር ከስልሳ ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ቆፍረው፣ በሚገባ ጠርበው እና አስተካክለው ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ያወጡትን አፈር መልሰው በማስገባት ጉብታ ያለው መቃብር  ደልድለው ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል- በውድድሩ፡፡

ውድድሩ ቀላል ቢመስልም ፍጥነት፣ ትክክለኛነት እና ዝርዝር ትኩረት አድርገው መከወናቸው በዳኞች ክትትል ይደረግበታል፡፡ መስፈርቱ የሚይዘው ጠቅላላ ነጥብ 10 ሲሆን አሥሩ በፍጥነት አፈፃፀም፣ በትክክለኛነት እና በዝርዝር የትኩረት አፈፃፀማቸው  በዳኞች ተገምግሞ የአሸናፊነት ደረጃቸው ይወሰናል ፡፡

በዘንድሮው መስከረም 6 2025 እ.አ.አ በተካሄደው ውድድር የሀንጋሪው “ፓራክላቶዝ” የተሰኘው ላዛሎ ኪስ እና ሮበርት ናጊ የተባሉ አባላትን የያዘው በድን አንድ ሰዓት ከ33 ደቂቃ ከ 20 ሰከንድ በሆነ ጊዜ ያለፈው ዓመት አንደኛነታቸውን አስጠብቀው ለሁለተኛ ጊዜ አሸናፊ መሆናቸው ነው ለንባብ የበቃው፡፡

ከ21 ተወዳዳሪዎች ከሩሲያ ሳይቤሪያ ቀጣና ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለው “ኖቮሲቢ ሪስክ ክሪማቶሪየም በሚሰኝ ቡድን ጐርቢኮቭ እና ሰርጌ ያኩሺንን ያቀፈው ልኡክ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ለሽንፈታቸው የመሬቱ ጥብቅ መሆን እና እንደ እሳት የሚፋጀው ሙቀት ተፅእኖ እንዳሳደረባቸው ነው የገለጹት፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here