በሱዳን የረሃብ አደጋ አንዣቧል

0
182

በሁለቱ ተቀናቃኝ ጄኔራሎች መካከል በሱዳን እየተካሄደ ያለው ዓመት ሊደፍን ከወር ያነሰ ቀናት የቀሩት የእርስ በርስ ጦርነት ወደ የከፋ የረሃብ አደጋ መደቀኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  አስጠንቅቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ሲንዲ ማኬይን እንደተናገሩት በሱዳን በሁለት ተፋላሚ ወገኖች መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ የሱዳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናዊያንን ሕይወት አመሰቃቅሏል።

የሱዳኑ ጦርነት በዓለም መጠነ ሰፊ የሚባለውን የረሃብ ቀውስ ያነሳሳ አደጋን ጋርጧል። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ሲንዲ ማኬን በመቶ ሺዎቹ የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን ስደተኞች በጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ተሰደው ያሉትን ጎብኝተዋል፤ በጉብኝታቸው ወቅትም ጦርነቱ ከፍተኛ የዓለማችን የረሃብ አደጋ መደቀኑን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም እንዳስታወቀው በመላው ሱዳን 18 ሚሊየን ሕዝብ በአሳሳቢ የረሃብ አደጋ ውስጥ ይገኛል። በየጦር ቀጣናው ታጥረው ባሉ ወገኖች ላይ ችግሩ የበለጠ አሳሳቢ መሆኑንም አሳስቧል።

እ.አ.አ በ2011 የዳቦ ዋጋ መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ አልበሽርን ከስልጣን እስከ ማስወገድ የዘለቀው ሕዝባዊ አመፅ ተካሂዶ የአልበሽርን መንግሥት አስወገደ። ይህም የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልስ መፍትሄ ያለው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተስፋን የሰነቀ ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከክል በተፈጠረ አለመግባባት ጦርነት አስከትሏል። የሱዳናዊያንን ተስፋም አጨልሟል፡፡

ዓመት ሊሞላው ከአንድ ወር በታች እድሜ የቀረው ጦርነት እስካሁን የማቆም ምልክት የማይታይበት፣ እጅግ አውዳሚ እና አደገኛ ችግር ሆኗል።

ዋና ከተማዋ ካርቱምም ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየረች ነው፤ ጦርነቱን የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች ከጀርባ የተሰለፉበት በመሆኑ የሱዳንን ችግር አወሳስቦታል። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀኔራል ሀምዳን ዳጋሎ በሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ዋግነር ቡድን የሚታገዝ ሲሆን የወታደራዊ ሽግግር መንግሥቱ መሪ ጄኔራል አልቡርሃን ደግሞ የተወሰኑ የዓረብ ሀገራት ታጣቂዎች እንደሚታገዙ ይነገራል።

ጦርነቱ በፍጥነት በመላ ሀገሪቱ ተዛምቶ ወላፈኑ እስከ ዳርፉር  ተዳርሷል። ባለፈው ዓመት የጃናጃዊድ የታጣቂዎች እና የዓረብ ሚሊሻዎች ወደ ዳርፉር መግባታቸውን ተከትሎ  የብዙ ሺዎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ ሚሊዮኖች ደግሞ የዓለማችን አስከፊው የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ትኩረት በማግኘቱ ጉዳቱን መቀነስ ተችሏል፤ ይሁን እንጂ ችግሩ ተባብሷል ነው የተባለው፡፡ የዓለም ፊት ወደ እስራኤል – ሃማስ ጦርነት በመዞሩ የሱዳን ጉዳይ የተረሳ ይመስላል። በመሁኑም ትኩረት ሊያገኝ እንደሚገባ ጥሪዎች እየቀረቡ ይገኛል።

መቋጫ ባላገኘው ግጭት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሱዳናዊያን ከቀያቸው ተፈናቅለው ሱዳን ውስጥ የተሻሉ ወደሚባሉት አካባቢዎች ወይም ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ መገደዳቸውን የተመድ ወኪሎች ይገልፃሉ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ሲንዲ ማኬይን  ጦርነቱ እንዲቆም እና የሰብዓዊ ድርጅቶች ሕይወት የማዳን ተግባራቸውን ያከናውኑ ዘንድ እንዲፈቅዱ ለተፋላሚ ኃይሎች ጥሪ አቅርበዋል።

“እርምጃ ያለመውሰድ (ምላሽ ያለመስጠት) ውጤቶች አንድ እናት ልጇን ለመመገብ እስከ አለማስቻል እና ቀጣናውን በመጭዎቹ ዓመታት እስከመቀየር የሚያልፍ ይሆናል” ብላለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በረመዳን ወር ተፋላሚዎቹ ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል፤ ይሁን እንጂ ጥሪውን እንደማይቀበል የሀገሪቱን የሽግግር መንግሥት አስታውቋል፡፡ ቅድመ ሁኔታዎች እስካልተሟሉ ድረስ ተኩስ አቁም እንደማያደርግ በመግለፅ ጥሪውን ውድቅ ማድረጉ የችግሩን አሳሳቢነት እንደጨመረው የአፍሪካ ኒውስ ዘገባ ያሳያል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ደግሞ ጦርነቱ ከፈነዳበት ጊዜ ጀምሮ የሱዳን ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ካርቱምን እና በአቅራቢያ ያሉ ከተሞችን ለመቆጣጠር ፍልሚያ ላይ ናቸው። ት በሮመዳን በሀገሪቱ መዲና ካርቱም ከባድ ውጊያ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ባለፈው ዓመት (2015 ዓ.ም) መጋቢት መጀመሪያ አካባቢ በተቀናቃኝ ወታደራዊ ኃይሎች መካከል በሱዳን የሲቪል አስተዳደር ሽግግር ላይ በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ግጭቱ መፈንዳቱ ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጦርነቱ በሀገሪቱ ከባድ ጉዳትኃ አስከትሏል፣ ከተሞችን በማውደም፣ ማህበረሰቡን በማፈናቀል፣ መሰረተ ልማቶችን አፈራርሷል። ሁሉም ወገኖች የበላይነትን እንደያዙ ቢገልጹም፣ የሱዳናዊያንን ሰቆቃ ከማባባስ የፈየደው አንዳች ነገር የለም።

የሰላም ዕድሉ ፈተናዎች እንደተስተጓጎለ ጦርነቱ ተባብሶ ቀጥሏል። የሱዳን መደበኛ ሠራዊት ላስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በኩል ውድቅ ተደርገዋል፤ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ያስቀመጣቸውንም ቅድመ ሁኔታዎች በተመሳሳይ በወታደራዊው ክንፍ በኩል ውድቅ ተደርገዋል፡፡

በዚያም ተባለ በዚህ ግን ሱዳን ከድጡ ወደ ማጡ እየገባች ነው፤ ችግሩም ቀጣናዊ እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሀንን ከመፈናቀል፣ በሀገሪቱ የሚታዩትን ምስቅልቅሎች ያነሳው የቢቢሲ ዘገባ፣ ጉዳዩም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው በዘገባው የጠቆመው።

በቅርቡ የተካሄደ አንድ የመንግሥታቱ ድረጅት ስብሰባ በሱዳን ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጓል። በዚህ ጉባኤም ላይ የድርጅቱ ሊቀመንበርነት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደተናገሩት አንድ ዓመት እየሞላው ባለው ግጭት ለቀጣናዊ አረመረጋጋት እና በሀገሪቱ የመፈረካከስ አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል።

ግጭቱ አስደንጋጭ የተጎጅዎች ቁጥር በሱዳን ሕዝብ ላይ መድረሱን የገለፁት ጉቴሬዝ፣ ይህም የሀገሪቱን አንድነት እያዳከመው እንደሚሄድ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሳህል እስከ አፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባሕር ድረስ የሚያካልል አሳሳቢ ቀጣናዊ አለመረጋጋት ሊቀሰቅስ እንደሚችል በሰሞኑ የመንግስታቱ ድርጅት ስብሰባ ላይ ጉቴሬዝ አስጠንቅቀዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ ላይ የአልጀሪያው ተወካይ እንዳሳሰቡት የውጭ ተዋናዮች ለችግሩ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ወደ ባሰ ችግር እየወሰዱት መሆኑ አሳሳቢ ነው። በመሆኑም እነዚህ ኃይሎች ሀይ ሊባሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሀገሪቱ በአሁኑ ሰዓት ትልቅ በሚባል የውስጥ መፈናቀል ችግር ውስጥ ስትሆን፣ ሰባት ሚሊዮን  ያህል ሰዎች መፈናቀላቸውን በማንሳት አስተማማኝ ዋስትና ውስጥ እንደሚያሻቸው  ጉተሬዝ ገልፀዋል።

እንደ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በመላው ሱዳን 18 ሚሊዮን ሕዝብ አሳሳቢ የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ከዚህ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ያህሉ በአሁኑ ወቅት በከፋ ረሃብ ላይ ይገኛሉ። እስካሁን ጦርነቱን ከተጀመረ ከ12 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here