የሚኖሩበትን ሀገር ለቀው ወደ ውጪ ሀገር የሚሄዱ ጡረተኞች (ተጧሪዎች) በአገራቸው ከሚኖሩት የበለጠ የብቸኝነት ወይም የማህበራዊ እና ስሜታዊ መነጠል አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በአሜሪካ የስነልቦና ማህበር 4995 ከኔዘርላንድ ውጪ የሚኖሩ እንዲሁም 1338 በኔዘርላንድ የሚኖሩ ጡረተኛ ዜጐችን በመጠይቅ ያካተተ የጥናት ውጤትን በመረጃ ምንጭነት ይፋ አድርጓል፡፡ በውጤቱም በውጪ ሀገር የሚኖሩ ጡረተኞች ከቤተሰብ እና አጋሮቻቸው ርቀው ሲለሚሄዱ ብቸኝነት ወይም ማህበራዊ እና ስሜታዊ መነጠል ይገጥማቸዋል፡፡ ይህ ማለት አረጋውያኑ በአዲስ ሀገር በሚፈልጉት እና በሚገጥማቸው ግንኙነት አለመመጣጠን ለጤና እክል እንደሚዳረጉ ነው የተብራራው – በጥናቱ ውጤት፡፡
በጥናቱ የተካተቱት ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው አረጋውያን ሲሆኑ ሁሉም 50 ዓመት ከሆናቸው በኋላ ወደ አዲስ መኖሪያ ሀገር የወጡ ናቸው፡፡
በጡረታ እድሜ ላይ ያሉ አዛውንቶች ወደ አዲስ ሀገር የሚጓዙት ለተሻለ ኑሮ፣ በዝቅተኛ ወጪ መኖርን በመሻት፣ በአዲስ የዓየር ሁኔታ ለመዝናናት ወ.ዘ.ተ ሊሆን እንደሚችል በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ከተጠየቁት የጥናት ተሳታፊዎች ከተገኘው ምላሽ ውጤት በውጪ ሀገር የሚኖሩ በእድሜ የገፉ ሰዎች ለብቸኝነት እና ለማህበራዊ መገለል፣ ለድብርት፣ ለልብ ህመም እና ለመገንዘብ ዓቅም ማሽቆልቆል ይጋለጣሉ፡፡
በኔዘርላንድ የስነህዝብ ተቋም ተመራማሪው አስማ ቤቱል ሳቫሽ በጡረታ እድሜ ማለትም ከ60 ዓመት በላይ ወደ ውጪ ሀገር መሰደድ አስደሳች ቢመስልም ተጨባጭ እውነቱ በተቃራኒው አለመሆኑ ነው የተሰመረበት፡፡
ይህ በመሆኑም ተመራማሪዎቹ በማጠቃለያ ምክረ ሃሳብነት ማንኛውም እድሜው የገፋ ወይም ጡረተኛ ወደ አዲስ አገር ከመንቀሳቀሱ አስቀድሞ ሊገጥመው የሚችለውን ተፅእኖ በጐ በጐውን ብቻ ሳይሆን ተቃራኒውንም ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ነው በማደማደሚያነት የሰፈረው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም