ሀገራችን በየጊዜዉ የሚገጥማትን የሰላም መደፍረስ እና የጸጥታ ችግር የምትፈታበት ባሕላዊ የእርቅ ስነ ሥርዓት ባለቤት ናት። እነዚህ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚኖራቸዉ አበርክቶ ከፍ ያለ እንደሆን ይታወቃል።
ሀገራችን ቀደም ካሉት ባሕላዊ የግጭት ማስወገጃ መንገዶች በተጨማሪ በቅርቡ ደግሞ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገች ነው።
በሀገራችን በተለያየ ወቅት የተከሰተዉ የሰላም መደፍረስ ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት፣ ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት፣ ማሕበራዊ ምስቅልቅል እና ስነ ልቦናዊ ጫና ማስከተሉ የአደባባይ ሃቅ ነዉ። ይህንኑ ችግር ያጤነችዉ ኢትዮጵያም ውስጣዊ ችግሮቿን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያስችላት ዘንድ ካላት ሀገር በቀል የእርቅ አፈታት ዘዴ በተጨማሪ የተለያዩ የሰላም አማራጮችን እና ጥረቶችን ስታካሄድ ኖራለች። ለዚህ እንደ ማሳያ የሚጠቀሰውም በቅርቡ የተደረገዉ የፕሪቶሪያ ስምምነት አንዱ ነው። ይህ ስምምነትም የሰሜኑ ጦርነት እንዲያበቃ ያስቻለ የሰላም ጥረት ነው።
የሰሜኑን ጦርነት ለማስቆም ከተፈረመዉ የፕሪቶሪያው ስምምነት ባሻገርም ኢትዮጵያ ላጋጠማት ዘርፈ ብዙ ቀውስ መፍትሔ ያመጣ ዘንድ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ወደ ምክክር ተገብቷል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መድረክ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መምጣት ችግሮችን እየለየ ቆይቶ መጋቢት 2017 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ደግሞ በአማራ ክልል ከሁሉም የማሕበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የአጀንዳ ልየታ አከናውናል። እነዚህ ተሳታፊዎችም
አጀንዳዉን ከመለየት ባሻገር ሀሳቤን እስከመጨረሻዉ ያደርሱልኛል ያላቸዉን ወኪሎቻቸዉን በመምረጥ አጠናቀዋል።
የአማራ ሕዝብ የወሰን እና የማንነት ጥያቄን ጨምሮ እንዲመለሱለት የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያነሳ ቆይቷል። በመሆኑም የምክክር ኮሚሽኑ አማራ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ጨምሮ ሀገራዊ ችግሮችን በመለየት ስር ነቀል መፍትሄ ለመስጠት እያከናወነ ያለው ሂደት መልካም ዕድል በመሆኑ እንዲሁም ለሁሉም እኩል ዕድል የሚሰጥ እንዲሁም ነጻ ውይይትን የሚከተል በመሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ተሳታፊ ዕድሉን መጠቀም ይኖርበታል።
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮች ዜጎችን ለችግር እያጋለጡ በመሆናቸው የችግሮች ማብቂያ ጊዜ ደግሞ አሁን መሆን አለበት። ለዚህም ደግሞ ምክክር ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ይህን ዕድል መጠቀም ለነገ የማይተዉ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው።
ኢትዮጵያዊያን በርካታ የፖለቲካ፣ የታሪክ እና የኢኮኖሚ ችግሮችን በጋራ እያሳለፍን በሀገራችን ጉዳይ ሳንደራደር ዘመናትን አስቆጥረናል። በሀገራችን ጉዳይ በአንድነት ለመዝመት እና ለመዋጋት እንደምንደፍረዉ ሁሉ አሁን ደግሞ በሰከነ መንገድ አንዱ ያንዱን ቁስል፣ ችግር፣ ስጋት እና ተስፋ ለማዳመጥ እና ለመደማመጥ የምንደፍርበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን። ለኢትዮጵያውያን ሕመም እና ቁስል ፈውስ ልናመጣ የምንችለውም እኛው ኢትጵያዊያን ነን በማለት ያስገነዘቡት የኢትጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽነር አምባየ ኦጋቶ (ዶ/ር) ናቸው።
በምክክር የማይነሳ ቅሬታ፣ ፍላጎት እና ችግር ስለማይኖር በሕዝብ ውክልና የተሰጣቸዉ ወኪሎችም የተለዩ ችግሮችን እና ጥያቄዎችን ሳይሸራረፉ በማቅረብ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያስገኙ አደራ ተሰጥቷቸዋል።
ምክክር የአንድ ወገን ሀሳብ ብቻ የሚወሰድበት ሳይሆን በየደረጃዉ ያለዉ ሁሉም አካል ያለምንም ፍርሃት እና ስጋት ለሀገር ይበጃል ያለውን አጀንዳ የሚያዋጣበት የሰላም መንገድ በመሆኑ ሁሉም ተወካይ ይህንን ሃሳብ በመረዳት ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይኖርበታል።
“ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ”፣ “አንድ አይፈርድ አንድ አይነድ” … የሚሉ አባባሎቻችን የሚነግሩንም በማንኛውም መንገድ ቢሆን ሕብረት፣ አንድነት እና መመካከር መፍትሄ አመላካች ርምጃ መሆኑን ነው። ሀገር የምትቆመው እና የምትረጋጋውም በምክክር፣ በውይይት፣ በይቅርታ እንዲሁም በእርቅ በመሆኑ ሀገራችን ለገጠማት ውስብስብ ችግር በጋራ በመሰባሰብ እና በመመካከር ችግሮችን ልንለይ እና ለችግሮችም መፍቻ ሀሳቦችን በማዋጣት ሀገራችንን ከገባችበት የግጭት አዙሪት አውጥተን ወደ ሰላም ማሻገር ይኖርብናል፡፡
በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም