በቴክኖሎጅ የታገዘ አሰራር መጀመሩን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ አስታወቀ

0
124

የኢ ትኬት አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረጉ በተገልጋዮች ላይ የሚደርስ እንግልት እየቀነሰ መሆኑን የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ይህን ያለው በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የበጀት ዓመቱን 3ኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ሲያደርግ ነው። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ያየህ የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የሚፈጠር ችግር ሁሉ አቀፍ ጉዳት የሚያመጣ በመሆኑ ይህንን ችግር ተረድተን እየሰራን ነው ብለዋል። በመሆኑም ተቋሙን የማደራጀት እና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።

“ትርፍ መጫን፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ማንገላታት፣ መጎተት፣ መስደብ እና ሌሎች አልባሌ ተግባራት በመናኸሪያዎች ውስጥ ሲስተዋሉ ነበር” ያሉት አቶ ወርቁ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የኢንተርኔት ትኬት መቁረጥ አገልግሎትን ጀምረናል ብለዋል።

ተሳፋሪዎች መናኸሪያ ውስጥ በሚገኙ ማዕከላት ትኬት እንዲቆርጡ መደረጉ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ቀርፏል ነው ያሉት አቶ ወርቁ።

ባለስልጣኑ “አሁንም ተሳፋሪዎች ወደ መናኸሪያ ሲመጡ  ልክ እንደ አየር መንገድ ደህንነት እና ምቾት እንዲሰማቸው በመፈለግ እየሰራ ነው” ብለዋል።

በክልሉ 10 ያህል መናኸሪያዎች የኢንተርኔት ትኬት አገልግሎት ተጀምሯል። ባለስልጣኑ በወረዳዎችም ጭምር አገልግሎቱን ለማስፋት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ተገልጿል።

በአማራ ክልል ምክር ቤት  የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ኢንዲስትሪ፣ ከተሞችና መሠረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በላይ ዘለቀ የትራንስፖርት ዘርፍ የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች የተሻሻሉበት የመናኸሪያ አሰራር ወደ ወረዳዎችም ወርዶ የኅብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት አለበት ብለዋል። አሁን በተጀመረው የኢንተርኔት ትኬት መቁረጥ  አገልግሎት “ትርፍ መጫን እና ተሳፋሪን ማንገላታት እየቀነሰ ነው” ሲሉም በመስክ ምልከታ ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

መናኸሪያዎችን ማስፋፋት፣ ማዘመን እና ምቹ ማድረግ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here