ገጣሚ እና ደራሲ ነቢይ መኮንን ባደረበት ህመም ምክንያት ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ረፋዱ ላይ አርፏል። በዚህ ጽሑፋችን ስለ ሥራዎቹና ሕይዎቱ ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡ ነብይ መኮንን በያዛቸው ሙያዎች ሁሉ ስኬታማ መሆኑን ከሥራዎቹ በተጓዳኝ ያለማንገራገር ብዙዎች የሚመሰክሩለት ምስጉን ሰው ነበር። ነብይ መኮንን ለሀገር የሚሳሳና አብዝቶ የሚጨነቅ መሆኑን ማሳያም በርካታ ሥራዎች አሉት። ይህንንም በሚመለከት ሐያሲ እና ፀሐፊ አብደላ ዕዝራ (ነፍስ ኄር) ‹የገጣሚ ነብይ መኮንን እማይነትበው ስዉር-ስፌት› በሚል በጻፈው ሐተታ ላይ ‹በጥሞና ስለ አራት ግጥሞች› ሲል ባሰፈረው አንድ ጽሑፍ ያነሳል። በዚህም ላይ አያሌ ገጣምያን ስለ ሀገር በተለያየ መንገድ የጻፉ መሆናቸውን አውስቶ፣ ነቢይ መኮንን ከአማርኛ ገጣሚያን የሚለየው አንድ ወይም ሁለት ሳይሆን፣ በሀገር ጉዳይ ከ20 ግጥሞች በላይ መቀኘቱ ነዉ›› ይላል።
ነቢይ መኮንን ከአቶ መኮንን ወንድም እና ከወይዘሮ በለጤ በድሉ፣ በነሐሴ ወር 1946 ዓ.ም፣ በናዝሬት ከተማ ተወለደ፡፡ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመግባቱ አስቀድሞ፣ መምህር ተከስተ ጋር የቄስ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን፤ እዚያም ሳለ ዳዊትን በቃሉ በመሸምደድ የማስታወስ ችሎታውን አዳበረ::
የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ናዝሬት በዐፄ ገላውዲዮስ ት/ቤት የተከታተለው ነቢይ መኮንን፤ በትምህርት አቀባበሉም ከጎበዞቹ ተርታ የሚሰለፍ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ለትምህርት ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ባልደረባ የነበሩት አባቱ፤ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡ ልጃቸው ሁልጊዜም በትምህርቱ ብርቱ ሆኖ እንዲቀጥል ምክራቸውን ይለግሱት ነበር፡፡ ነቢይም፣ ከክፍሉ አንደኛ በመውጣት አባቱን ከማስደሰት ቸል ብሎ አያውቅም::ነቢይ አባቱን አቶ መኮንን ወንድምን በሞት ያጣው የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር ይላል ኢትዬ ኤክስፕሎረር ድረ ገጽ ስለ ነብይ ባሰፈረው ጽሐፍ፡፡
ነቢይ መኮንን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ፣ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ልዑል በእደ ማርያም ተማሪ ቤት ከገቡ ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ነበር፡፡ በመቀጠልም በ1966 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲን የተቀላቀለው ነቢይ፤ ኬሚስትሪን በዋናነት (ሜጀር)፣ ሂሳብን ደግሞ ማይነር በማድረግ አጥንቷል::
በደርግ ዘመን በኢህአፓ አባልነቱ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን በልቷል፡፡ ነገር ግን ደርግንም ሆነ ሀገሪቱን ወይም ሌላ ወገን ሲያማርር፣ ሲወቅስ ወይም ሲረግም አይሰማም፡፡ እንደ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግዬለታለሁ፣ ሞቼለታለሁ ወዘተ እያለ አይመጻድቅም፤ በሚመጻደቁትም ይስቃል ሲሉ ተዋናይ አበበ ባልቻን ጨምሮ የቅርብ ጓደኞቹ ይናገራሉ፡፡ እሱና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ሆነ ክፉ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት ከመጻፍ እና ከመናገር ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ጽንፈኝነት እና አክራሪነት እንደማያዋጣ ሲመክር ኖሯል፤ በጽሑፎቹ፡፡ ቁምነገርን በቀልድ እያዋዛ ማቅረብ ይወዳል – በጽሁፉም በንግግሩም፡፡ መድረክ ላይ ከወጣ ታዳሚን በሳቅ ያፈርሳል፤ አፍ ያስከፍታል፡፡ አንደበቱም ብዕሩም የተባ ነው፡፡
ነቢይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኬሚስትሪ ያጠና ቢሆንም፣ በገጣሚነት፣ በደራሲነት፣ በተርጓሚነትና በጋዜጠኝነት በርካታ ሥራዎችን ለአንባቢያን ያበረከተ ታላቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነበር።
በ1992 ዓ.ም ህትመት የጀመረችውን አዲስ አድማስ ጋዜጣን ከመሰረቱት አንዱ የነበረው አንጋፋው የጥበብ ባለሙያ ነቢይ መኮንን፤ ለሁለት አስርት ዓመታት ጋዜጣዋን በዋና አዘጋጅነት በመምራት፣ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ስኬታማ አድርጓታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ነቢይ፣ በጋዜጣው ላይ በየሳምንቱ በተረትና ምሳሌ እያዋዛ በሚጽፋቸው ርዕሰ አንቀጾች ታዋቂነትን ያተረፈ ሲሆን፤ ለጋዜጣዋም ተነባቢነትን አቀዳጅቷታል::ነቢይ መኮንን ወደ 700 ገደማ ተረቶችን ጽፏል። እነዚህንም ተረቶች በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ርዕስ አንቀጽ ውስጥ አስነብቦናል፤ ይህም የእሱ መለያ ነበር።
ሁለገቡ ከያኒ ነቢይ መኮንን፣ ከአሰርት ዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ ከማብቃቱም በላይ በትወናም ተሳትፎበታል፡፡ የእዚህ ተከታታይ ድራማ ጭብጥ ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ሲሆን፣ ታዋቂዎቹ ተዋናዮች አበበ ባልቻ፣ ፈቃዱ ተክለማሪያምና ፍቅርተ ጌታሁንን ጨምሮ ሌሎችም ተሳትፈውበት ነበር፡፡
ነቢይ፣ “ናትናኤል ጠቢቡ” እና “ጁሊየስ ቄሳር” የተሰኙ ተውኔቶችንም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል። ”ባለካባ እና ባለዳባ” በተሰኘ ተውኔት ላይ ደግሞ በትወና ተሳትፏል። “ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ” የሚለው ነቢይ መኮንን፤ “ጥቁር፣ ነጭ፣ ግራጫ ግጥሞች” እና “ስውር ስፌት- (ሁለት ቅጾች)” የግጥም መድበሎችን ለንባብ አብቅቷል::
ነቢይ፤ “የኛ ሰው በአሜሪካ” የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻው፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ሲወጣ ቆይቶ፣ በመጨረሻ በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ ለህትመት የበቃ ሌላኛው ሥራው ነው። ለንባብ የበቃው ሌላው የነቢይ መጽሐፍ ደግሞ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲሆን፤ “ዘ ላስት ሌክቸር” ከሚለው መጽሐፍ የተተረጎመ ነው።
ነቢይ፤ ዳን ብራውን የጻፈውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረውን “The Davinci Code” የተሰኘ መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ አስነብቧል፡፡ በአሜሪካዊቷ ደራሲ ማርጋሬት ሚሼል ተደርሶ፤ በመላው ዓለም ከፍተኛ ተነባቢነትን ያገኘውን “Gone With The Wind” የተሰኘውን ረጅም ልብ ወለድ መጽሐፍ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ ተርጉሞ አስነብቧል:: በደርግ ዘመን እንደ እኩዮቹ ሁሉ፣ በጸረ-አብዮተኝነት ተጠርጥሮ ወህኒ የተወረወረው ነቢይ መኮንን፤ ከዛሬ ነገ ይሙት ይትረፍ እርግጠኛ ባልሆነበት ሁኔታ፣ Gone With The Wind የተሰኘውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ በሲጋራ ወረቀት ላይ እየተረጎመ፣ በድብቅ በማስወጣት ነው፣ በመጨረሻ ሲፈታ ያሳተመው፡፡
ከነቢይ ጥበባዊ ሥራዎች ሌላው የሚጠቀሰው “ማለባበስ ይቅር” ነው፡፡ ኤች አይቪ-ኤይድስ የሀገር አደጋ በሆነበት ዘመን፣ ነቢይ መኮንን “ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትን ማግለል በሽታውን ያባብሳል፤ ስለዚህ ፍቅር እንስጣቸው፤ አናግልላቸው” የሚል መልእክት ያዘለ ግጥም ገጥሞ ታዋቂ ወጣት ዘፋኞች አቀንቅነውታል::“ማለባበስ ይቅር” የተሰኘው የሙዚቃ ሥራ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ይታይ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከ32 ዓመት በፊት ሜጋ ኪነጥበባት ማእከልን ከመሰረቱት አንዱ የነበረው ነቢይ መኮንን፤ በጊዜው በሜጋ ኪነጥበባት ማእከል አሳታሚነት ትወጣ የነበረችውን ‹‹ፈርጥ›› የኪነ-ጥበብ መጽሔትንም በዋና አዘጋጅነት በመምራት ይታወቃል፡፡
ነቢይ፣ ከጋዜጠኝነቱ እና ከጥበብ ሥራው ጋር በተገናኘ የተለያዩ የዓለም ሀገራትን የመጎብኘት ዕድል የገጠመው ሲሆን፤ ከጎበኛቸው ሀገራት መካከልም ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኢራን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ኬንያ እና ሱዳን ይገኙበታል፡፡
ነቢይ ለሀገሩ ኪነጥበብ ማደግ ከወጣትነቱ ጀምሮ ብዙ የለፋ ታላቅ የሀገር ባለውለታ እንደመሆኑ መጠን፣ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የቅርብ ወዳጆቹ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ፣ ነቢይ በሀገሩ ይከበራል የሚል የምስጋና መሰናዶ አዘጋጅተውለት ነበር፡፡ ነቢይ መኮንን የሦስት ሴት ልጆች አባት ነበር።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም