በቲክቶክ ላይ መደነስን ያገዱት

0
158

በአሜሪካ የዌስት ቨርጂኒያ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ተጫዋቾቻቸው ቡድናዊ ስሜትን አጐልብተው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ እየደነሱ በቲክቶክ እንዳይለቁ ማገዳቸውን ዩፒአይ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስንብቧል፡፡

የዌስት ቨርጂኒያ የእግር ኳስ ክለብ ወይም  “ማውንቴይነርስ” እየተባለ የሚጠራው ቡድን ቀደም ብሎ ያሰለጥኑት የነበሩትን ሂልብራውንን ከስራቸው አሰናብቷቸዋል፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የእግር ኳስ ክለቡ ውጤት እያሽቆለቆለ መምጣቱ ነበር፡፡

የ61 ዓመቱ አሰልጣኝ ሪች ሮድሪጌዝ ባለፈው ታህሳስ ወር 2024 እ.አ.አ ነበር የእግር ኳስ ክለቡን የተረከቡት፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ ክለቡ  ያለበትን ደረጃ፣ የተጫዋቾቹን ጠንካራ እና ደካማ ጐኖችን ለመለየት ጥረት ማድረጋቸውን ነው ያበሰሩት፡፡ አሰልጣኝ ሪች ሮድሪጌዝ እግር ኳስ በግለሰቦች ጥረት የቡድን ውጤት የሚገኝበት፣ የቡድን ስራ የሚስተዋልበት፣ ሁሉም ተጫዋቾች በቴክኒክ እና በታክቲክ ተክነው በቡድን ውጤት የሚደምቁበት የስፖርት ዓይነት መሆኑን ነው ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም አሰልጣኙ በተረከቡት የክለብ ተጫዋቾች ደካማ ጐን ያሉትን አጢነው አዲስ እገዳ ጥለዋል- እየደነሱ ወይም እየጨፈሩ በቲክቶክ መልቀቅን፡፡ ተጫዋቾች በየጥጋጥጉ በተናጠል ስስ ጥብቅ ያለ ወይም የሰውነታቸውን ቅርፅ የሚያሳይ ልብስ ለብሰው አማረ? አላማረ በሚል ቲክቶክ ዳንስ ላይ  ተጠምደው ማየት እንደማይሹ ቁርጥ ያለ ውሳኔያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም  ለቡድኑ ውጤት ማሽቆልቆል እና ቡድናዊ ስሜት መቀዛቀዝ ዋነኛው ምክንያት በቲክቶክ በተናጠል እየጨፈሩ ለመልቀቅ የሚያደርጉት ጥረት መሆኑን በመገንዘባቸው እገዳውን ማስተላለፋቸውን ነው በማደማደሚያነት ያሰመሩበት፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here