“በሲድኒ ኦሎምፒክ እስከ ዛሬ ያልተሰበረ ክብረወሰን ተመዝግቧል”

0
140

በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከ30 ዓመታት በላይ ቆይተዋል:: በዚህ ቆይታቸው በርካታ አትሌቶችን አሰልጥነዋል:: ለአብነትም ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋር እና ሌሎች ተጠቃሽ ናቸው:: ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ በክብር ሰንደቅ ዓላማዋ እንዲውለበለብ አስችለዋል:: በውትድርናው ዘርፍም ሀገራቸውን አገልግለዋል፡- ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ:: ኮሚሽነሩ ከአሚኮ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርባለን::

መልካም ንባብ!

 

ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ ውልደት እና እድገታቸው ምን ይመስላል?

ተወልጄ ያደኩት በአሁኑ ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በሙኔሳ ወረዳ ኒኖ ቡሊዘና ቀበሌ ነው:: መንደሯ በእህል ምርት የታወቀች ናት:: አንደኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት ቦለገደና በሚባል ትምህርት ቤት ነው:: ጭቄ ተራራ ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት እና በቀርሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ 12ኛ ክፍል ተምሬያለሁ::

 

እንዴት ወደ አትሌቲክሱ ገቡ?

አካባቢያችን ገጠራማ ነው:: ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ በሩጫ ነው:: የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ በአካባቢያችን ወረዳውን ለመወከል የአትሌቲክስ ውድድር ነበር:: ውድድሩ 21 ኪሎ ሜትር ማራቶን ነው:: ከእኛ በእድሜ የሚበልጡ እነ ንጉሴ ኡርጉ እና ሌሎች አንድ ቀን ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ሊወዳደሩ ሰውነት ሲያሟሙቁ ተመለከትኩ:: ለምን ተወዳድሬ አልሞክረው የሚል ሀሳብ መጣልኝ፤ ምንም ልምምድ ግን የለኝም፤ ለጓደኞቼ ደብተሬን ሰጠሁ፤ የለበስኩትን ካኪ ሱሪ ወደላይ ሰብስቤ በባዶ አግሬ መሮጥ ጀመርኩ::

ከቀርሳ ኢጎ የሚባል ቦታ ደርሶ መልስ ነበር ውድድሩ:: ያለምንም ልምምድ ሦስተኛ ደረጃ ይዤ አጠናቀኩ:: አሟሙቄ ወደ ውድድሩ ባለመግባቴ ለንድ ሳምንት ሰውነቴ ቆሰለ፤ እግሬ አበጠ:: ነገር ግን ማጣሪያውን አለፍኩ፤ ትምህርት ቤቴን ወክየ ወደ ቦቆጂም ሄድኩ:: በመምህሬ ፍላጎት በ800 እና 1500 እንድወዳደር ተደረገ:: በ800 ሜትር ውድድር አንደኛ በመውጣት ለትምህርት ቤቴ ሜዳሊያ አመጣሁ:: በዚህ መንገድ ነበር ወደ ሩጫው የገባሁት:: ይህ ሁሉ የሆነው በ1976 ዓ.ም ነው::

በሚቀጥለው ዓመት ጂማ ላይ የሚካሄድ የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ተሳታፊ ለመሆን ተመርጬ ነበር:: ነገር ግን በሀገራችን ድርቅ በመከሰቱ ውድድሩ ተሰረዘ:: የስፖርቱ ፍቅር እየበረታብኝ መጣ:: በ1978 ዓ.ም የፌደራል ማረሚያ ቤት በተለያዩ ዘርፎች ባወጣው ቅጥር ማስታወቂያ መሠረት ከ700 በላይ ሰዎች ጋር ተወዳድሬ ማረሚያ ቤቱን ተቀላቀልኩ:: ያለፍነው ስምንት ሰዎች ብቻ ነበርን፤ ወደ አዲስ አበባ መጥተን ውትድርናን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደናል::

 

ያለምንም ልምምድ የጀመሩት አትሌቲክስ ብዙ አልገፉበትም፤ በምን ምክንያት እንደሆነ ቢነግሩን?

በአትሌቲክሱ እጅግ ውጤታማ ነበርኩ። በተለይ በ800 እና በ1500 ሜትሮች የሀገር ውስጥ ውድድሮችን አሸንፌ ከቀድሞው ፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም በተደጋጋሚ ሽልማቴን ወስጃለሁ:: ነገር ግን ለአጭር ጊዜ ነው የሮጥኩት፤ ማለትም እስከ 1979 ድረስ፤ ሩጫዉን እንዳቆም ያደረገኝ ሁኔታ ነበረ:: የፌደራል ማረሚያ ቤት በወታደርነት ያለፈ እና እዛው ከውስጥ አድጎ የመጣ አሰልጣኝ አልነበረም፤ ከውጪ ነበር በኮንትራት አሰልጣኝ የሚመጣው:: ስለዚህ “ለምን ከውስጣችን የወጣ፣ ወታደር የሆነ፣ ለማረሚያ ቤቱ ፍቅር እና ተቆርቋሪነት ያለው ሰው አናወጣም?” የሚል ሀሳብ መጣ:: በወቅቱ ኮሎኔል አበራ አያና ነበሩ ኃላፊው፤ በእሳቸው ትዕዛዝ አና መልማይነት ተመረጥኩ::

በወቅቱ ለአሰልጣኝነት የ15 እና የ21 ቀናት ሥልጠና ተሰጥቶ ነበር ፍቃድ የሚሰጠው፤ እኛ ግን በፌደራል ማረሚያ ቤት በነበረን ስድስት ወር የስልጠና ጊዜ በሞስኮ ኦሎምፒክ የተሳተፈ መቶ አለቃ ተገኘ በዛብህ ነበር አሰልጣኛችን፤ ሩ.ው.ዝ (ሩጯ፣ ውርወራ እና ዝላይ) በአጠቃላይ ያስተምረን ነበረ:: እንደመደበኛ ስልጠና ስድስት ወር ሙሉ ሰልጥነናል:: ህጋዊ ስልጠና ባይኖረኝም፤ ከሰልጣኙ ሁሉ በሁሉም ረገድ የተሻለ ውጤት እንደነበረኝ ይታወቃል:: በመሆኑም “እሱ አሰልጣኝ ቢሆን ብዙ ልጆችን ማፍራት ይችላል” በሚል ታምኖብኝ ወደ አሰልጣኝነት ተቀይሬያለሁ:: አሰልጣኝ የሆንኩት ገና በ25 ዓመቴ ነው:: ውሳኔው ሲወሰን ግን ደስተኛ አልነበርኩም:: አኩርፌ ለሦስት ወራት ሀገር ቤት ተቀምጯለሁ:: እንዲያውም ሾፌር ልሆን ነበር:: ጫማየን ሼጬ መንጃ ፍቃድ ለማውጣት ሁለት ሦስቴ ሞከርኩ አልተሳካም::

ከተማ ቀምሻልሁ፤ ገጠሩን እንደገና ለመልመድ አቃተኝ፤ ከዚህ ባለፈ በዋናነት ጓደኞቼ “ምንአልባት ይሄ እንጀራህ ሊሆን ይችላል። ምን ይታወቃል?” ብለው አግባብተው አሳመኑኝ:: በጓደኞቼ ጉትጎታ አሰልጣኝነቱን ተቀበልኩ:: በዚህ ምክንያት ከሯጭነት ወደ አሰልጣኝነት ተቀየርኩ::

ከዚያ በኋላ የአትሌቲክስ አጭር እና ረጃጅም የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን ወስጃለሁ። ለምሳሌ በሀንጋሪ ቡዳፔስት ዩኒቨርሲቲ የአትሌቲክስ ከፍተኛ ስልጠና ወስጃለሁ:: ከእነ ዶክተር ወልደ መስቀል ኮስትሬ፣ ጺዮን ሳንቴ፣ ንጉሤ ጌቻሞ እና የመሳሰሉ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን የወሰዷቸውን ከፍተኛ ስልጠናዎች ተከታትያለሁ:: ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በስፖርት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝቻለሁ::

 

ስድስት ኦሎምፒኮች ላይ ተሳትፈዋል፤ እስኪ ስለሱ ይንገሩን?

በኦሎምፒክ ታሪክ ደራርቱ ካሸነፈችበት ባርሴሎና ኦሎምፒክ ጀምሮ ነው መሳተፍ ጀመርኩት:: ፋጡማ ባሸነፈችበት የአትላንታ ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ አልነበርኩም፤ ስለሆነም ኦሎምፒኩ ወደተዘጋጀበት ቦታ አልሄድኩም። የመሳተፍ እድል አልገጠመኝም:: ነገር ግን የፋጡማ አሰልጣኝ ነበርኩ:: ከአትላንታው ድል በኋላ የምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ እንዲሁም 40 ሺህ ብር ተሸልሜያለሁ:: ይሄን መሰል ሽልማት የተሸለመው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነበርኩ::

በሲድኒ እነ ሀይሌ፣ ሚሊዮን፣ ደራርቱ ወርቆቹን ሲያመጡ የዶክተር ወለወደመስቀል ምክትል ሆኜ ነበር የሠራሁት:: ወደ አቴንስ፣ ቤጂንግ ሪዮ ለንደን ቶኪዮ ስድስቱን ኦሎምፒኮች በዋና እና በምክትል አሰልጣኝነት ነው የሠራሁት:: አሁን ደግሞ በፓሪስ ኦሎምፒክ ለሰባተኛ ጊዜ እሳተፋለሁ (ቃለ ምልልሱ ኦሎምፒኩ ከመጀመሩ በፊት የተካሄደ ነው):: ምናልባትም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ ይህን ያክል ጊዜ (ለሰባት ጊዜ ያክል) በኦሎምፒክ በአሰልጣኝነት የተሳተፈ አለ ብየ አላስብም:: በተጨማሪም በአትሌትክስ ዘርፍ አሰልጣኝ ሆኖ የረዳት ኮሚሽነርነት እድል ያገኘ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ነኝ:: በዚህም እኮራለሁ እደሰታለሁ::

ለዚህ መሳካት ደግሞ ቀን ከሌት ሳንል፣ ሰርግ ክርስትና ሳንታደም፣ በዓላትን በሥራ በማሳለፍ በተደረገ ትጋት የመጣ ውጤት ነው:: 33 ዓመታት ያክል በለፋነው መሠረት ወርቅ በወርቅ ላይ ደራርበን ማምጣት ችለናል:: ከሦስት መቶ በላይ ለሀገር ለተገኙ ሜዳሊያዎች አስተዋጽኦ አለኝ፤ ይህ በመሆኑ ?በሕይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ::

 

በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የአሰልጣኝነት ጊዜ የማይረሱት ገጠመኝ ካለ?

የኦሎምፒኩን አሳጥሬ ተናገርኩ እንጂ ሌሎች ትላልቅ ውድድሮች ላይ በአሰልጣኝነት ተሳትፌያለሁ:: ለአብነት ስድስት ኦል አፍሪካ ጌምስ፣ 12 የዓለም ሻምፒዮና ፣ 14 ክሮስ ካንትሪ፣ የወጣቶች፣ የቤት ውስጥ ውድድሮች እና የግብዣ ውድድሮች ይጠቀሳሉ:: በዚህም ወደ 97 ሀገሮች ቡደኖችን ይዤ ዞሬያለሁ:: አሁን የምንሄደው የፓሪስ ኦሎመፒክ 98ኛየ ነው::

 

በኦሎምፒክ የተደሰቱባቸው እና የማይረሷቸው ክስተቶችን ያጫውቱን?

የማልረሳው ለምሳሌ የሲዲኒ ኦሎምፒክ አንዱ ነው:: በኦሎምፒኩ እስከዛሬ ያልተሰበረ ሬኮርድ የተመዘገበበት ነው:: በ5000 እና በ10000 ሜትሮች ሦስት፣ በማራቶን አንድ በአጠቃላይ አራት ወርቆች ያገኘንበት ነበር፤ ይህ ትልቅ የታሪክ አጋጣሚ እና የሀገር ኩራት ነው:: በቤጂንግ ኦሎምፒክ በጥሩየ እና በቀነኒሳ  አራት ወርቆች ያገኘንበት የማይረሳ ነው:: እንደገና በዓለም ሻምፒዮና በሄልሲንኪ በ5000 ሜትር ከአንድ እስከ አራት የወጡበት ለእኔ በጣም ትልቅ እርካታ ነው::

በተጨማሪ እነ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ፋጡማ፣ ደራርቱ፣ ቀነኒሳ፣ ጥሩየ፣ መሠረት ደፋር አሰልጣኝ በመሆኔ  የእኔ ኩራት ደስታ ወደር የለውም:: ደራርቱ ቱሉን እና  ፋጡማ ሮባን የፌደራል ማረሚያ ቤት ያፈራቸው ናቸው:: እኔ ነኝ መልምየ ቀጥሬ ያመጣኋቸው፤ ይህን በማድረጌ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል:: ጥሩየ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ሁለት ወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችበት ክስተት አይረሳኝም፤ እስከ ቤጂንግ ኦሎምፒክ ድረስ አንድ አትሌት በረዢም ርቀት ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣ የለም:: ጥሩየም አሳድጌ መልምየ ያመጣኋት ናት::

 

ያሰለጠኗቸው ታላላቅ አትሌቶች ለስኬት እንደሚበቁ እንዴት ነው የሚያውቁት? ምን የተለየ ባሕሪ ነበራቸው?

ሦስት አይነት ባሕሪ ያላቸው አትሌቶች ይገጥሙናል፤ አንደኛ ፈጣን እና ወዲያው ውጤታማ የሚሆኑ አሉ:: በመካከለኛ ጊዜ ውጤታማ የሚሆኑ ደግሞ በሁለተኛው ረድፍ ናቸው::  ሦስተኞቹ በጣም በረዘመ ጊዜ ቀስ በቀስ ወደ ውጤት የሚመጡት ናቸው:: ለምሳሌ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ደራርቱ፣ ቀነኒሳ እና ጥሩየ በቶሎ ውጤታማ የሆኑ ናቸው::

እነዚህ ልጆች ወደ ፌደራል ማረሚያ ቤት ሲመጡ እድሜያቸው አልደረሰም ተብሎ በሰው ኃይል እንዳይቀጠሩ ተከልክለው ነበር:: እኛ ነን ለውትድርና አይደለም ለስፖርት ነው የምንፈልጋቸው ብለን ያስቀጠርናቸው:: እነዚህ ልጆች ለረጂም ጊዜ ውጤታማ ሆነው መሮጥ የሚችሉ ናቸው። ተሰጥኦ አላቸው፤

ሁለተኛ እና ሦስተኛ ላይ የጠቀስናቸው (ተምሳሌት የሆኑ አትሌቶችን ለመጥራት አልፈለጉም) በፍጥነት ውጤታማ የማይሆኑት እና ለረጂም ዓመታት በኦሎምፒክ መሳተፍ የማይችሉት በተለያየ አሰልጣኝ ለመሰልጠን ስለሚሞክሩ ነው:: አንዱን ዓመት ከሌላ ሌላውን ዓመት ከሌላ አሰልጣኝ ለመሰልጠን ይሞክራሉ:: ምናልባትም በሂደት ነው ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት:: ዘለቄታም አይኖራቸውም:: ሳይንሳዊ ተከታታይ አሰልጠኘ ካገኙ ውጤታማ ይሆናሉ። በአንድ አሰልጣኝ ብቻ መሰልጠን አለባቸው:: እኔ እንደዚሁ እይቼ ለአጭር ርቀት፣ ለመካከለኛ እና ለረዢም ርቀት እንዲሁም ለውርወራ እና ለዝላይ መሆን የሚችሉ አትሌቶችን መለየት እችላለሁ::

 

ስለጻፉት መጸሐፍ ይንገሩን?

በሕይወት  ሳላልፍ የኖርኩትን እና ለትውልድ ማስተላለፍ የምፈልገውን አስፍሬ ለማለፍ ነው የሞከርኩት:: በመጽሐፉ አንድ ጀማሪ አትሌት ምን ምን ማድረግ አለበት? የሚለውን አካቷል፤ ስለ ስነ ምግብ፣ የአትሌቲክስ ቴክኒኮች፣ ስለ ዶፒንግ እና ሌሎች ቴክኒካል ነገሮች ተካተውበታል:: በተጨማሪ የተለያዩ ውጤታማ አትሌቶች አጫጭር ታሪኮች እና ከእኔ ጋር የነበረን የመጀመሪያ አጋጣሚዎች ተካተዋል:: መጽሐፉን የአርሲ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ለማስተማሪያነት እንደሚጠቀሙት ቃል ገብተውልኛል:: እኔ ባልፍም ታሪኬ አያልፍም። መጽሐፉ “ዳኛው አሰልጣኝ” ይሰኛል:: በኦሮምኟም እንዲሁ ቀርበል።

 

ለነበረውን ቆይታ አናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here