በተማሪ ምዝገባ ማሳካት ያልተቻለውን በውጤት ማካካስ ወቅታዊ አንኳር የትምህርት ሥራ ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 ዓ.ም መዝግቦ ለማስተማር ዕቅድ ይዞ የነበረው ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎችን ነው፡፡ ቢሮዉ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማውን ከምእራብ ጎጃም፣ አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ ከሰሜን ጎጃም ዞን፣ ከደቡብ ጎንደር ዞን፣ ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ከደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ገምግሟል፡፡ በመድረኩ እንደተገለጸው አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው፡፡ ተመዝግበው በትምህርታቸው ላይ ካልተገኙት ውጭ በትምህርት ላይ ይገኛሉ የተባሉት ደግሞ ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ እንደሆኑ ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል፡፡ ሲማሩ የከረሙ ተማሪዎችን በማብቃት ሁሉንም ወደቀጣዩ የክፍል ደረጃ ማሸጋገር፣ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሰጥተው ማሳለፍ የማይችሉ ትምህርት ቤቶች እንዳይኖሩ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
በ2016 ዓ.ም ከትምህርት እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ወጥቶ የቆየው የምዕራብ ጎጃም ዞን በዚህ ዓመት 79 ትምህርት ቤቶቹን ከፍቶ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ የመምሪያ ኃላፊዉ የሥጋት ደሴ 521 ትምህርት ቤቶች አሁንም ሳይከፈቱ 2018 ዓ.ም እንዲጠብቁ መሆናቸውን በግምገማ መድረኩ በተገኙበት ወቅት አስታውቀዋል፡፡ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዓመታዊ የተማሪ ቅበላ ዕቅድ 396 ሺህ 549 የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በትምህርት ላይ የሚገኙት 37 ሺህ 168 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡
እንደ አቶ የሥጋት የምዕራብ ጎጃም ዞን በተማሪ ምዝገባ ያጣውን በውጤት ለማካካስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም በዓመቱ በስድስተኛ ክፍል አንድ ሺህ 792፣ በስምንተኛ ክፍል አንድ ሺህ 934 እና በ12ኛ ክፍል አንድ ሺህ 233 ተማሪዎችን ያስፈትናል፡፡
ባለፈው ዓመት አንድ ትምህርት ቤት ብቻ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ያስፈተነው የሰሜን ጎጃም ዞን በዚህ ዓመትም 418 ትምህርት ቤቶቹን አልከፈተም፡፡ እንደ ዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ነጋልኝ ተገኘ በመማር ማስተማር ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ቁጥር 85 ናቸው፡፡
በዓመቱ በሁሉም የትምህርት ተቋማት መዝግቦ ለማስተማር የተያዘው ዕቅድ 448 ሺህ 939 ተማሪዎችን ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በማስተማር ላይ የሚገኙት ግን 44 ሺህ 600 ተማሪዎች ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡
ምንም እንኳ 404 ሺህ 339 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው 2018 ዓ.ም እንዲጠባበቁ ቢሆኑም በትምህርት ላይ ያሉትን በማብቃት ዓመቱን በድል እንዲያጠናቅቁ የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ መሆናቸውን አቶ ነጋልኝ አስታውቀዋል፡፡ በዞኑ በስድስተኛ፣ ስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ከአራት ሺህ በላይ ተማሪዎች ይፈተናሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የዩኒቨኒርሲቲ መግቢያ ፈተና የሚወስዱ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም እና የሰሜን ጎጃም ዞኖችን ጨምሮ በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ባለድርሻ አካላት በምን አይነት መንገድ ተማሪዎችን ለማብቃት እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የእያንዳንዱን የትምህርት ይዘት በአግባቡ መሸፈን፣ ያልሸፈኑትም በወቅቱ እንዲሸፍኑ ቁጥጥር እና ክትትል እያደረጉ ናቸው፡፡ የማጠናከሪያ ትምህርትን በተጠናከረ መንገድ እየተሠጠ ነው፡፡ ያለፉ ይዘቶችን መከለስ፣ ያለፉ ዓመታትን የፈተና ጥያቄዎች መሥራት፣ መምህራንም ፈተናው ትኩረት ያደርግበታል በሚሏቸው ይዘቶች ላይ ጥያቄዎችን እያዘጋጁ በመሥጠት ይበልጥ እንዲዘጋጁ እያደረጉ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች የሳምንቱን የእረፍት ቀናት እና የምሳ ሰዓትን ጨምሮ የአዳር ጥናት እያካሄዱ ተማሪዎቻቸውን በሚገባው ልክ እያበቁ ነው፡፡ ቤተ መጻሕፍት ቤቶችን በአጋዥ መጻሕፍት ማሟላት እና የመማሪያ መጻሕፍትን አንድ ለአንድ ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራም ነው ብለዋል፡፡
ለ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ፈተናው ከስንተኛ ክፍል ጀምሮ እንደሚወጣ የማሳወቅ ሥራ መሠራቱም ተመላክቷል፡፡ በዚህም ተማሪዎች ከዘጠነኛ ክፍል ነባሩን፤ ከአሥረኛ፣ አሥራ አንደኛ እና 12ኛ ክፍል ደግሞ የአዲሡን ሥርዓተ ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲዘጋጁ እየተደረገ ነው፡፡
ሥነ ልቦና ግንባታ ላይ በትኩረት መሥራት ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ጉልህ አበርክቶ እንደሚጫወት የመምሪያ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡ ተማሪዎች በእስካሁን ጉዟቸው ስጋት ውስጥ ናቸው፣ የሚሰሙት እና በዐይናቸው ያዩት የተረጋጋ ስነ ልቦና እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡ ለዚህም ከወዲሁ ትምህርታቸው ላይ እና በቀጣይ በሚወስዱት ፈተና ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ ሥነ ልቦና ግንባታ ላይ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል፡፡
አቶ የሥጋት ደሴ ትምህርት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በቀጣይ ዓመታት ላይ ምን ውጤት ሊያሳርፍ እንደሚችል መገመት እንደማይከብድ ገልጸዋል፡፡ ችግሩ የአማራ ክልል ጭራ እንዲሆን አድርጎታል ባይ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የክልሉ ዜጎች ከሀገራዊ ሐብት ተጠቃሚነት እንዲገቱ የሚያደርግ፣ ቀስ በቀስም ሀገሪቱን ወደ አለመረጋጋት የሚመራ በመሆኑ ጦሱ ከፍተኛ ይሆናል ይላሉ፡፡
አቶ የሥጋት “ባልተመጣጠነ ምግብ ትውልድ እንደሚቀነጭር ሁሉ በአስተሳሰብም የሚቀነጭር ትውልድ እንዲፈጠር መፍቀድ አይገባም” ሲሉ የችግሩን የነገ ውጤት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የቀነጨረ ትውልድ እንዳይፈጠር ማኅበረሰቡ ትምህርትን የነገ የኔ የተሻለ አገልግሎት ማግኛ መንገድ ነው ብሎ ሊጠብቀው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ትምህርት የማኅበረሰብን ድጋፍ ሲያገኝ የትምህርት ተሳትፎ እንደሚያድግ፣ ጥራትም እየተሻሻለ ሄዶ ችግር ፈቺ ትውልድ እንደሚፈጠር፣ ይህም ለሀገራዊ ሰላም እና መግባባት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው አቶ የስጋት እምነታቸው መሆኑን በማስመር ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችንም ከፖለቲካ የስበት ማዕከል ነጻ ማድረግ በትምህርት መድረስ ለሚቻለው ከፍታ መሠረት እንደሚሆን ያምናሉ፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ነጋልኝ ተገኘ በበኩላቸው ትምህርት ዋና መሠረቱ ሕዝብ ነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ጀምሮ ትምህርት ቤቶቹን እንደ ራሱ ሐብት እና ንብረት ቆጥሮ ለደኅንነታቸው ከለላ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
በዕውቀት እና በስነ ልቦና ዝግጁ የሆኑ ተማሪዎችን በመፍጠር የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ማፍራት የክልሉ የ2017 ዓ.ም ተጠባቂ ውጤት መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ እየሩስ መንግሥቱ ናቸው፡፡ ክልል ዓቀፍ እና ሀገር ዓቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ተወዳዳሪ እና ብቁ ለማድረግ የተጠናከረ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሁለት ሺህ 642 የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች 148 ሺህ 256 ተማሪዎቻቸውን ያስፈትናሉ፡፡ ሦስት ሺህ 551 ትምህርት ቤቶችም በዓመቱ መጠናቀቂያ የስድስተኛ ክፍል ፈተና የሚሰጡ ሆነው ተለይተዋል፡፡ 154 ሺህ 260 ተማሪዎች ደግሞ ተፈታኝ ናቸው፡፡
በ2017 ዓ.ም 470 የ12ኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች 99 ሺህ 880 ተማሪዎቻቸውን ያስፈትናሉ፡፡ ይህ ቁጥራዊ አኃዝ መደበኛ ተማሪዎችን ጨምሮ የግል፣ የማታ እና በርቀት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ተፈታኞች ጋር ሲነጻጸር በ21 ሺህ 339 ያነሰ ነው፡፡ እንደ ወይዘሮ እየሩስ ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 98 ሺህ 519 ተፈታኞች መካከል 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ስድስት ነጥብ ስድስት በመቶ ብቻ ናቸው፡፡
አምስት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ሁሉንም ተማሪዎቻቸውን ሲያሳልፉ፣ 64 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ እንዳላሳለፉ ተናግረዋል፡፡ የዚህ ዓመት ከፍተኛ የቅድመ ዝግጅት ሥራም ሁሉም ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ሁሉንም እንዲያሳልፉ፣ ተፈታኞችም የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ቀጣዩን የክፍል ደረጃ እንዲሸጋገሩ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ እየሩስ እስካሁን 415 ትምህርት ቤቶች የተደራጀ የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ 70 ሺህ 658 ተማሪዎች ደግሞ የማጠናከሪያ ትምህርቱን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡
የሥነ ልቦና የምክር አገልግሎት ለላቀ ውጤት አጋዥ ይሆናል ተብሎ እየተሠራበት እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ 338 ትምህርት ቤቶችም የሥነ ልቦና የምክር አገልግሎት መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ 63 ሺህ 283 ተማሪዎች የምክር አገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ አሁንም የሥነ ልቦና ድጋፍ የሚፈልጉ ተማሪዎች መኖራቸውን ያስታወቁት ወይዘሮ እየሩስ፣ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
86 ትምህርት ቤቶችም የአዳር ጥናት ማስጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡ አንዳንዶች ምግብ እና መኝታ አሟልተው አገልግሎቱን እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተሞክሮነት ሊወስዱት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ደቡብ ወሎ ዞንን በ17፣ ማዕከላዊ ጎንደርን በ11፣ ምዕራብ ጎንደርን በስምንት፣ አዊ ብሄረሰብ አስተዳደርን በስምንት… ትምህርት ቤቶች አብነት አድርገው ጠቅሰዋል፡፡
አሥር ዞኖች በተደራጀ መንገድ በሁሉም ትምህርት ቤቶቻቸው የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ እንደሚገኙ ወይዘሮ እየሩስ ሲያስታውቁ፣ በተሞክሮነት ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲወስዱት በመጠየቅም ጭምር ነው፡፡ ወልቃይት፣ ጎንደር ከተማ፣ ሰሜን ጎጃም፣ ኮምቦልቻ፣ ወልድያ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ደብረታቦር፣ ደብረ ማርቆስ እና ምዕራብ ጎንደር ዞን በአብነት አንስተዋል፡፡
ተማሪዎችን ከማብቃት ጎን ለጎንም ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የተናበበ የፈተና አስተዳደር ሥርዓት መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም