በአርጀንቲና ከቦነስአይረስ በስተደቡብ የምትገኘው ሂላሪዮ አስካሱቢ ከተማ በሺህ በሚቆጠሩ የዱር በቀቀኖች በመወረሯ በጩኽታቸውም ሆነ መሰረተ ልማት ላይ በሚያደርሱት ጥፋት ኗሪዎች መማረራቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::
ኗሪዎች ከተማዋ ቀደም ባሉት ዓመታት ጀምሮ በበቀቀኖች መንጋ ብትወረርም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን እየተበራከቱ የሚያደርሱት ጥፋትም ሆነ የድምፅ ብክለት እያየለ መምጣቱን ነው በምሬት የገለጹት:: የበቀቀኖቹ መንጋ ቁጥራቸው እየተበራከተ በመሄዱ በቋሚ ምሰሶ ላይ የተዘረጉ የስልክ፣ የበየነ መረብ፣ የኤሌክትሪክ ገመዶችን በመንከስ እና በመቆራረጥ ለኪሳራ መዳረጋቸው ነው የተብራራው::
በየጐዳናዎች እና ዳርቻዎች በቀቀኖቹ የሚጥሉት ኩስ ከተማዋን አጉድፎ ከማስቸገሩም ባሻገር ሌት ተቀን የሚያሰሙት የማያቋርጥ ጩኽት ኗሪዎቹን ማወኩ ነው በእማኞች የተጠቀሰው::
አምስት ሺህ የሚደርሱት የሂላሪዮ አስካሱቢ ኗሪዎች ከአእዋፉ ጋር አብረው መኖር እንደማይችሉ ቢያስታውቁም የከተማዋ አመራሮች ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ነው ምላሽ የሰጡት::
በከተማዋ የተስተዋለው በበቀቀኖች የሚደርሰው ችግር አዲስ አለመሆኑን እና ባለስልጣናቱ ችግሩን ለማቃለል ቢጥሩም ምንም ማድረግ አለመቻላቸው ተጠቁሟል:: በባለስልጣናቱ ከተሞክሩ የችግር ማቅለያዎች አእዋፉን ማባረሪያ ድምፆች ማሰማት፣ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው መብራቶችን (laser light) መልቀቅ ይገኙበታል:: በመከላከያ ወይም በማራቂያነት ቢተሞከሩት ድምፅና ቀለማትን የሚፈነጥቅ ብርሃን በመጀመሪያው ጊዜ ቢሸሹም በሂደት እየተላመዱት ሁከታቸው መቀጠሉ ነው የተገለፀው::
የግብርና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ፓኦሎ ሳንቼዝ አንሳኖቫ ከ2013 እ.አ.አ ጀምረው በከተሞች የዱር በቀቀኖች ብዛታቸው ለመጨመሩ መነሻው ምን እንደሆነ አጥንተዋል:: በጥናታቸውም ሰዎች በበቀቀኖቹ ተፈጥሯዊ መኖሪያ ደን ላይ ባደረሱት ጭፍጨፋ እና ምንጣሮ መሰደዳቸውን አረጋግጠዋል::
የዱር በቀቀኖች በአርጀንቲና ጥበቃ ስለሚደረግላቸው በአእዋፉ ላይ የሚወሰድ ጉዳት የሚያደርስ ርምጃ በጥብቅ በመከልከሉ ከመታገስ ውጪ አማራጭ መፍትሄ አለመኖሩ ነው በማደማደሚያነት የሰፈረው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም