በአስደናቂ ፍጥነት እየተሻሻሉ እና እያደጉ ከመጡ ስፖርቶች መካከል እግር ኳስ አንዱ ነው። ይህ ተወዳጅ ስፖርት ከታክቲኩ እና ከቴክኒኩ ባሻገር ሕጎቹም እየተሻሻሉ እና እየተቀየሩ መጥተዋል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሜዳ ላይ ተግባራዊ ሆነው ከተመለከትናቸው ሕጎች መካከል ከአስከፊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ የተጫዋቾች ቅያሪ ብዛት ወደ አምስት ከፍ ብሏል።
በየ25 ደቂቃ ልዩነት ተጫዋቾች የውኃ እረፍት ሰዓት እንዲጠቀሙም የተፈቀደው በዚህ ወቅት ነበር። የተንቀሳቃሽ ምስል ዳኝነት (VAR)፣ የረቀቀ የግብ መስመር ቴክኖሎጂ፣ በተለያየ ምክንያት የሚባክነውን ደቂቃ ለማካካስ የሚጨመረው ደቂቃም በዓለም ዋንጫው ተሻሽሎ ተመልክተናል። ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ በኋላም ሜዳ ውስጥ በዋዛ ፈዛዛ የሚባክን ደቂቃ እንደሌለ በየጨዋታው ዐይተናል።
ለአብነት እነዚህን አነሳን እንጂ በቀጣይ አዲሱ የውድድር ዘመንም አዲስ ሕግ ተግባራዊ እንደሚደረግ መረጃዎች አመልክተዋል። እንደ ሜል ስፖርት መረጃ በ2024/25 የውድድር ዘመን የተጫዋቾች አቋቋም ሕግ (Offside rule) ተሻሽሎ ተግባራዊ ይሆናል። ጥናት እየተደረገባቸው ያሉ ሌሎች ተጫማሪ ሕጎችም እንዳሉ ተነግሯል። የቀድሞው የአርሴናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በዓለም እግር ኳስ የላቀ አስተዋጽኦ ካደረጉ እና ስማቸው በተደጋጋሚ ከሚነሱ የእግር ኳስ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው። ቬንገር ከአሰልጣኝነት ሥራቸው ከተገለሉ በኋላ በፊፋ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ልማት ዳይሬክተር ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ።
እርሳቸው ወደዚህ ሙያ ከመምጣታቸው በፊት በርካታ የእግር ኳስ ሕጎች እና ደንቦች እንዲቀየሩ እና እንዲሻሻሉ ግፊት ሲያሳድሩ እንደነበር አይዘነጋም። ፈረንሳዊው የእግር ኳስ ሊቅ ከተሾሙ በኋላም ለእግር ኳሱ ይበጃል የሚሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው።
አርሰን ቬንገር መሻሻል አለባቸው ከሚሏቸው ሕጎች ውስጥ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የዓለም ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ መደረግ አለበት፣ በጨዋታ ወቅት የእጅ ውርወራ ብዙ ደቂቃዎችን እያባከነ በመሆኑ ወደ ቅጣት ምት መቀየር አለበት የሚሉ ይገኙበታል። እንደ አርሰን ቬንገር ማብራሪያ ከእጅ ውርወራ ይልቅ በአምስት ሴኮንድ ውስጥ በእግር መመታት አለበት የሚል ሀሳብም አላቸው።
ሌላው በቀድሞው አሰልጣኝ ከሚኮነኑ የእግር ኳስ ሕጎች መካከል በክለቦች ውድድር ከሜዳ ውጪ የሚቆጠር ግብን የተመለከተ ነው። ላለፉት 50 ዓመታት በተለይም በጥሎ ማለፍ የክለቦች ውድድር ከሜዳ ውጪ የሚቆጠሩ ግቦች የተለየ ጥቅም ሲሰጣቸው የቆየ መሆኑን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል።
በ1960ዎቹ የረቀቀው ይህ ሕግ ክለቦቹ ከሜዳቸው ውጪ ግቦችን እንዲያስቆጥሩ ለማበረታት ታስቦ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል። አንድ ክለብ ከሜዳው ውጪ አንድ ግብ አስቆጠረ ማለት ባለ ሜዳው ተጋጣሚውን ቡድን ለማሸነፍ የግድ እንግዳው ክለብ ካስቆጠራቸው ተጨማሪ ሁለት ግቦች ከመረብ ማገናኘት ይኖርበታል። አዲሱ ሕግም ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በተጫማሪ በኢሮፓ ሊግ፣ በኢሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ የማጣሪያ እና የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ጭምር መረጃዎች አስነብበዋል።
አሁን ላይ ዘመናዊ እግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ በሚቆጠሩት የግብ ቁጥሮች ብልጫ ብቻ መወሰን አለበት ተብሏል:: በ2022 ሕጉ የተሻሻለ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሴፌሪን ከሜዳ ውጪ ለሚቆጠር ግብ የተለየ ጥቅም መሰጠቱ አላስፈላጊነቱን ከሁለት ዓመታት በፊት ሲያስረዳ እንዲህ ማብራራቱን ሜል ስፖርት አስነብቧል።
“ሕጉ እ.አ.አ ከ1965 ጀምሮ በአውሮፓ የክለቦች ውድድር ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። ነገር ግን ሕጉ መቀየር ስላለበት ባላፉት ጥቂት ዓመታት ከተወያየንበት በኋላ አስፈላጊ ሆኖ ስላልተገኘ እንዲቀየር ወስነናል:: በርካታ ደጋፊዎች ፣ አሰልጣኞች እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም የፍትሐዊነት ጥያቄ እንደሚያስነሳ በተደጋጋሚ ሲነግሩን ነበር። አሁን ግን እንዲቀየር አድርገናል’’ብሏል የማህበሩ ፕሬዚዳንት::
እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ ከሜዳ ውጪ የሚቆጠር ግብ በተለየ መንገድ ጥቅም እንዳይኖረው በተደጋጋሚ ሲናገሩ የነበሩት ቬንገር በመጨረሻ ሀሳባቸው ተቀባይነት አግኝቷል። የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በ2022 እ.አ.አ የቆየውን ሕግ በመሻር ከሜዳ ውጪ የሚቆጠር ግብ የተለየ ጥቅም እንዳይኖረው አጽድቋል።
በዋናነት ሕጉ የተሰረዘበት ምክንያት ክለቦቹ ወይም ቡድኖቹ በሜዳቸው ሲጫወቱ በጥብቅ መከላከል ግቦች እንዳይቆጠሩባቸው ያደርጋሉ በሚል ነው። ይህ ደግሞ የምርጡን እና አዝናኙን እግር ኳስ ውበት እንዲበላሽ ያደርጋል ተብሏል።
ከዚያ ይልቅ ክለቦች በጥሎ ማለፉ ጨዋታ በሜዳቸው እና ከሜዳቸው ውጪ በድምሩ በሚያስቆጥሯቸው ግቦች አሸናፊ መሆን እንዳለባቸው በሕጉ ተቀምጧል። ሁለት ተጋጣሚ ቡድኖች ባስቆጠሯቸው ግቦች እኩል ከሆኑ ደግሞ ጨዋታው ወደ ተጨማሪ ደቂቃ ያመራል። ከዚህ ካለፈ ደግሞ ወደ መለያ ምት እንደሚያመራ ሕጉ ያትታል።
ከዚህ በፊት በእንግሊዝ ካራባኦ ዋንጫ ከ90 ደቂቃ በኋላ ውጤቱ አቻ ከሆነ ጭማሪ ደቂቃ (Extra time) እንደነበር ይታወቃል። ዘንድሮ ግን ተጨማሪው ደቂቃ አስፈላጊ አይደለም በሚል በቀጥታ ጨዋታው ወደ መለያ ምት እንዲያመራ መደረጉ አይዘነጋም።
በአውሮፓ እግር ኳስ ከሜዳ ውጪ የሚቆጠር ግብ ጥቅም ላይ እንዳይውል ከሁለት ዓመታት በፊት ሕጉ ፀድቆ ዘንድሮ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በእስያ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ውድድር ገና ዘንድሮ ነው ሕጉ የፀደቀው።
አንባቢያን ሆይ፣ ከዚህ በፊት ከሜዳ ውጪ በተቆጠሩ ግቦች የክለቦችን ማለፍ እና መውደቅ ዕጣ ፈንታን የወሰኑ የማይዘነጉ ጥቂት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ምሽቶችን እናስታውሳችሁ።
በ2017/18 የውድድር ዘመን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑልን 3ለ1 አሸንፎ ዋንጫ በወሰደበት ወቅት ካታሎናውያን የባርሴሎና ደጋፊዎች ክለባቸው ከሩብ ፍጻሜ የተሰናበተበትን ምሽት መቼም አይረሱትም።
ባርሴሎና እና የጣሊያኑ ክለብ ሮማ በሩብ ፋጻሜው የተገናኙ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ባርሴሎና በሜዳው ካምፕ ኑ 4ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ጉዞውን አሳመረ ተብሎ ተወራ። አንድ ግብ ያስቆጠሩት ሮማዎችም የመልሱን ጨዋታ ተስፋ በማድረግ በፈንጠዚያ ወደ ጣሊያን ተመለሱ።
ሁለተኛው ዙር ጨዋታ በሮማ ሜዳ ስታዲዮ ኦሎምፒክ ነበር የተደረገው። ሮማዎችም 3ለ0 አሸነፉ። ካታሎናውያንንም ጸጥ እረጭ አደረጉ። ሮማዎች ወደ ስፔን ተጉዘው ያስቆጠሯት ብቸኛ ግብ ከሜዳ ውጪ ግብ ባስቆጠረ በሚል ሕግ ግማሽ ፍጻሜ ደርሰዋል። በግማሽ ፍጻሜው ግን በሊቨርፑል ተሸንፎ ጉዞው ተሰናክሏል።
እ.አ.አ በ2018/19 የውድድር ዘመን ቶተንሀም ሆትስፐርስ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊጉ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍጻሜ የደረሰበት ወቅት ነው። የሰሜን ለንደኑ ክለብ በግማሽ ፍጻሜው የኔዘርላንድሱን ክለብ አያክስ አምስተርዳምን በማሸነፍ ነበር ፍጻሜ የደረሰው። በአሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፓቺቲኖ ይመራ የነበረው ቶተንሀም አስደናቂ የግማሽ ፍጻሜ ምሽት ማሳለፉ አይዘነጋም።
ቶተንሀም በመጀመሪያው ዙር የመድረኩ ፍልሚያ በሜዳው 1ለ0 ተሸንፏል። በመልሱ ጨዋታ ደግሞ ወደ ኔዘርላንድስ ዩሀን ክራይፍ አሬና ስቴዲየም ተጉዞ በሉካስ ሞራ ሦስት ግቦች 3ለ2 አሸንፏል።
የግማሽ ፍጻሜው ትንቅንቅም በድምር ውጤት 3 አቻ የተጠናቀቀ ሲሆን ከሜዳው ውጪ ሦስት ግቦችን በአያክስ መረብ ላይ ማዝነቡ ፍጻሜ እንዲደርስ ምክንያት ሆኖታል። በፍጻሜው ከሌላኛው የእንግሊዝ ክለብ (All English final) ከሊቨርፑል ጋር ተገናኝቶ 2ለ0 ተሸንፎ ነው ዋንጫውን ያጣው።
በ2020/21 እ.አ.አ በታላቁ መድረክ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ለመቀላቀል በጥሎ ማለፉ ጁቬንቱስ እና ፖርቶ ተገናኝተዋል። በመጀመሪያው ዙር መርሐ ግብር ፖርቶ በሜዳው 2ለ1 አሸንፎ የጣሊያኑን ክለብ ሸኝቶታል። ወደ ጣሊያን የተጓዘው የፖርቹጋሉ ፓርቶ ድጋሚ ጁቬንቱስን ማሸነፍ አልቻለም። እንዲያውም ጁቬንቱስ ነው በተመሳሳይ ውጤት 2ለ1 የረታው።
ጨዋታውም ወደ ጭማሪ ደቂቃ አምርቷል። በጭማሪው ደቂቃ ሁለቱም ክለቦች አንድ አንድ ግብ በማስቆጠራቸው በጨዋታ እኩል አራት አቻ ውጤት መመዝገብ ችሏል። ይሁን እንጂ ፖርቶ ከሜዳው ውጪ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ሩብ ፍጻሜ እንዲቀላቀል አስችሎታል። በሩብ ፍጻሜው ግን በቸልሲ 2ለ1 ተሸንፎ መሰናበቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
ሌላው እ.አ.አ በ2008/9 የውድድር ዘመን ባርሴሎና እና ቼልሲ በግማሽ ፍጻሜው የተገናኙበትን ትንቅንቅ ታሪክ እንዲህ ያስታውሳል። የሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያው ዙር የታላቁ መድረክ ፍጥጫ በካምፕ ኑ ተደርጎ ያለ ምንም ግብ ነው የተጠናቀቀው። በጉጉት የተጠበቀው የስታንፎርድ ብሪጁ የመልስ ጨዋታ ደግሞ በአንድ አቻ ውጤት ነበር የተጠናቀቀው።
የካታለኑ ክለብ ወደ ምዕራብ ለንደኑ ክለብ ተጉዞ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብም ከሜዳ ውጪ ግብ ባስቆጠረ በሚለው በቆየው ሕግ ፍፃሜ ለመድረስ በቅቷል። በፍጻሜው ሌላኛውን የእንግሊዝ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድን 2ለ0 በመርታት ዋንጫውን ማሳካቱን ታሪክ ያወሳል። ዘንድሮስ በተሻሻለው አዲስ ሕግ በሻምፒዮንስ ሊጉ፣ በኢሮፓ ሊጉ፣ በኢሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ የትኞቹ ክለቦች ተጠቃሚ ይሆናሉ? አብረን የምናየው ይሆናል::
የመረጃ ምንጫችን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ድረ ገጽ፣ ዘ ሰን፣ ሜል ስፖርት እና ስካይ ስፖርት ናቸው::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም