የሁለት ሺህ አስራ ስምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከመቼውም ጊዜ በተለየ መንገድ ነው የተጀመረው:: የክለቦች ቁጥር ወደ 20 ማደጉ እና የዝውውር ገበያው የፈጠረው አዲስ ስሜት ለሊጉ ልዩ ድባብ ሰጥቶታል። በዚህ ፈታኝ የውድድር መድረክ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከሚጠበቁ እና የቀደመ ጠንካራ ተፎካካሪነታቸውን ለማስቀጠል ከሚታገሉ ክለቦች መካከል ባሕር ዳር ከነማ አንዱ ነው። የጣናው ሞገድ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ወይም ሦሰተኛ ደረጃ ላይ እየተቀመጡ ማጠናቀቁ አይዘነጋም:: በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን በመወከል ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የተሳተፈው የጣናው ሞገድ ዘንድሮስ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል? የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ስብስብ በመጀመሪያዎቹ ሰባት ሳምንታት ያሳየው ጉዞ ወደ ዋንጫ የሚያስጠጋ ነው? ወይስ የማንቂያ ደወል የሚፈልግ ነው?
ባሕር ዳር ከነማ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፏል፤ በሁለት ጨዋታ ሲሸነፍ፣ በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል:: ይህ መረጃ አስከተጠናቀረበት የስምንተኛ ሳምንት መርሀግብር ድረስ በድምሩ 12 ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል:: ስምንት ግብ ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችም ተቆጥረውበታል:: ምንም እንኳ ይህ ውጤት ባለፉት ሦስት ዓመታት የሊጉ ዋነኛ ተፎካካሪ ለነበረ ክለብ ደካማ ውጤት ቢመስልም በመጀመሪያዎቹ ጥቂት የሊጉ ሳምንታት እንደዚህ ዓይነት ውጤት ማስመዝገብ ግን ለክለቡ እንግዳ አይደለም::
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት የሊጉ ስምንተኛ ሳምንት ድረስ በድምሩ 12 ነጥቦችን በመሰብሰብ በሊጉ 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ለብዙዎች “ቀዝቃዛ አጀማመር” ሊመስል እንደሚችል ይገመታል:: የመጀመሪያዎቹን አምስት ሳምንታት ብቻ ስንመለከት በያዝነው የውድድር ዓመት ባሕር ዳር ከነማ ስድስት ነጥቦችን መሰብሰቡ የሚታወስ ነው:: ይሁን እንጂ ይህ ቁጥር ከ2016 እና 2017 የውድድር ዓመታት አጀማመር ጋር ሲነጻጸር ተመሳሳይ መሆኑን ቁጥሮች ይመሰክራሉ:: የጣናው ሞገድ በ2016 ዓ.ም ሰባት ነጥብ መሰብሰቡ አይዘነጋም:: በ2017 ዓ.ም ደግሞ ልክ እንደ ዘንድሮው በስድስት ነጥብ ነበር የጀመረው:: እናም ባሕር ዳር ከተማ በሊጉ አጀማመሩ ዘገምተኛ (Slow Start) ባህሪ ያለው በመሆኑ ደጋፊዎች፣ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኙ የቡድኑ አባላት ሊደነግጡ እንደማይገባ ነው ቁጥሮች የሚያስረዱት::
የተለመደ አጀማመር በመሆኑ የቡድኑ ስነ-ልቦናውም መጎዳት እንደሌለበት ቁጥሮች ይመሰክራሉ:: ታዲያ ቡድኑ ባልተለመደ ቀውስ ውስጥ እንዳልሆነ በመረዳት መረጋጋት እንዳለባቸው ተገቢ መሆኑን ከመረጃዎች መገንዘብ ይኖርበታል:: ይሁን እንጂ የዘንድሮው ፉክክር ከባለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ እንደሚለይ መዘንጋት የለበትም:: እንደ ሲዳማ ቡና እና መቻል ያሉ ክለቦች የሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ዘንድሮ ብቅ ብለዋል::ምንም እንኳ ውድድሩ ገና ስምንተኛ ሳምንት ላይ ቢሆንም ክለቡ በፍጥነት የማሸነፊያ መንገዱን ካላገኘ ለዋንጫ በሚያደረገው ፉክክር ከመሪዎች ጋር የሚኖረው ልዩነት ሊሰፋ ይችላል::
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አሰልጣኞችን መቀያየር ፋሽን እስኪመስል ድርስ እየተለመደ ምጥቷል:: ባሕር ዳር ከነማ ግን ከአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጋር መቆየቱ ትልቁ ጥንካሬው ነው:: የአሰልጣኙ በክለቡ ውስጥ መቆየቱ በቡድን ግንባታው ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል፤ እያሳረፈም ይገኛል። በዘንድሮው ስብስብ ልምድ ያላቸው እና የወጣት ተጫዋቾች እንዲሁም የነባር እና የአዳዲስ ተጫዋቾች ውህደትን እየተመለከትን ነው:: የተከላካይ መስመሩ በስምንት ጨዋታ ስድስት ግብ የተቆጠረበት የኋላ ክፍሉ ከዚህ የተሻለ ጥንካሬ እንደሚጠበቅበት ከአሚኮ ስፖርት ጋር ቆይታ ያደረገው የዘርፉ ባለሙያ አቶ አብርሃም መላኩ ተናግሯል::
ባሕር ዳር ከነማ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ስምንት ግብ ብቻ ማስቆጠሩ በፊት መስመሩ ላይ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል:: አማኑኤል ገብረሚካኤልን የመሰለ ልምድ ያለው አጥቂ ይዞ እንዴት ግብ ይጠፋል? የሚል ጥያቄ ይነሳል። ባሕር ዳር ከነማ እየተጫወተ ያለው በቡድን የማጥቃት (Group Play) ታክቲክ ነው። ግቦቹ የሚመጡት ከአንድ አጥቂ ብቻ አይደለም። በርካታ ግቦች የተቆጠሩት በተለያዩ ተጫዋቾች መሆኑ ቡድኑ በአንድ ተጫዋች ላይ ጥገኛ አለመሆኑን እንደሚያመላክት ባለሙያው ያስረዳል::
በአሰልጣኝ ደግአረገ ዕይታ የገቡ አዳዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን ቀይረውታል። በተለይ ከከፍተኛ ሊጉ የተገኘው ማንያዘዋል እና ክንዴ ባየልኝ ያሳዩት ብቃት አስደናቂ መሆኑን አቶ አብርሃም ይናገራል:: “ማንያዘዋል ለሊጉ አዲስ ቢሆንም ሜዳ ላይ የሚሰጠው አገልግሎት ግን የረጅም ጊዜ ልምድ እንዳለው ተጫዋች ነው። በረከት ጥጋቡም ቢሆን አሁን ባለው ብቃት ለብሄራዊ ቡድን ጭምር ጥሪ ሊደረግለት የሚገባ ትክክኛ እድሜ እና አቋም ላይ ይገኛል” ብሏል ባለሙያው:: የዘንድሮው የባህር ዳር ከነማ ልዩነት በጉልህ የሚታየው በሁለተኛው የሜዳ ክፍል መሆኑን እስካሁን በነበረው መርሀግብር ተመልክተናል:: እናም የመሀል ሜዳው ጥንካሬ ቡድኑ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት በሚያደርገው ጥረት ወሳኝ መሆኑን የእግር ኳስ ባለሙያው ተናግሯል::
ዘመናዊ እግር ኳስ ኃላፊነትን ለሁሉም የሚሰጥ ነው፤ አጥቂው መከላከል አለበት፤ ተከላካዩ ማጥቃት አለበት። ባሕር ዳር ከነማ ደግሞ ይህንን በሚገባ ተረድቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል:: በተለይ ቡድኑ ከቆሙ ኳሶች (Set pieces) ግብ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት በልምምድ የተቀረጸ የታክቲክ ውጤት መሆኑን አቶ አብርሃም ይመሰክራል:: የዘንድሮው የባሕር ዳር ከነማ መለያው እስከ መጨረሻው ሽርፍራፊ ሴኮንድ ያለው ተጋድሎ”(Fighting Spirit) ነው። ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ የሚያሳዩት የአልሸነፍ ባይነት እና የአሸናፊነት ስሜት የሚደነቅ እንደሆነም የእግር ኳስ ባለሙያው ተናግሯል::
ጨዋታን በሚቆጣጠሩበት ጊዜም ሆነ ጫና ውስጥ በሚገቡበት ወቅት የሚወስዱት ታክቲካዊ እርምጃ የብስለታቸው ማሳያ እንደሆነም ተነግሯል:: ታዳጊዎች አሰልጣኙ የሰጣቸውን መመሪያ ቅድሚያ ሰጥተው ለመተግበር የሚያደርጉት ጥረት የታክቲክ ዲሲፕሊናቸውን ያሳይል፤ ቡድኑ ለእያንዳንዱ ጨዋታ የተለየ ዝግጅት እና ስልት ነድፈው እንደሚገቡ የቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያመለክታል ነው ያለው የእግር ኳስ ባለሙያው አቶ አብርሃም::
የጣናው ሞገድ ልክ እንደ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን የወጥነት (Consistency) ችግሩን መቅርፍ እንደሚኖርበት ባለሙያው ይጠቁማል:: ቡድኑ በአንድ ጨዋታ ያሳየውን ድንቅ አቋም በቀጣዩ ጨዋታ ለመድገም ሲቸገር ይስተዋላል:: እናም ቡድኑ በተከታታይ የማሸነፍ ባህል ሊኖረው ይገባል- የአቶ አብርሃም አስተያየት ነው:: ዓመቱን በፌሽታ ለመጨረስ የማጥቃት ሂደቱንም በተጋጣሚ ሜዳ ላይ (Final Third) የማጠናቀቅ ወጥነት ላይ መስራት ይጠበቅበታል ተብሏል።
ቡድኑ በተወሰኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ላይ ጥገኛ የመሆን ምልክቶችን እያሳየ ይገኛል:: እንደ ወንድሜነህ፣ በረከት እና አማኑኤል ያሉ ተጫዋቾች በጉዳት ወይም በቅጣት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ ቢሆኑ እነሱን ተክቶ የሚገባው ተጫዋች አቅሙ ምን ያህል ነው? የሚለው የብዙዎች ስጋት ነው:: ታዲያ የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቡድን የተጫዋቾችን የመጫወት ደቂቃ እና የቅያሪ አማራጮችን በጥንቃቄ ማስተዳደር እንዲሁም ተተኪዎችን ማብቃት ያስፈልገዋል:: የጨዋታ ማኔጅመንት (Game Management) በክለቡ ውስጥ የታየ ሌላኛው ችግር ሲሆን በፍጥነት ካልተስተካከለ ወሳኝ በሆኑ ጨዋታዎች ላይ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ይገመታል:: እንደ አቶ አብርሃም መላኩ እምነት ባሕር ዳር ከነማ ዘንድሮ ለዋንጫ ከሚፎካከሩት ክለቦች አንዱ ብቻ ሳይሆን ዋንጫውን የማንሳት ሰፊ እድል ያለው ቡድን ነው::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


