ሰማኒያ ከመቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መተዳደሪያ እና 40 ከመቶ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) አስተዋፅኦ ያደርጋል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ምርቶች ምንጭም ነው:: ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በቀዳሚነት ይነሳል – ግብርና::
ሀገሪቱ ለውጪ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች ውስጥ 80 ከመቶ የሚሆነው የሚሸፈነው ከግብርና ምርቶች መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በ2012 ዓ.ም የክልሉ የዘር ስርዓት ማሻሻያ ጥናት ባደረገበት ሰነድ ተረጋግጧል:: ጥናታዊ ሰነዱ ግብርና በአማራ ክልል ልዩ ትርጉም እንደሚሰጠው አመላክቷል:: ክልሉ በተለይ ለሰብል ልማት ተስማሚ የሆነ ሥነ-ምህዳር እና የአየር ንብረት፣ ውኃ፣ ሰፊ እና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት በመሆኑ በዋና ዋና የምግብ ሰብሎች የሀገሪቱን 33 በመቶ ምርት አስተዋጽኦ ያበረክታል:: በክልሉ ከሚመነጨው ኢኮኖሚ ውስጥ ግብርና ያለው ድርሻ ከ53 በመቶ በላይ መሆኑን ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
ታዲያ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገትን ለማምጣት የአመራረት ሂደቱን ማዘመን፣ ምርታማነትንም ለማሳደግ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በበቂ መጠን እና አይነት በማምረት መጠቀም፣ የአፈር ለምነት ማስጠበቂያ ግብዓት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ ይገባል:: ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ የምርታማነት መሠረቶች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባለመሆናቸው ዛሬም ሀገሪቱ ከእጅ ወደ አፍ አልፋ ለዓለም ገበያ በቂ እና ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ማቅረብ ተስኗት እየታየች ነው::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ የመጡ የሰላም እና ደኅንነት መናጋቶች ደግሞ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ፈተና እየሆኑ መጥተዋል። ለሰብል ልማት ምቹ የሆነው መሬት በዘር እንዳይሸፈን ከማድረግ ጀምሮ የተሸፈነውም በጦርነት ምክንያት ከጥቅም ውጪ መሆኑ፣ ግብዓትን ተደራሽ ለማድረግ የመንገድ መዘጋት… በዘርፉ ላይ ምን ያህል ተጽእኖ እያደረሱ ለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው።
ጦርነት (ግጭት) የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ምን ያህል እንደሚጎዳው በሰሜኑ ጦርነት የደረሰውን የምርት መቀነስ ብቻ ማየት በቂ ይሆናል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ጦርነት በተደረገባቸው ዘጠኝ ዞኖች ለሦስት ወራት ጥናት አድርጓል። ጥናቱ በክልሉ ያሉ የግብርና ምርቶች፣ የግብርና ቢሮዎች፣ የግብርና ምርምር ተቋማት፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲዎች እንዲሁም የእንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲዎችን ዳሷል:: ቢሮው ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጥናቱን አጠናቆ ይፋ አድርጓል:: በዚሀም ጦርነቱ በግብርና ዘርፉ ላይ 340 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ውድመት ማድረሱ በጥናት መረጋገጡን ሪፖርተር የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑትን አልማዝ ጊዜው (ዶ/ር) በመረጃ ምንጭነት ጠቅሶ በፈረንጆቹ የካቲት 6 ቀን 2022 ዘግቧል::
ትልቁ ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ስምምነት ተጠናቆ የደረሰውን ውድመት ለመመለስ ከፍተኛ የመልሶ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ቢሆንም አሁንም ግጭቶች አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መቀጠላቸው ግብርናው ከአጣብቂኝ እንዳይወጣ አድርጎታል:: የግጭቶች እልባት አለማግኘት አርሶ አደሩ ከቀየው እንዲፈናቀል እና ከምርት ውጭ ሆኖ እንዲከርም ያደርገዋል:: የተመረተውም በወቅቱ እንዳይሰበሰብ ከማድረግ በተጨማሪ የባሩድ ቀለብ እንዲሆኑ ያደርጋል። በሰብል ልማት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ደግሞ አምራች እጆች ለልመና እንዲዘረጉ እንደሚያደርግ በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ምስክር ናቸው::
ይህ ወቅት አርሶ አደሩ እረፍት የሚያጣበት፤ እርሻ የሚያርስበት፣ ያመረተውን ሽጦ የግብርና ግብዓት የሚያሟላበት ነው። ይሁን እንጂ አሁንም የግጭቶች አለመብረድ እና በተደጋጋሚ እየተስተዋለ የመጣው የመንገዶች መዘጋት አርሶ አደሩ እና የግብርናው ዘርፍ ለ2016/17 የምርት ዘመን እያደረጉት ያለውን የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ እንዳያስተጓጉሉት ተሰግቷል:: መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳያጋጥም፣ ግዥ የተፈጸመውም በወቅቱ ተጓጉዞ አርሶ አደሩ በሚፈልግበት ወቅት እንዲሰራጭ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል:: በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም መናጋት በአቅርቦት እና ስርጭቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረበት መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቋል:: በዓመቱ አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በዘር በመሸፈን 169 ሚሊዮን ኩንታል ክልላዊ ምርት ለማግኘት ታቅዷል:: ለዚህም በቂ የአፈር ማዳበሪ እና ምርጥ ዘር በወቅቱ ለማሰራጨት እየሠራ ቢገኝም የጸጥታ ችግሩ ግን አሁንም ፈተና እንደሆነበት አስታውቋል::
በኲር ጋዜጣም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን በማነጋገር የ2016/17 የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ቃኝታለች:: በአማራ ክልል በትርፍ አምራችነታቸው ከሚታወቁ አካባቢዎች መካከል የምሥራቅ ጎጃም ዞን አንዱ ነው:: በዞኑ የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ የቤዛ ብዙኃን ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ፍሬው ንብረቴ በዓመቱ ሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር ማሳን በበቆሉ፣ በጤፍ፣ በስንዴ እና ገብስ ለመሸፈን ማቀዳቸውን ለበኲር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል:: ማሳቸውን ከማጽዳት ጀምሮ ተደጋጋሚ እርሻ ሲያከናውኑ መቆየታቸውንም አስታውቀዋል::
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዘር ከሚሸፍኑት የማሳ መጠን ውስጥ ከራሳቸው የምግብ ፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚቀርብ ለማምረት የሚያስችሉ የግብርና ግብዓት ለማሟላት እየተሯሯጡ ይገኛሉ:: በአጠቃላይ በዘር ለሚሸፍኑት ማሳቸው 12 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና ሰባት ኩንታል ዩሪያ ያስፈልጋቸዋል:: ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት መጋቢት መገባደጃ ድረስ ያገኙት ግን አንድ ኩንታል ማዳበሪያ እና አንድ ኩንታል ዩሪያ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል:: ይህም ቀድመው ለሚዘሩት የበቆሎ ሰብል የሚውል ነው:: ቀሪውን ለማግኘት ሐሳብ እንደገባቸው አርሶ አደሩ ተናግረዋል::
የግብርና ግብዓት አቅርቦቱ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በዚህ ዓመት ቀድሞ መድረሱን፣ በዋጋም ቅናሽ መታየቱን ተናግረዋል:: ባለፈው ዓመት የማዳበሪያ እጥረት አጋጠሟል መባሉን ተከትሎ ግብዓቱ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ነጋዴ መግባቱ በሚፈለገው መጠን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸው እንደነበርም አስታውሰዋል:: ዘንድሮ ፍትሐዊ የግብዓት ክፍፍል መኖሩን አድንቀዋል:: በዋጋም ካለፈው ዓመት የተሻለ እና የአርሶ አደሩን አቅም ያገናዘበ ቢሆንም በጸጥታ ስጋቱ ምክንያት ግብዓቱ ካሉበት ቀበሌ ድረስ አለመድረሱ ግን ለተጨማሪ ወጪ እና የጉልበት ኪሳራ እንደዳረጋቸው ተናግረዋል::
ዘንድሮ የአፈር ማዳበሪያ ችግር እንደሌለ፣ ነገር ግን የተፈለገው መጠን በወቅቱ እንዳይደርስ የጸጥታ ችግሩ ፈተና መሆኑ በመንግሥት በኩል እየተገለጸ እንደሚገኝ አርሶ አደሩ ተናግረዋል:: በመሆኑም መንግሥት ለሰላም ልዩ ትኩረት በመሥጠት አቅርቦቱን በፍጥነት ተደራሽ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል:: የአፈር ማዳበሪያን ክረምት ከመግባቱ በፊት ማስገባት እና ማሰራጨት ካልተቻለ በየመንገዱ የሚፈጠረው ጎርፍ እና ጭቃ ተሽከርካሪን በማስተጓጎል ሌላ እክል ይዞ ሊመጣ እንደሚችልም ስጋታቸው መሆኑን ጠቁመዋል::
በባሕር ዳር ዙሪያ ጎንባት ቀበሌ ያነጋገርናቸው አንዳንድ አርሶ አደሮችም ለመጭው የመኸር ወቅት ግብዓት በመጠንም ሆነ በዋጋ ካለፈው ዓመት በእጅጉ መሻሉን ነግረውናል:: ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ለሕገ ወጥ ንግድ በመጋለጡ አርሶ አደሩ ለከፍተኛ ወጪ ተዳርጎ እንደነበር የሚያስታውሱት አርሶ አደሮቹ፣ ዘንድሮ እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ጊዜ ድረስ አንድ ኩንታል በሦስት ሺህ 930 ብር ገዝተዋል:: በጊዜም ቀድሞ መድረሱን ገልፀዋል::
የሁለት እጁነሴ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ዋሴ በስልክ እንደነገሩን በወረዳው ጤፍ፣ በቆሎ እና ስንዴ በስፋት ይመረታል:: በምርት ዘመኑ 36 ሺህ 424 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ይሸፈናል:: ከዚህም 1 ሚሊዮን 761 ሺህ 557 ኩንታል ምርት ይጠበቃል::
በዓመቱ ለማግኘት የታቀደውን ምርት ከእርሻ ጀምሮ ግብዓት የማሰራጨት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል:: ወረዳው በሰብል ለሚሸፍነው አጠቃላይ የማሳ መጠን 90 ሺህ 14 የማዳበሪያ (ኤን ፒ ኤስ) እና 68 ሺህ 446 የዩሪያ አቅርቦት ይፈልጋል:: እስከ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በሁለቱም የግብዓት አይነቶች 36 ሺህ 408 ኩንታል ቀርቧል:: ይህም የዕቅዱ 23 በመቶ ነው:: እስከተጠቀሰው ቀን ድረስ 33 ሺህ 708 ኩንታል መሰራጨቱን ኃላፊው ጠቁመዋል:: ስርጭቱ ጭነት እንደተራገፈ ወዲያው እየተሰራጨ መሆኑንም ጠቁመዋል::
አንድ ሺህ 748 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር መቅረቡን እና እስካሁን አንድ ሺህ 450 ኩንታል መሰራጨቱም ተመላክቷል::
የባለፈው ዓመት የግብዓት አቅርቦት እና ስርጭት እጅጉን መዘግየት የታየበት ከመሆኑም በላይ የቀረበውን ለአርሶ አደሩ ከማድረስ አኳያ የተስተዋለው ክፍተት አርሶ አደሩን ያስኮረፈ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል:: ችግሩ በ2016/17 የምርት ዘመን እንዳይቀጥል ግብርና ጽ/ቤቱ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከጸደይ ባንክ ሠራተኞች ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: የሰላም ችግሩ ግብዓት የማሰራጨት ሂደቱን እንደሚያስተጓጉለው ቢታመንም የማዳበሪያ ስርቆት ሌላ ፈተና ሆኖ ብቅ እንዳይል ወረዳው በትኩረት እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል::
በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ የመንገድ መዘጋቶች የግብርና ግብዓት በወቅቱ ከተፈለገው ቦታ እንዳይደርስ ከማድረጉ በተጨማሪ በየቦታው የሚጠየቀው ቀረጥ የግብዓት አቅርቦቱ ሌላው ፈተና መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል:: የሰላም እጦቱ ያስከተላቸው ችግሮች በግብዓት አቅርቦቱ ላይ የከፋ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ ቢሆንም አቅርቦቱ በጊዜም ሆነ በመጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል::
የተፈጠረው የሰላም እጦት ግብዓትን ቀበሌ ድረስ ወርዶ ለማሰራጨት እክል መፍጠሩን ኃላፊው ጠቁመዋል:: በአሁኑ ወቅት ስርጭቱ እየተከናወነ ያለው በሞጣ ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነው:: በእንደዚህ አይነት መንገድ ስርጭት ማከናወን ጫናው ከባድ መሆኑንም ኃላፊው አስታውቀዋል:: ይሁን እንጂ ከልማት የሚበልጥ ሥራ ባለመኖሩ የወረዳ አመራሩ ከወረዳ እስከ ቀበሌ ከሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ስርጭቱ በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል::
የክልሉ የሰላም ችግር አርሶ አደሩ ወደተሟላ የግብርና ሥራ እንዳይገባ፣ ያመረተውንም ወደ ገበያ እንዳያቀርብ እያደረገ በመሆኑ ማንኛውም ሰው የሆነ ሁሉ ለሰላም እንዲተጋ ጠይቀዋል::
