በመንግሥት  ክርክር የሚደረግባቸው ክሶች

0
109

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉ መንግሥት እና ተቋማቱ ተከራካሪ በሚሆኑባቸው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን እንዲሁም የሕዝብ እና የመንግሥት ጥቅም በያዙ የፍትሐብሄር ክርክሮች ላይ ለሚነሱ ቅሬታዎች እና ችግሮች መፍትሔዎችን ለማፈላለግ በችግሮቹ ዙሪያ ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በመንግሥት ተይዘው ክርክር በሚደረግባቸው ክሶች ላይ ብዙ የአሠራር ችግሮች እየገጠሙ እንደሆነ ነው የተጠቆመው፡፡ በክልሉ መንግሥት የተያዙ ክሶች ሲታዩ ሁሉም ተቋማት በተለይ የፍትሐብሄር ጉዳዮችን  በሚመለከት የተያዙ ክሶች በአግባቡ ክርክር ስለማይደርግባቸው ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ እና የመንግሥታ ጥቅም እየታጣ መሆኑን   ነው፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰይፉ ሰይድ ጥናቱን መሰረት አድርገው እንደተናገሩት ከ80 ከመቶ በላይ የፍትሐብሄር ክርክሮች የመሬት ጉዳዮች መሆናቸውን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ እንደ ተቋም ፍርድ ቤቶች የሚጠይቋቸውን መረጃዎች በወቅቱ ከመስጠት  እና ማስረጃ አሟልቶ ከማቅረብ አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ማስተካከል እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

በየደረጃው ካሉ ፍርድ ቤቶች ጋር በሚደረጉ ክርክሮች በመንግሥት በኩል ቅሬታ እንደሚቀርብ  ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በዚህም የመንግሥት ተቋማት የመሠማት መብታቸው ሳይረጋገጥ በፍርድ ቤት በኩል ፍርድ እንደሚሰጥ እንዲሁም  በፍርድ አፈፃፀም ሂደት ደግሞ ተቋማቱ ይህንን ለመፈፀም ስለማይችሉ ለፍትሕ መረገጋጥ እንቅፋት  እንደሆኑ  አቶ ሰይፉ አንስተዋል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ፍርድ ቤቶች አንዱ የመንግሥት አካል ቢሆኑም ከመንግሥት ተቋማት ጋር በመተጋገዝ ሥርዓት ማስፈን አለመቻሉን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ የክልሉን ሕዝብ የፍትሕ አስተዳደር ማስተካከል ከተፈለገ የሚመለከታቸው ሕግ አውጭ፣ ተርጓሚ አና አስፈጻሚ አካላት በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አብራርተዋል፡፡

በመንግሥት ተቋማት በኩል ማስረጃ መዛባት ሲኖር የፍትሕ ሚዛን ትክክለኛ ማስረጃ በማቅረብ እንደ ተቋም የመንግሥት ክሶችን በቸልተኝነት  አቅርቦ አለማስረዳት እና ባለው ክርክር ፍርድ ቤት ሲወሰንበት ደግሞ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ  (ወደ ቀጣይ ፍርድ ቤት) ይግባኝ በማለት እስከ መጨረሻ በመከላከል በኩል ትልቅ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ጉዳይ   በቀጣይ እንዲስተካከል ማድረግ እንደሚገባ መገንዘባቸውን አቶ ሰይፈ ገልፀዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች ነፃ እና ገለልተኛ የመሆን ሕገ መንግሥታዊ መብት ስላላቸው ይህንን መብታቸውን ጥያቄ ውስጥ በማያስገባ መንገድ ያለአግባብ በሆነ ምክንያት እንዳይወስኑ ተጠቁሟል፡፡  በተለይ ጉድለቶችን ከዳኞች ሥነ ምግባር እና ሕጉን በአግባቡ ካለመገንዘብ የሚፈጠሩ የግንዛቤ ክፍተቶችን እንደ ፍርድ ቤት መሙላት እንደሚገባ በውይይቱ ተነስቷል፡፡

በመንግሥት የሚደረጉ የፍትሐብሄር ክርክሮች ከግንባታ (ኮንስትራክሽን) ፣ ከመሬት ዘርፍ፣ ከንግድ እና ኢንቨስትመንት ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው እነዚህን የሚያስተዳድሩ ሕጎች መኖራቸው ተነስቷል፡፡ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት የሚያገለግሉት ደግሞ ሕዝብን ስለሆነ ፍርድ ቤቶችም እንደተቋም ከማስረጃ አሰጣጥ ጋር፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ ከማስፈፀሚያ መመሪያ ጋር ተያይዞ በተለይም በቀበሌ፣ በወረዳ እና በከተሞች ደረጃ ያሉ አስተዳደሮች የፍርድ ቤት ትእዛዝን አለመፈፀም እንደሚስተዋል ተነስቷል፡፡  በተለይ በመሬት አስተዳደር መዋቅር ሥር ያሉ አንዳንድ ባለሙያዎች ትእዛዝን ያለመቀበል እና ማስፈፀም አለመቻል ችግር ስላለ ተከታትሎ የማረም ሥራ እንደሚጠበቅ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች ብቻቸውን የሚፈቱት ችግር ስለሌለ አሠራርን በማስተካከል በጋራ እየተመካከሩ ማረም እንደሚያስፈልግ  አቶ ሰይፈ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ መንገድ በጋራ ከተሠራ ደግሞ የሕዝቡ መልካም አስተዳዳር ችግሮች ይፈታል ሲሉ ነው የገለፁት፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳዳር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው ከተሞች ሀብታቸውን በአግባቡ መጠቀም ካልቻሉ የችግሩ እዳ ወደ ፊት ለሚመጣው   ትውልድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ከተሞች ያላቸው ሀብት መሬት በመሆኑ በአግባቡ ይዘው ለሕዝብ ልማት ከመጠቀም አኳያ የሚታዩ የማጭበርበሪያ መንገዶች ምንድን ናቸው? በሚለው ጉዳይ ዙሪያ   ከሕግ ተርጓሚው እና  ከአቃቢ ሕግ ጋር በምን መልኩ  መሥራት እንዳለባቸው ውይይት ተደርጓል፡፡

ሕግ ተርጓሚው አካል ደግሞ ገለልተኛ ተቋም ነው፤ ነገር ግን ከመንግሥት አካልም ስለሆነ የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት ከመጠበቅ አኳያ በተለይ ከተማ አስተዳደሮች እና ዞኖች አካባቢ ከቅርብ ጊዜያት  ወዲህ የማጭበርበር ወንጀል መልኩን ቀይሮ ከፍ ባለ ሁኔታ እየተፈፀመ  በመሆኑ የችግሩን ሥፋት ለማየት መሞከራቸውን ነው የገለፁት፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው በበኩላቸው መንግሥት ተከራካሪ በሆነባቸው የፍትሐ ብሄር ጉዳዮች አያያዝ እና በፍርድ ቤት በሚሰጡ ውሳኔዎች ዙሪያ በርካታ ቅሬታዎች እንደሚነሱ  አስታውሰዋል፡፡ ቅሬታዎቹን የሚያቀርቡት በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት መሪዎች እንደሆኑም ጠቁመዋል። አብዛኛዎቹ ቅሬታዎች በፍትሐ ብሄር ፍትሕ አሥተዳደር ሂደቱ የተለያዩ አካላት ያላቸውን ሚና በውል ባለመገንዘብ የሚቀርቡ መሆናቸውንም  ነው፡፡

የፍርድ ቤት ሚና ሕግ እና ማስረጃን መሠረት አድርጎ በገለልተኛነት የመዳኘት እንጅ በክርክር ሂደት በመንግሥት በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን እየሞላ የመሄድ አለመሆኑን በውል መገንዘብ እንደሚገባም አመላክተዋል። የመንግሥትን እና የሕዝብን ጥቅም ማስከበር የየተቋማቱ መሪዎች ዋነኛ ተግባር ስለመሆኑም መገንዘብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በመሆኑም የመንግሥት ተቋማት በፍትሐብሄር ክርክሮች የሕዝብ እና የመንግሥትን ጥቅም ሊያስከብሩ የሚችሉት ተገቢውን ማስረጃ በወቅቱ በማቅረብ እና የሚከሱባቸውንም ሆነ የሚከሰሱባቸውን ጉዳዮች በአግባቡ በመምራት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል። የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በይግባኝ እስካልተሻሻሉ ድረስ  የፍርድ ባለዕዳ የሆነ ተቋም የተወሰነበትን ውሳኔ ቢያምንበትም ባያምንበትም የግድ መፈጸም እንዳለበት አቶ ዓለም አንተ ተናግረዋል።

የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን አለመፈጸም ደግሞ ሕግን ከመጣስ ባለፈ የመንግሥትን ሥርዓት የሚያናጋ እና ሥርዓት አልበኝነትን የሚያመጣ ስለመሆኑም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡  ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ያስፈለገውም ክፍተቶችን በጋራ ለመሙላት ታስቦ እንደሆነ ጠቁመዋል።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሰኔ 30  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here