በስፖርት እና በአመጋገብ  ጤናዎን ይጠብቁ

0
69

የስልሳ ሰባት ዓመቱ አዛውንት ይብሬ ሷልህ በሳምንት ለሁለት ቀናት ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡  እኒሁ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወደ ሥራ ከመሄዳቸው አስቀድሞ ራሳቸውን ለማነቃቃት እና ጤናቸውን ለመጠበቅ ይህን ተግባር ለዓመታታ እያከናወኑት ይገኛል፡፡

ሌላው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የካሳው ይርዳው በተከታታይ ሰባት ዓመታት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ሲያሰቃየው ከነበረው የኮሊስትሮል ህመም ፈውስ አግኝቷል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ግለሰቦች በጋራ በመሰረቱት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማህበር አባል በመሆን እየሰሩ ጤናቸውን ከመጠበቅ ባለፈ ሌሎች ሰዎችም የእነርሱን መንገድ እንዲከተሉ እያደረጉ መሆኑን ነግረውናል፡፡

እንዲህ እንደሰሞኑ በዓል ሲመጣ ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸው ወቅት መሆኑን የድልነሳ የጤና እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማሰልጠኛ ማህበር አሰልጣኝ ፋሲል አስማረ ይናገራል፡፡ ከሶስት ሳምንታት በፊት የረመዳን ፆም ተጠናቋል፡፡ አሁን ደግሞ የፋሲካ በዓል በመሆኑ የአመጋገባችን ሁኔታ ሊቀየር ስለሚችል በተለይም ቅባት እና ስብ የበዛባቸውን ምግቦች ባለመመገብ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሰልጣኙ ፋሲል አስማረ ገልፆልናል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ በከተሞች የማህበረሰቡ ችግሮች ሆነዋል፡፡ በተለይም ግፊት፣ የስኳር ህመም፣ የልብ እና የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡

አቶ ካሳው ይርዳው የኮሊስትሮል ህመም ሲያሰቃያቸው ቆይተው በአንድ ጓደኛቸው ምክር  ወደ   አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማእከል በማምራት ስፖርቱን በመስራታቸው ለሰባት ዓመታት ካሰቃያቸው የኮሊስትሮ ህመም ሊፈወሱ ችለዋል፡፡ ስፖርት ከመስራት ባሻገርም በአመጋገብ ላይ ጥንቃቄ ማድረጋቸው ላገኙት ፈውስ አስተዋፅኦ ማድረጉን ነው የገለፁልን፡፡

ዛሬ ላይ የሰውነት ቅርጾቸው የተስተካከለው  አቶ ካሳው ይርዳው ስፖርት እና የአመጋገብን ሁኔታ ከእኔ በላይ ምስክርነት የሚሰጥ የለም ሲሉ አጫውተውናል፡፡

በመግቢያችን ላይ የጠቀስናቸው የ67 ዓመት  አዛውንት አቶ ይብሬ ሷልህ ስፖርት በመስራታቸው እና አመጋገባቸውን በማስተካከላቸው ከእርሳቸው  ባለፈ ቤተሰቦቻቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሃምሳ በላይ አባላት ያሉት ድልነሳ የጤና እና አካል ብቃት ማሰልጠኛ ማእከል በተለይም በህክምና ተእዛዝ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ትእዛዝ የተሰጣቸው አንዳንድ ህሙማን  እንደ አዲስ ማህበሩን ሲቀላቀሉ አሰልጣኙ ፋሲል አስማረ ከሚያደርግላቸው ክትትል  ባለፈ የማህበሩ አባላት እንዲሚያበረታቷቸው በዚህ ዘገባ በተገኘንበት ወቅት ተመልክተናል፡፡

የማህበሩ አባላት በሳምንት ሶስት ቀን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይሰራሉ፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ደግሞ የእግር ጉዞ እና ተራራ የመውጣት ተግባር ያከናውናሉ፡፡ እነዚህን ተግባራት ካከናወኑ በኋላ የሚመገቡትም ጥንቃቄ የተሞላበትና ቤት ያፈራውን እንደሆነ አባላቱ ነግረውናል፡፡ የሴቶች ቁጥርም ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ ወጣት ቃል ኪዳን እሸቴ በአሰልጣኝነት በምትሰራበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማእከል ላይ ቁጥራቸው 10 የሚደርስ ሴት ተሳታፊዎች ይገኛሉ፡፡ በባሕር ዳር ከተማ ብቸኛ የሴት አካል ብቃት አሰልጣኝ በምትገኝበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ ማህበር የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ፡፡

ከዚህ ማእከል ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ቀበሌ 13 በሚገኘው አዲሱ የስፖርት ሜዳ በሳምንት ሶስት ቀን ይሰራሉ፡፡ እዚህ ቦታ በተገኘንበት ወቅት በፈለገ ህይወት   አጠቃላይ ሆስፒታል የድንገተኛ እና ጽኑ ህሙማን ሐኪም  ዶ/ር ንጋት አስማማው ለተሳታፊዎች ምክር ሲያስተላልፉ አግኝተናቸዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት ለአካል ብቃት ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክትም፡- “ጥንቃቄ የተሞላበት አመጋገብ  ካልተደረገ ስፖርት በመስራት ብቻ ጤናን መጠበቅ አይቻልም” ብለዋል፡፡

በቀን ከሁለት እስከ ሶስት ሊትር ውኃ መጣጠት ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ንጋት ወቅቱ የፆም ጊዜ ስለነበር የፍስክ ምግቦችን በምንመገብበት ጊዜ መጠኑን እና አይነቱን ማገናዘብ እንደሚያስፈልግ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በተቻለ መጠን በቂ የእረፍት ሰዓት ሊኖር እና በጊዜ ልንመገብ ይገባል ያሉት ዶ/ር ንጋት “ስፖርት ስንሰራ በተለይም ከሰአት በኋላ ከሆነ ከሁለት ሰአታት አስቀድሞ መመገብ ይገባል” ሲሉ መክረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጠዋት ተነስተው መንገድ ዘግተው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተዟዙረን ባስተዋልነው ቅኝታችን ታዝበናል፡፡ ይህም ተላላፊ ያልሆኑ ገዳይ የሚባሉት በሽታዎች እየተበራከቱ መምጣት  አስገዳጅ ደረጃ ላይ ስመድረሱ ብዙዎች የሚናገሩት ነው፡፡ በእርግጥ ለጤናቸው የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ ለሰውነት ቅርጻቸው ሲሉ ስፖርትን የሚያዘወትሩ በርካቶች ናቸው፡፡

የወንዶች ቁጥር በተበራከተባቸው  የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማእከላት ውስጥ የሴቶች ቁጥርም እየጨመረ  መሆኑን ተዟዙረን በቃኘናቸው ማእከላት አስተውለናል፡፡

እናስ?

እናማ  እባክዎን አመጋገብዎን በማስተካከል እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ጤናዎን ይጠብቁ!

(መልሰው ጥበቡ)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here