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2016/17 የምርት ዘመን 112 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ22 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዶ እየሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን አስታውቀዋል:: ለግቡ ስኬትም ለሰብል የተለዩ ማሳዎችን በድግግሞሽ ማረስ፣ ምርጥ ዘር እና የማዳበሪያ በሚፈለገው መጠን በወቅቱ ተደራሽ ማድረግ ላይ አተኩሮ እየሠራ ነው:: በዓመቱ በሰብል ለሚሸፈነው የማሳ መጠንም አንድ ሚሊዮን 545 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ከዚህ ውስጥም 36 በመቶው ወደ ዞኑ ገብቷል። ከ450 ሺህ በላይ የሚሆነው ደግሞ አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች መሰራጨቱን አረጋግጠዋል።
በ2016/17 የምርት ዘመን የማዳበሪያ ግብዓት አቅርቦት ችግር እንደማያጋጥም ኃላፊው ጠቁመዋል፣ ነገር ግን በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ለዞኑ ግዢ የተፈጸመው የአፈር ማዳበሪያ በሚፈለገው መጠን ከተፈለገው ቦታ እንዳይደርስ ከፍተኛ እክል መፍጠሩን አንስተዋል። ይሁንና ዞኑ ከክልሉ ግብርና ቢሮ እና ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በመተባበር የግብርና ግብዓት ስርጭት ከዘር በፊት ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
የምርጥ ዘር አቅርቦት ሌላው የምርታማነት መሰረት ነው ያሉት ኃላፊው፣ ዞኑ 30 ሺህ ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ዕቅድ ቢኖረውም ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈቀደለት 19 ሺህ 875 ኩንታል መሆኑን አስታውቀዋል። ቢሮው በዞኑ በበቆሎ የሚሸፈነው የማሳ መጠን በቅርበት በመከታተል ተጨማሪ እንደሚመድብ ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። አርሶ አደሩ ሳይጉላላ ግብዓት በፍጥነት የሚወስድበት አሰራር ተግባራዊ መደረጉንም ጠቁመዋል።
የግብርና ግብዓትን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን የአፈር ለምነት ለማስጠበቅ በኖራ የማከም እና የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት ለመጠቀም ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ኃላፊው ተናግረዋል።
ኃላፊው ለአማራ ክልል የሚያዋጣው ብቸኛው የማደጊያ መንገድ ግብርና ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ሰላም እና ልማትን መሳ ለመሳ አድርጎ ሊጓዝ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ለ2016/17 የምርት ዘመን ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ወደ ክልሉ እየተጓጓዘ መሆኑን የቢሮው የግብዓት አቅርቦት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል። አቅርቦቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ እንዳለውም አረጋግጠዋል::
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ ግዢ ተፈጽሞ ጅቡቲ ወደብ የደረሰው አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ነው። ይሁን እንጂ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ፈተና ገጥሟል። የጸጥታ ችግሩ ጭነት የያዙ ተሽከርካሪዎች ከአንድ ወር በላይ መንገድ ላይ እንዲቆዩ እያደረጋቸው ነው። ያም ሆኖ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም አጓጉዞ የአፈር ማዳበሪያ የአርሶ አደሩ ስጋት እንዳይሆን በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የቢሮው ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው አርሶ አደሩ ባለፈው ዓመት የማዳበሪያ እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ ችግሩ እንዲፈታ በህብረት ያሳየውን ከፍተኛ ተሳትፎ በዚህ ዓመትም ለሰላሙ መረጋገጥ ሊደግም እንደሚገባ አሳስበዋል። አርሶ አደሩ እና መላው ሕዝብ ቅድሚያ ለሰላም ሲሰጥ የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና ለአሲዳማ አፈር ማከሚያ የሚውለውን ኖራ ያለምንም ችግር ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት ምርታማነትን ማረጋገጥ ይቻላል። በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች እና መላው ሕዝብ የግብርና ግብዓት በወቅቱ እንዲደርስ በጋራ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም