በእግር ኳሱ ዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአውሮፓ እና በሌሎች አብዛኞቹ ሀገራት የተጫዋች ዝውውር የሚፈፀመው በክረምት እና በጥር ወቅት ነው:: የጥር የተጫዋቾች ዝውውር ወቅት ክለቦች የቡድናቸውን ክፍተት ወይም ቀዳዳ ለመሸፈን የሚጠቀሙበት በውድድር ዓመቱ አጋማሽ የሚከናወን ዝውውር ነው:: ይህ የዝውውር ወቅት ለአንድ ወር ብቻ የሚቆይም ነው::
በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ወቅት ግን ክለቦች አዲስ እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ የሚነድፉበት፣ እንደገና ቡድናቸውን የሚያደራጁበት እና ለዝውውር በርካታ መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱበት በመሆኑ በርካታ ተጫዋቾች የሚዘዋወሩበት ወቅት ነው:: ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በአምስቱ ታላላቅ ሊጎች የሚገኙ ክለቦች የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች ያስኮበልላሉ:: ተጫዋቾችም ህልማቸውን ለመኖር ህልማችን ናቸዉ ወደሚሏቸው ክለቦች መዳረሻቸውን ያደርጋሉ::
በአንድ ወቅት ጥቂት የነበረው የእግር ኳስ ተጫዋቾች የዝውውር ክፍያ እያደገ ሄዶ ስፖርቱ አሁን ላይ በቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ ሆኗል። በጥቂት ክፍያ የጀመረው የተጫዋቾች ዝውውር አሁን ላይ አስደንጋጭ የገንዘብ መጠን ላይ ደርሷል። በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጫዋቾች ዝውውር መደበኛ ያልሆነ እና እንደ ሥራ ዕድል ፈጠራ ነበር የሚታየው።
ይሁን እንጂ ዘርፉ ወደ ፕሮፌሽናልነት ሲያድግ በተደራጀ መንገድ መመራት ጀምሯል። እ.አ.አ በ1885 የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር የተጫዋቾችን ዝውውር ሕጋዊ እንዲሆን አዲስ ሕግ ካፀደቀ በኋላ በዝውውሩ አዲስ አብዮት ተፈጥሯል። እ.አ.አ በ1893 የመጀመሪያው ሕጋዊ የተጫዋቾች ዝውውር የተከናወነበት ጊዜ ነው። የዌስትብሮም አልቢዮኑ ተጫዋች ዊሊ ግሮቭ ወደ አስቶንቪላ ያቀናበት ዝውውር በእግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው ዝውውር ሆኖ በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል።
በወቅቱ ሀብታም ክለብ የነበረው አስቶንቪላ ለዝውውሩ መቶ ዶላር ወጪ ማድረጉንም ታሪክ ያስታውሰናል። በዚህ ገንዘብም ብዙ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ወጪው ተጋኗል በሚል መደንገጣቸውንም ጭምር መረጃው ይነግረናል። በ1905 እ.አ.አ ደግሞ ይህ ገንዘብ በአስር እጥፍ አድጎ አንድ ሺህ ዶላር ደርሷል። አልፍ ኮመን ከሰንደርላንድ ወደ ሚድስብራው ሲዘዋወር በወቅቱ የእንግሊዝ ከፍተኛ የተባለው ገንዘብ ወጥቶበታል።
አሁን ላይ የተጫዋቾች የዝውውር ዋጋ ሰማይ ነክቷል። በየዝውውር ወቅቱ አዳዲስ የክብረ ወሰን ዋጋዎችን መስማትም እየተለመደ መጥቷል። በመቶ ዶላር የተጀመረው የእንግሊዝ የተጫዋቾች ዝውውር አሁን ላይ መቶ ሚሊዮኖች ላይ ደርሷል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በእንግሊዝ የወቅቱ የተጫዋቾች ዝውውር ክብረ ወሰን 116 ሚሊዮን ፓውንድ ነው። የአውሮፓ ደግሞ 200 ሚሊዮን ፓውንድ መሆኑን የቢቢሲ መረጃ ያስነብባል።
በተለያየ መንገድ የእግር ኳስ ክለቦች ገቢ መጨመር፣ የቦስማንን ሕግ ተከትሎ የተጫዋቾች መብት እና ስልጣን ከፍ ማለት፣ የወኪሎች ሚና መጨመር፣ አዳዲስ የክለብ ባለሀብቶች መምጣት፣ በክለቦች መካከል ያለው ፉክክር ማደግ እና ሌሎችም ምክንያቶች በየጊዜው የተጫዋቾች ዝውውር ዋጋ እንዲጨምር አድርጎታል። በአውሮፓ የምንጊዜም ውዱ ዝውውር የተፈጸመው እ.አ.አ በ2017 ነው። ፓሪሴን ዥርሜን ኔይማር ጁኔርን ከባርሴሎና በ200 ሚሊዮን ፓውንድ ያስፈረመበት ዋጋ እስካሁን የፕላኔታችን ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። የፓሪሱ ሀብታም ክለብ ክሊያን ምባፔን ከሞናኮ ያስፈረመበት ዋጋም ሁለተኛው ውዱ ዝውውር ነው። የፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ ለምባፔ ዝውውር 165 ሚሊዮን ፓውንድ ማውጣቱን መረጃዎች አመልክተዋል።
ቸልሲ ስፔናዊውን ግብ ጠባቂ ኬፓ አሪዛብላጋን ከአትሌቲክ ቢልባኦ በ71 ሚሊዮን ፓውንድ ያስፈረመበት ዋጋ በግብ ጠባቂዎች ቦታ እስካሁን የዓለማችን ክብረ ወሰን ነው። በ2019 እ.አ.አ ማንቸስተር ዩናይትድ ሀሪ ማጎየርን ከሳውዝ አምፕተን ያስፈረመበት 80 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብም ከተከላካዮች ውዱ ዝውውር መሆኑን ቢቢሲ ያስነብባል። አርጀንቲናዊው አማካይ ኤንዞ ፈርናንዴዝ ከቤኔፊካ ስታንፎርድ ብሪጅ ሲደርስ 107 ሚሊዮን ፓውንድ እንደወጣበት አይዘነጋም። ታዲያ ይህ ገንዘብ ከጨዋታ አቀጣጥይ ተጫዋቾች ውስጥ እስካሁን ትልቁ ዝውውር ሆኖ ተመዝግቧል።
ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልኩ ከተዋቀረ በኋላ እ.አ.አ በ1992 አለን ሽረር ከሳውዝ አምፕተን ወደ ብላክብረን ሮቨርስ ሲያቀና ክብረ ወሰን የሆነ ዋጋ ወጥቶበታል። ብላክብረን ሮቨርስ ሦስት ሚሊዮን 600 ሺህ ፓውንድ ገንዘብ አውጥቷል። ብላክበረን ሮቨርስ ለመጨረሻ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያሳካ በአለን ሽረር ምትሀተኛ እግሮች በመታገዝ ነበር። አለን ሽረር በፕሪሚየር ሊጉ 260 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የምንጊዜም ቀዳሚ ተጫዋች ነው።
ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ የአለን ሽረርን የዝውውር ክብረ ወሰንን ክሪስ ሱተን አሻሽሎታል። ክሪስ ሱተን ከኖርዊች ሲቲ ወደ ብላክበርን ሮቨርስ ሲያቀና አምስት ሚሊዮን ፓውንድ ነበር የወጣበት። በዚህ መንገድ የተጀመረው የእንግሊዝ የተጫዋቾች ዝውውር ዋጋ አሁን ላይ መቶ ሚልዮንን ተሻግሯል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 116 ሚሊዮን ፓውንድ ደርሷል። በእንግሊዝ ምድር የዝውውሩ ባለክብረ ወሰን ተጫዋችም ጀርመናዊው አጥቂ ፍሎሪያን ዊርትዝ ነው። የ22 ዓመቱ አጥቂ በያዝነው የክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ወቅት ነው ከባየርሊቨርኩስን ወደ ሊቨርፑል ያቀናው። ለዚህ ወጣት ባለተሰጥኦ ቀዮች 116 ሚሊዮን 500 ሺህ ፓውንድ ወጪ አድርገዋል።
ይህም ከሦስት ዓመታት በፊት ልክ በዚህ ወቅት በሞይሴስ ካይሴዶ ተይዞ የነበረውን የዝውውር ክብረ ወሰንን ነው ጀርመናዊው አጥቂ ያሻሻለው። እ.አ.አ ነሐሴ 22 ቀን 2022 ኢኳዶራዊው አማካይ ሞይሴስ ካይሴዶ ከብራይተን ቸልሲን ሲቀላቀል አዲስ የእንግሊዝን የተጫዋቾች ዝውውር ዋጋ በመስብር ነበር። ቸልሲ በወቅቱ ለዝውውሩ 115 ሚዮን ፓውንድ ከፍሏል። የመሀል ሜዳው ሞተር እስካሁን በስታንፎርድ ብሪጅ 73 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ግቦችንም አስቆጥሯል።
የኮንፍረንስ ሊግ እና የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫዎችንም ማንሳቱ የሚታወስ ነው። እ.አ.አ በ2023 ቸልሲ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ክብረወሰን የሰበሩ ዝውውሮችን መፈጸሙ አይዘነጋም። ካይሴዶ ስታንፎርድ ብሪጅ ከመድረሱ ቀደም ብሎ በውድድሩ አጋማሽ በወርሀ ጥር ኤንዞ ፈርናንዴዝ ነበር በእንግሊዝ ውድ በሆነ የዝውውር ዋጋ ምዕራብ ለንደን የደረሰው። ቸልሲዎች አርጀንቲናዊውን አማካይ ከቤኔፊካ ሲስያስፈርሙ 106 ሚሊዮን 800 ሺህ ፓውንድ ገንዘብ አውጥተዋል።
ማንቸስተር ሲቲ እ.አ.አ ነሐሴ አምስት ቀን 2021 በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ውድ የተባለለትን ዝውውር የፈጸመበት ቀን ነው። ውኃ ሰማያዊ ለባሾች ለእንግሊዛዊው አጥቂ ጃክ ግሪልሽ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ በመክፈል ከአስቶንቪላ አስፈርመውታል። ግሪልሽ በፔፕ ጓርዲዮላ ስር 94 ጨዋታዎችን አከናውኖ 12 ግቦችን ብቻ ነው ያስቆጠረው። ነገር ግን አጥቂው የወጣበትን ገንዘብ ያህል በኢትሀድ ተጽእኖ መፍጠር አልቻለም። የጃክ ግሪሊሽ ዝውውር ማንቸስተር ሲቲ በታሪክ የከሰረበት ውዱ ዝውውር እንደሆነም በተደጋጋሚ ይነገራል።
ቤልጂየማዊው አጥቂ ሮሚዮ ሉካኩ በብዙ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ተጫውቷል። ከአምና ጀምሮ ደግሞ ለኔፕልሱ ክለብ ናፖሊ እየተጫወተ ይገኛል። የሠላሳ ሁለት ዓመቱ አጥቂ ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ አቅንቶ አልተሳካለትም። እ.አ.አ በ2021 ለመጀመሪያ ግዜ ከሀገሩ ክለብ አንደርሌክት ስታንፎርድ ብሪጅ የደረሰበት ጊዜ ነበር። ከሦስት ዓመታታ የምዕራብ ለንደን ቆይታ በኋላም ከክለቡ ጋር ተለያይቷል። በ2021 እ.አ.አ የክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ወቅት ግን በእንግሊዝ ምድር ከፍተኛ በሆነ ዋጋ ድጋሚ ወደ ቸልሲ ተመልሷል። ሰማያዊ ለባሾች ለዝውውሩ 97 ሚሊዮን 500 ሺህ ፓውንድ ማውጣታቸውንም መረጃዎች አመልክተዋል። ይሁን እንጅ አሁንም ሊሳካለት ባለመቻሉ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል።
ሌላው በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ከፈረሙት መካከል ፈረንሳያዊው አማካይ ፖል ፖግባ ነው። ፖግባ በ2012 እ.አ.አ ያደገበትን ማንቸስተር ዩናይትድን በመልቀቅ የጣሊያኑን ክለብ ጁቬንቱስን ተቀላቅሏል። ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ ድጋሚ ወደ ኦልትራፎርድ አምርቷል።
በዚህ ወቅት በእንግሊዝ የተጫዋቾች የዝውውር ታሪክ ወዱ ተጫዋች እንደነበረም የሚታወስ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ ለዝውውሩ 89 ሚሊዮን 300 ሺህ ፓውንድ ማውጣቱ ይታወሳል። ፖግባ ካልተሳኩ የስድስት ዓመታት የኦልትራፎርድ ቆይታ በኋላ ተመልሶ አሮጊቶችን ተቀላቅሏል። ጸረ አበረታች መድኃኒት ተጠቅሞ ከእግር ኳስ ታግዶ የነበረው ፖግባ አሁን ላይ በፈረንሳዩ ክለብ ሞናኮ ቤት ይገኛል።
ከኤርትራውያን ቤተሰቦቹ ስዊድን የተወለደው አሌክሳንደር ኢሳክ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሊቨርፑልን ለመቀላቀል እየተነጋገር ይገኛል። የሀያ አምስት ዓመቱ አጥቂ ኒውስካትል ዩናይትድን በመልቀቅ ሊቨርፑልን ለመቀላቀል ፍላጎቱን አሳይቷል። ሊቨርፑልም ለዝውውሩ 120 ሚሊዮን ፓውንድ መነሻ ገንዘብ አቅርቧል። ይሁን እጂ ኒውካስትል ዩናይትድ ከ150 ሚልዮን ፓውንድ ገንዘብ በታች እንደማይቀበል ዘ ሰን አስነብቧል። ምን አልባት ይህ ዝውውር እውን የሚሆን ከሆነ አሌክሳንደር ኢሳክ የወቅቱ የእንግሊዝ ውዱ ተጫዋች ይሆናል። በፍሎሪያን ዊርትዝ የተያዘው ክብረወሰንም ይሰበራል:: በሀገራችንም ቆሎ በመጋበዝ የተጀመረው የተጫዋቾች ዝውውር አሁን ላይ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ መሻገሩ ይነገራል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም