በስልሳ ዓመት “ለወይዘሪትነት”

0
178

የስልሳ ዓመቷ ጠበቃ እና ጋዜጠኛ ተፈጥሮ በለገሳት የወጣትነት ገጽታዋ በመኖሪያ ከተማዋ የወይዘሪት ቦነሳይረስ አክሊልን ደፍታ  በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በሚካሄደው የወይዘሪት አርጀንቲና የቁንጅና ውድድር ለመካፈል በዝግጅት ላይ መሆኗን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::

ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ “ሚስ ዩኒቨርስ” የቁንጅና ውድድር ከ1958 እ.አ.አ ጀምሮ ተፈፃሚ ሲያደርግ የነበረውን የተሳታፊዎች የእድሜ ገደብ ማስቀረቱ ተጠቅሷል:: የእድሜ ገደቡ በመነሳቱም ከ40ዎቹ እና 50ዎቹ የዘለሉ ተሳታፊዎችንም የሳበ ሆኗል- የቁንጅና ውድድር::

የቦነሳይረስ ከተማ ነዋሪዋ   አሌክሳንድራ ማሪሳ ሮድሪጌዝም በ60 ዓመቷ በደርዘን ከሚቆጠሩ ወጣት ሴቶች ጋር ተወዳድራ ማሸነፍ ችላለች::

አሌክሳንድራ የ2024 እ.አ.አ. ሚስ ቦነስአይረስን ካሸነፈች በኋላ “በጣም ደስተኛነት እና ክብር ይሰማኛል:: ለሁሉም ሴቶች ውበት እድሜ እንደማይወስነውና መሰናክሎችን ማለፍ እንደምንችል ማሳየት እፈልጋለሁ” ስትል ተናገራለች::

አሌክሳንድራ የወጣትነት ገጽታዋ እና እድሜዋ 60 መሆኑ በርካቶችን አነጋግሯል:: በማህበራዊ ሚዲያም ክርክሮችን አስነስቷል:: ያም ሆነ ይህ አሌክሳንድራ በ60 ዓመት እድሜዋ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ትሰራለች። የተመረጠ ምግብን ትመገባለች።  ለፊቷም የተመረጠ ቅባት እንደምትጠቀም ነው የገለፀችው።

በመጨረሻም በመጪው ግንቦት ወር 2024 እ.አ.አ “ሚስ ዩኒቨርስ አርጀንቲና” አክሊልን ለማጥለቅ እንደምትጥር ነው ያስታወቀችው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here