በተከበርንበት ቶኪዮ እንዴት እንፈር?

0
63

እንደ አይን ብሌን ጠብቀን ያልያዝነው አትሌቲክሳችን በአይናችን እያየነው ተኖ ሊጠፋ ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የሰራቻቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች በአለም መድረክ ገጽታዋን በመቀየር ረገድ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይነገራል። ከመንግስታዊ ዲፕሎማሲ ቀጥሎ ትልቁን የገጽታ ግንባታ የተወጣው አትሌቲክስ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ የታላላቅ አትሌቶች መገኛ መሆኗ ነው።

በጃፓን ቶኪዮ እየተከናወነ የሚገኘው 20ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ህመም ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የቁልቁለት ጉዞው ፈጣን መሆኑን በተጨባጭ አሳይቷል። በተለይም ሀገራችን በምትታወቅባቸው የረጅም ርቀቶች ታስመዘግባቸው የነበሩት የወርቅ ሜዳሊያዎች በአውሮፓውያን ተወስደዋል። ጎረቤት ኬንያ ልንፎካከራት የምትገባ ሀገር ሳትሆን ሄደን ልምድ ልንቀስምባት የሚገባት ሀገር ሆናለች። የኬንያ አሸናፊነት ከበርካታ አመታት ጀምሮ የተገነባ ሆኖ ሳይንሳዊና ዘመናዊ አትሌቲክስ ስፖርት አሰራርን የምትከተል ሆናለችና።

በዚህ መድረክ የተመለከትናቸውን የአውሮፓ ሀገራት ለውጥና ውጤታማነት  ብንመለከት በቂ ማስረጃ ይሆናል። በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ፈረንሳይ ወርቅ አሸንፋለች። በተመሳሳይ ርቀት በሴቶች ጣሊያን ብር አግኝታለች። እነዚህ ሀገራት ከዚህ በፊት በዚህ ርቀት ሜዳሊያ አይደለም ዙሩን የሚጨርስ አትሌት አልነበራቸውም። ለጥቁሮች በር የከፈተው በኦሎምፒክ ታሪክ ሰርቶ ያለፈው የአበበ ቢቂላ ሀገር ምን ነክቷት ነው የአትሌቲክስ ስፖርቷ ወርዶ የተፈጠፈጠው የሚል ጥያቄ የሚያነሱ በርካቶች ናቸው።

አለም የደረሰበትን ዘመናዊ አሰለጣጠን ከመከተል ይልቅ በድሮውና በነበረው የስልጠና ባህል አትሌቲክሱ መቀጠሉ ለዛሬ ውድቀቱ ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩ እንዳሉ ሁሉ ትክክለኛውን አትሌት ወደ ማሰልጠኛ ቦታዎቹ ወርዶ መልምሎ ማምጣት የሚችል ቆራጥ ባለሞያ ጠፍቷል የሚሉም አሉ። ከሀገር ፍቅርና ክብር የግል ጥቅምን የሚያስቀድሙ አሰልጣኞች አትሌቶችና ማኔጀሮች መበራከት ሌላኛው ምክንያት ስለመሆኑም ሙያተኞች ያነሳሉ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የአትሌቶች መገኛ ሀገር ናት እየተባለ ደረጃውን የጠበቀ የመለማመጃ ትራክ እንደ ሀገር ያገኘችው ባለፈው ወር ነበር:: ይሄ ለአትሌቲክስ ክብር የማይመጥን ሆኖ መቆየቱ ለውድቀቱም ምክንያት ያደርጉታል። የፌዴሬሽኑ አመራሮችና ስራ አስፈጻሚዎች ስራቸውንና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ ለወንበር ሲሉ የፈጠሩት አተካራ ሀገር ተረስታ አትሌቲክሱ ለመውደቁ ሌላኛው ሙያተኞች የሚሰጡት መንስኤ ነው።

የቶኪዮ የአለም አትሌቲክስ ውድድር  ከኢትዮጵያ በኩል አዲስ ተወዳዳሪ አትሌት ያልተመለከትንበት፣  አዲስ አሰልጣኝ ያላየንበት፣ አዲስ የአሰራር ሀሳብ ያላቸው ሙያተኞች የሌሉበት መሆኑን በደንብ አይተናል:: ውጤቱም የሚያሳየው ይህንኑ ነው። የአሰለጣጠን መንገዱን ሌሎች ሀገራት ወስደው አዳብረው አሻሽለው ቴክኒክ ላይ የበሰሉ አሰልጣኝ ቀጥረው ለውድድር ስለቀረቡ ደጋግመው ያሸነፉን ብዙ ያሳየናቸውን ብዙ ያስተማርናቸውን እኛን ነው። እንግዲህ እንዴት ነው ለውጥ የሚመጣው የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው።

ከዚህ በፊት በኦሎምፒክ እና በአለም ሻምፒዮና ሜዳሊያ የሚገኝባቸው የኢትዮጵያ ርቀቶች በሙሉ በሌሎች ሀገራት ተወስደዋል:: ምን መሰራት አለበት በሚለው ጉዳይ በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ መምህርና የአትሌቲክስ ስፖርት ባለሞያ ድረስ እንዳለው የራሱን ትዝብት በተከታይ አጋርቶናል።

“በቶኪዮ የአለም አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ እያገኘችው ያለው ውጤት የነበረንን  ታሪክ አይገልጽም::

“ታሪካችን ካለን የህዝብ አንድነት እና ተፈጥሮአዊ   ጸጋ  ጋር  ተዳምሮ  በእነ አበበ ቢቂላ፣ በእነ ምሩጽ  ይፍጠር….ወዘተ ከኢትዮጵያ  አልፎ  አፍሪካን  በመወከል  በአለም  መሪ  ሆነን  ቆይተናል:: ያን መሪነት ለማስቀጠል የአለምን የእድገት ፍጥነት በመረዳት አንድነትን፣ አሰራርን ፣የስራና የሙያ ጥራትን፣ ተሳትፎ  ማብዛትን… ወዘተ ነገ እንዳንቀደም በማሰብ  በመተንበይ  ማስቀጠል  ይቻል  ነበር:: ግን ጉዞው ተቃራኒ ነው::” ነው ያሉት::

ያሁኑን ውድድር ችግሮች  በሁለት ይከፍላቸዋል-የፌዴሬሽን እና የአሰልጣኝ በሚል::

 

የፌዴሬሽን ችግር፡-

ከድጋፍ ና ክትትል  አኳያ አሰልጣኝ ከአሰልጣኝ፣ አትሌት ከአትሌት፣ አሰልጣኝ ከአትሌትና  ከፌዴሬሽን  ጋር  ያለውን  መናበብ  ስናይ  ለኢትዮጵያ  የሚመጥን  ዝግጅት  አለመኖሩን  ያሳያል::

ከማናጀሮች ጋር (የውጭ ) ያላቸው ግንኙነት መመጠን አለበት፤ ማለትም የግል ውድድሮች መቀነስ እና ቅድሚያ ለሃገር መሰጠት አለበት፣ የስልጠና ፕሮግራሞች በአገር ውስጥ አሰልጣኞች  ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መቃኘት አለበት::

 

የአሰልጣኝ ችግር

የአትሌቲክስ ሰራ የወታደር  ስራ  ማለት ነው::  ወታደር  ሊያጠቃ ሲፈልግ  አብሪ ይልካል:: ትልቅ የቡድን ስራ ይጠይቃል::

አትሌትክስም ለማሸነፍ አድካሚ ያስፈልጋል:: ውጤቱ  የሁሉም ነው::

የሚታዩትን ችግሮች በስልጠና ማስተካከል ይቻል ነበር:: ግን በግል ተቀባይነት ለማግኘት፣ ለመብለጥ፣ ጥቅም ለማግኘት…. ወዘተ  በሚል በተደበቀና ቀናነት በሌለው የስራ ሂደት  ኢትዮጵያን  መጉዳት እንጂ መጥቀም አይቻልም::

“የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማእድ” እንደተባለው በመካከል ያለው ስፖርታዊ እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር መኖሩን  የአሰልጣኞችና የአትሌቶች  ስራ አንድነት  ማሳያ  ነው::

መፍትሄው

ፌዴሬሽን  ከላይ እና ከታች ያሉ ችግሮችን ቀድሞ መፍታትና መልካሙን  ስራ ማላመድ፣ ካልሆነ ጊዜው ሳያልፍ  ለህዝብ  አሳውቆ  የራስን  ጥቅም  ትቶ  መልቀቅ መልካም ነው::

የግል ውድድሮችን ማስቆም (መመጠን) ደግሞ ሌላው መፍትሄ ነው::

ውጤትን በጸጋ እየተቀበሉ ቀሪውን ስነ ልቦና ከስሜታዊነት ውጭ  ለማከም መሞከርና  የአገርን ድክመት ተቀብሎ አሰራርን መቀየር ነው”ብሏል- የደብረታቦር ዩኑቨርሲቲ መምህር እና የስፖርት ባለሙያው ድረስ እንዳለው::

(መልሰው ጥበቡ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here