በስቃይ መሠራት

0
151

ሰው ከፈንጠዝያ  ይልቅ የኀዘን ስሜት ውስጥ ብዙ መቆየት ይችላል። ኮሪስቶል በጭንቀታችን ወቅት ከአደሬናሊን  እጢ የሚመነጭ ሆርሞን ነው። ሰውነታችን ብርታት እና ጉልበት እንዲያገኝ ያግዘዋል። ዶፓሚን ደግሞ የደስታ እና የፈንጠዝያ ስሜት ውስጥ ስንሆን የሚመነጭ ሆርሞን ነው። ፈንጠዝያ ቅጽበት ነው፤ በቅጽበት ይጠፋል። ከሰው ልጅ ተጨማሪ ነገር የመፈለግ ባህሪ አንጻር አንዱ ደስታ እንደገጠመን በዚያ እንሰለችና ሌላ የደስታ ስሜት እንፈልጋለን።

ሁልጊዜ አዲስ አዲስ እንፈልጋለን፤ የያዝነውን እንተውና ደስታን ማሳደድ እንጀምራለን። አምላክም ይህንን የሰው ተፈጥሮ በማየት ይመስላል ከኀዘኑ በስተጀርባ ደስታን የሰጠው። የሀገሬ ሰው “ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ” የሚለው ለዚህ ነው። የደስታ ስሜት ለብዙዎች የመጥፊያ ሲሆን እናያለን። ደስታን ፍለጋ ሲያስሱ በምኞት ገመድ ተጠልፈው ወድቀዋል። በደስታ ስሜት ውስጥ  መቆየት ጉድለትን፣ መሰናከልን፣ ኪሳራን ያመጣል፤ “ደስ የሚል ስቃይ” እንዲል ዘፋኙ። ስቃይ ደስ የሚል ስሜት አለው።

የሰው ልጆች ካላቸው ይልቅ የሌላቸውን ነገር ለማሟላት ባደረጉት ፍለጋ ነው ዓለምን የቀየሩት። የሰው ልጅ የተሠራው በማጣት ነው፤ ያደገው በመከራ ነው። ቶማስ ኢዲሰን እናቱን ያጣው  ቀዶ ህክምና ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች መብራት ባለመኖሩ በሌሊት መሥራት ባለመቻላቸው ነበር። አምፖል ቢኖር ማታ ቀዶ ህክምና ማድረግ ይቻል ነበር ብሎ አመነ፤ አምፖልንም ፈለሰፈ። ሁለቱ ወንድማማቾች ከአሜሪካ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚደረግ የመኪና ጉዞ ጊዜን ባይወስድባቸው እናም ምቾት ባይነሳቸው በሰማይ መብረር በሚል አውሮፕላን መሥራት ባላሰቡ ነበር። ዓለምን የቀየሩት የሰው ልጅን የገጠሙት ፈተናዎች ናቸው። ስቃይ መሠሪያ ነው።

ዶክተር ፍሎይድ ስፔንስ ዓለም አቀፍ የሰብዕና ዕድገት ላይ በመሥራት ይታወቃል። “ስቃይ የስኬት መንገድ ነው” ይላል። ስኬታማ የንግድ፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ሰዎች በስቃይ ውስጥ በማለፍ ነው ስኬታማ የሆኑት ይላል። ሁሉም ስቃይ ምቾት ማጣት አይደለም፤ ካሰቡት ቦታ ለመድረስ አንደኛው የማወቂያ እና መብቂያ መንገድ እንጂ። አትሌቶችን በምሳሌነት የሚያነሳው ፍሎይድ ክብረ ወሰን ለማሻሻል እና ለማሸነፍ የሚያልፉበትን ስቃይ የተሞላበት የልምምድ መንገድ በምሳሌነት ያነሳል። “ኖ ፔን፤ ኖ ጌን” (ካላረሱ እጅ ሙሉ አይጎርሱ) ከሚለው የሀገራችን ብሂል ጋር ይመሳሰላል። በስቃይ፣ በድካም፣ በአስቸጋሪ መንገድ ማለፍ ካልቻልህ ምንም አታገኝም ነው የሚለን ፍሎይድ። አሸናፊነት በነሲብ የሚገኝ አይደለም፤ በስቃይ ውስጥ በጽናት ማለፍን ይጠይቃል።

ስቃይ ጊዜያዊ ነው። በውስጡ ማለፍ ከውጤቱ በላይ የሚሰጠው እውቀት እና ልምድ የጎላ ነው። መሰቃየታችንን ምክንያት ያለው መሆኑን መቀበል፤ ማደግ እና መለወጥ የሚቻለው በዚህ ውስጥ ማለፍ ሲቻል ነው ይላል ፍሎይድ። ፍሎይድ ስቃይ መሠሪያ ነው ከሚለው ቀጥሎ የሚያነሳው ሌላ ነጥቡ “ሁሉም ስኬታማ ሰዎች በከፋ ስቃይ ውስጥ አልፈዋል” የሚለውን ነው። ስለዚህ ምናልባትም እኛ ዛሬ በሕይወታችን የገጠመችን ትንሽ  ፈተና ተስፋ ታስቆርጠን ይሆናል። “ፈጣሪ መከራዬን አበዛው” ብሎ ማማረር ለእኛ ጆሮ በተደጋጋሚ የምንሰማው መሰላቸት ነው። እውነታው ግን በምድር ላይ ጉልህ አሻራቸውን ያስቀመጡ ሰዎች በከፋ ስቃይ ውስጥ አልፈዋል።

እናም የቀደሙት ስኬታማ ሰዎች በስቃይ ውስጥ አልፈው ማሳካት የቻሉትን ሁሉ እናንተም ማሳካት ትችላላችሁ ነው የሚለው ፍሎይድ። ብዙዎቻችን ግን ስኬትን የምንጠብቀው እጃችንን ታጥበን መጥቶ እንዲጨብጠን ነው። ስኬትን በቀላል መስዋዕት፣ በአቋራጭ መንገድ ሊያገኙት የሚፈልጉ ብዙ አሉ። ስኬት ግን  ከዚህ በፊት ያልሄዱበትን አቀበት እና ቁልቁለት ያለበትን ተራራ እንደ መውጣት ነው። በአንድ አዳር የተገኘ ስኬት፣ በቀላሉ የመጣ ዝና፣ በዘመድ፣ በሙስና የተገኘ ስልጣን ጣዕም አልባ ነው።

አትሌቶች ከረጂም ጊዜ ልምምድ በኋላ አሸንፈው ወርቅ ሲሸለሙ ተመልከቷቸው። ደስታቸው እና ርካታቸው ፊታቸው ላይ ይነበባል። የድካማቸውን ፍሬ በመብላታቸው ውስጣዊ ሰላም አላቸው። ሁለተኛው በስቃይ ውስጥ ማለፍ የሚሰጠው የሕይወት ልምድ እና እውቀት አለ። ያንን እውቀት አቋራጭ ተጓዦች አያገኙትም።  በግዢ የተገኘን ስኬት እና ዝና ላልተገባ ተግባር ያውሉታል። በቶሎ ይካባሉ፤ በፍጥነት ይናዳሉ። ስኬትን የሚያጣፍጡት በማለፊያ መንገዱ የምንከፍላቸው ዋጋዎች ናቸው። ዋጋ ያልከፈለ የስኬትን ጣዕም አያውቃትም። የስኬት መንገድ ረጂም፤ እንቅፋቶች የበዙበት ነው።

የብዙዎች የስኬት መንገድ እንደሚነግረን ኀላፊነት መውሰድ፣ ፍርሐትን መጋፈጥ እናም ራስን በሚገባ መረዳት ነው። ታዋቂው ደራሲ ሮቢን ሻርማ “ለውጥ መጀመሪያ ከባድ ነው። መሃሉም ትርምስ ነው። መጨረሻው ግን የከበረ ነው” ይላል። ዴል ካርኒጌም ይህንን ሐሳብ ይደግፈዋል። “ስኬታማ ሰዎች  ምንም የተስፋ ጭላንጭል በሌለበት ተጉዘው የተሳካላቸው ጠንካራዎች ናቸው” ሲል። ውድቀት ጓደኛም ጠላትም ሊሆን ይችላል። ሞኝ ሰዎች ውድቀት እና ስቃይን እንደ ጠላት ይውሰዱት እንጂ ጥቂት ብልሆች አስተማሪ እና መካሪ ጓደኛ አድርገው ይመለከቱታል። ከዚህ ምልከታም በመነሳት ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን ያስቀድሙለታል፤ ለስቃይ እና ውድቀት የዳግም መማሪያ ዕድል ነው።

የፎርድ መኪና መስራች ሄነሪ ፎርድ እ.አ.አ በ1901 ስራውን ለቆ መኪና መገጣጠሚያ ለመገንባት ወሰነ።  በዘመኑ 150 ሺህ  ዶላር ይዞ ፋብሪካ የከፈተው ሄነሪ ፎርድ ኪሳራ ገጠመው። አብሮት የነበረው ባለድርሻ አልሚ በፎርድ እምነት ነበረው። ከጊዜያት በኋላ አልሚው ባለሀብት ከፎርድ ጋር የነበረውን ስምምነት አፍርሶ ኩባንያው ተዘጋ። በዚህ ሁሉ ጊዜ በጽናት የቆመው ሄነሪ ፎርድ ከሁለት ዓመታት በኋላ የአሁኑን ፎርድ የሞተር ኩባንያ ለመመስረት አሰበ። ኪሳራ ውስጥ የነበረውን ኩባንያም እንደገና እንዲያንሰራራ አደረገው። አሁን ፎርድ በዓለም ተወዳጅ እና ዝናው የናኘ መኪና አምራች ድርጅት ነው። ፎርድ በችግሮች ውስጥ ማለፍን አሳይቷል።

ኢንተርፕሩነር ድረገጽ የሰው ልጆች በሕይወት ጉዟቸው የስኬት ጫፍ ላይ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት የሚገጥሟቸውን ስቃዮች አስፍሯል። ሁሉም ሰው ስኬታማ ለመሆን በስቃይ ጎዳናዎች ተራምዷል። ስለዚህም የመጀመሪያው ስቃይ አይቀሬ የስኬት መዳረሻ መንገድ ነው። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፉ ሰዎች የልፋታቸውን ዋጋ በደስታ ያገኛሉ። “በመከራ የሚዘሩ በደስታ ያጭዳሉ” እንዲሉ። ጭንቀት፣ ስቃይ ተስፋ ማጣት የስኬት ጫፍ ላይ ለመድረስ በእጃቸው  ለሚቧጥጡ ሰዎች አይቀሬ ናቸው። ትንሽ ጭንቀት የሰው ልጆች ራሳቸውን ወደ መልካም የሕይወት አቅጣጫ እንዲያዞሩ ታደርጋለች።

በስኬት ጉዞ ላይ ተስፋ መቁረጥ ያጋጥማል፤ ብርቱዎች ግን ያልፉታል። አንዳንድ ጊዜ ስራዎች፣ እቅዶች፣ ተግባራት ዝብርቅርቅ ይላሉ። ያን ጊዜ አቅጣጫ ቢስ እና ተስፋ የለሽ ሆኖ መታየት ያጋጥማል። በዚህ ጊዜ ብልሆቹ ወደ ኋላ መለስ ብለው ለምን እንደጀመሩ፣ ግባቸውን፣ ተግባራቸውን መገምገም ይጀምራሉ። አዕምሯቸው ውስጥ የሚመላለሰውን አሉታዊ ሐሳብ አያዳምጡትም። ባሉበት ሆነው ይታገሳሉ፤ ይጸናሉ። እጃቸውን ለተስፋ ማጣት አይሰጡም።

ሰዎች ሲሳካላቸው ወዳጆቻቸው ይርቋቸዋል። ስኬት ብዙ መስዋዕት ይፈልጋል። ጥሩ ወዳጆቻችሁ አይደግፏችሁም። ይርቋችኋል።  ግንኙነት፣ ጊዜ እና ጉልበትን ለስኬት መስዋዕት ማድረግ ካለብህ አድርጋቸው። ሁሉም ሰው የራሱን ጉዞ ነው የሚባዝነው እናም አንተም የራስህን ጉዞ ተራመድ። ማንም ጊዜ እና ገንዘቡን ለአንተ መስዋዕት ለማቅረብ አልተፈጠረም። የራስህን እየሰዋህ ትጓዛለህ እንጂ።  ሕልምህን የማይጋሩ ሰዎችን ከዙሪያህ ታርቃለህ፤ ስታድግ መንገድህ እየጠበበ ይመጣል። ከፍታው ላይ ጥቂት ሰዎች ናቸው ያሉት። ብዙኀኑ ከታች ናቸው።  ስለዚህ ከፍ ስትል ብቸኛ ትሆናለህ፤ መምረጥ ትጀምራለህ፤ ማግበስበስ ታቆማለህ።

በስኬት መንገድ ሰዎች ተስፋ ያስቆርጡሃል። ሕልሞችህን በውስጥህ አስቀምጥ፤ ለማይመጥኑ ሰዎች ብትነግራቸው ያጣጥሉብሃል። የሰው አዕምሮ ለአሉታዊ ሐሳቦች ቅድሚያ እንዲሰጥ በመኖር ተለማምዷል። ብዙኀኑ ያልተሄደበትን መንገድ እጓዝበታለሁ ስትላቸው “ትሰበራለህ፣ ትጠፋለህ፣ ትከስራለህ” የሚሉ መሰል አሉታዊ ሐሳቦችን ያነሱብሃል። አዲስ መንገድን ሁሉም ይፈራዋል። ይቅርብህ የሚሉህም መንገዱን ስለማይረዱት ነው። ፍርሀት እና ጥርጣሬን በውስጥህ የሚያሰራጩብህ ብዙ ሰዎች ይገጥሙሃል። በስኬት ጎዳና ስትገሰግስ እነዚህን አሉታዊ ሐሳቦች የሚቋቋም ትክሻ ማዳበር አለብህ። “ብትችልስ አንተ ስለ ሕልምህ እና ስራህ አታውራ፤ ራሱ ስራህ ይናገር” ይላል ኢንተርፕሩነር ድረገጽ።

“ያለ ምክንያት ሰዎች ይጠሉሃል” የሚለው ኢንተርፕሩነር በእውነታው ዓለም ሰዎች ስኬታማ ሰዎችን አይወዷቸውም የሚለውን ሐሳብ አስፍሯል። ሰዎች ለየት ያለ ነገር ሲያዩ ይቀናሉ፣ ምቀኝነት ያጠቃቸዋል። ደካማ ሰዎች እነሱ መስራት ያልቻሉትን ሰዎች ሲያሳኩት ይበሳጫሉ። እነዚህን ሰዎች አንደ ማደጊያ ጉልበት ተጠቀምባቸው፤ እንደ ስልጠና ተገልገልባቸው። ስኬት በቀል ነው፤ ጠላቶችህ እንዲያሳድጉህ አድርጋቸው።

ወደ ስኬት ስትጓዝ ራስህን መጠራጠርህ አይቀሬ ነው። እውቀትህን፣ ውሳኔዎችህን፣ ውስጥህን መጠራጠር ትጀምራለህ። ወደ ፊት ግቦችህን ለማሳካት ስታስብ ውስጥህ ያለው ጥርጣሬ ይታገልሃል። በግጭት መሐል ታልፋለህ። መጥፎ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተሳስቼ አጥፊ ውጤት እንዳይገጥመኝ የሚል ስጋት አይቀሬ ነው። ሁሉም ችግሮች መፍትሔ አላቸው። አዲስ አቅጣጫ ሁልጊዜ በሕይወት አለ። ሁልጊዜም ጥርጣሬህ እንዲያሸንፍ አትፍቀድለት። በስኬት ጥርጣሬ አይቀሬ ነው፤ ዋናው ጉዳይ አንተ ምን ያህል ትታገላቸዋለህ የሚለው ነው። ለጥርጣሬ ፊት አትስጥ።

ኢንተርፕሩነር ውድቀት በስኬት ኀሰሳ የማይቀር መሆኑን ይናገራል። አደጋዎች ይገጥሙሃል። አደጋዎችን ሊያመጡብህ የሚችሉ አጣብቂኝ ውስጥ ያሉ ውሳኔዎችን ትወስናለህ። አደጋዎች በተፈጥሮ ያስፈራሉ። ትችት፣ ስም ማጥፋት ሊመጣብህ ይችላል።  ወደ ፊት የሚነዳህ ጉልበት ዶፓሚን መሳይ ጉልበት ተስፋ ነው። ትወድቃለህ ደግሞም ዋጋ ከፍለህ በትጋት ትነሳለህ። መሳሳትህ ወደ አዲስ መንገድ እና ስኬት ይመራሃል። ቶማስ ኤዲሰን ተደጋጋሚ እና አሰልቺ ሙከራዎችን አድርጎ አምፖልን አብርቷል። “አንድ ሺህ አምፖል የማይሰራባቸውን መንገዶች ነው የሞከርሁት እንጂ አልተሳሳትሁም” ሲል መልስ ሰጥቷል። መውደቅ፣ መሳሳት ወደ ትክክለኛው መንገድ ይመራሃል። አንተ ምን ያህል በሙከራህ ጸንተህ ለመቀጠል ተዘጋጅተሃል?

በመጨረሻም ሁልጊዜ በሥራህ እና ጉዞህ ደስተኛ እና መልካም አስተሳሰብ ይኑርህ። እንደሚሳካልህ እመን፤ በጉዞህ ተማመን። ቀና ሐሳብ እና ተግባር ሲቀናጁ ላይሳካልህ የሚችልበት ምንም ምክንያት የለም ይላል ኢንተርፕሩነር ገጽ።

 

(አቢብ አለሜ)

በኲር የህዳር  23  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here