ሁሉም ሰው የተጓዘበት መንገድ፣ ያገኛቸው ሰዎች፣ የተጋራቸው ጨዋታዎች፣ የተመለከታቸው እና የሰማቸው ሐሳቦች አሻራ ውጤት ነው:: አእምሯችን ከመጥፎም ሆነ ከጥሩ ልምዶች ለመማር ትዝታዎችን እንዲያከማች ሆኖ የተሰራ ነው:: እድሜ በሁኔታዎች፣ በቦታ እና በጊዜ ተሸንሽኖ ትናንት ወደ ሚባል የጊዜ ቀለበት ይጠቀለላል:: ያ ጥቅል ደግሞ የትውስታ ባንካችን በሆነው አዕምሮ ውስጥ ይከማቻል::
አንጎላችን ከማያውቀው ይልቅ የሚያውቀውን ማሰላሰል ይቀናዋል:: ለዚህም ደጋግሞ ወደ ትናንት ማህደር እያስገባን በትዝታ ውስጥ ፊታችን በእንባ እንዲያቀረዝዝ፣ ዓይናችን ቡዝዝ እንዲል ያደርገናል:: አሁን ላይ ማተኮር፤ በተለይ በዚህ ዘመን በስፋት እየተነገረ ያለ ሐሳብ ነው:: ትናንት ላይለወጥ አለፈ:: ነገም በማንም ዘንድ በርግጠኝነት የሚጠበቅ አይደለም:: ለዚህም አሁን ያለንበትን ቅጥጽበት እንድናጣጥም የሰብዕና ግንባታ ምሁራን ይመክሩናል::
ዛሬ ያለንበት ሕይወት ጥሩም ይሁን መጥፎ በድንገት አልተገነባም:: የየዕለት ሐሳብ፣ ስሜት፣ ድርጊት ተጠራቅሞበታል:: ባለፈው ጊዜ ላይ ስንጣበቅ ሐሳባችን ትናንት፣ ስሜታችን ጸጸት፣ ድርጊቶችን ብስጭት፣ ውጤታችን ተስፋ ማጣት ይሆናል:: ያለፈው ዘመን ትውስታችን በሙሉ የሚወገዝ አይደለም:: እውቀት ነው፤ ልምድ ነው:: በልምድ የተኖረ መስመር ነው:: በሙከራ የተረጋገጠ ነው:: ይሁን እንጂ አብዛኛው ጊዜ ጸጸት እና ቢሆን ኖሮ የሚሉ የማይመለስ ቁጭቶች የሞሉበት ይሆናል::
የአሜሪካ ሳይኮሎጂካል ማህበር ገጽ ትዝታ ነገሮች የተሻሉ፣ ቀላል እና የበለጠ አስደሳች መስለው የሚታዩበት ያለፈውን ጊዜ የመናፈቅ ስሜት ነው ይላል:: “ስፍር ቁጥር የሌላቸው ተወዳጅ ዘፈኖች መነሻ የሆነው ስሜት ነው:: የድሮ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እንደገና እንዲያንሰራሩ የሚያደርግ እና በፖለቲከኞች ጥቅም ላይ የሚውል ነው” ብሏል ገጹ:: ከምንም በላይ “ሰዎች በዛሬው ሁኔታ በማንኛውም ምክንያት ደስተኛ ካልሆኑ፤ ነገሮች ቀደም ባሉት ጊዜያት የተሻሉ ነበሩ የሚል ስሜት የመሰማት ዕድላቸው ሰፊ ነው” ሲል ስለ ትዝታ ምንጭ ጽፏል::
የነርቭ ሳይንስ ምሁራን የሰው ልጆች በቀን እስከ 60 ሺህ የሚጠጉ ሐሳቦችን ያስባሉ ብለዋል:: ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ድግግሞሽ ነው:: እንዲሁም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች ከወደፊቱ ጊዜ ይልቅ ስላለፈው 70 በመቶ ያስባሉ:: ሰዎች ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የአእምሮ ጉልበታቸውን ያለፉ ክስተቶችን በማሰላሰል ላይ ያውሉታል::
ትዝታ የሰው ልጅ ማንነት ወሳኝ አካል ነው:: ካለፈው እንማራለን፣ መልካም ጊዜያትን እያስታወስን እንደሰትበታለን፣ ከባድ ገጠመኞቻችን ደግሞ ጥንካሬን ይሰጡናል:: ነገር ግን ይህ ብቻም አይደለም:: በተቃራኒው የጉዳት መልክም አለው::
ዘፈን በ1990ዎቹ ቀረ፤ ኑሮ ድሮ ነበር እንጂ፤ ፋሽንማ በእኛ ጊዜ ነበር’ንጂ የሚሉ እና መሰል ገለጻዎች በብዙዎቻችን አፍ ውስጥ አሉ:: አዕምሮ ያለማቋረጥ ወደ ኋላ እየተጓዘ ባለፈው ኩራት፣ ስህተት፣ ፀፀት እና ኪሳራ ውስጥ ሲዘፈቅ በርግጥም ትዝታ ጉዳቱ ያመዝናል::
ዛሬን ግራዋ አድርጎ ትናንትን ማር የማድረግ ዝንባሌ ውስጣችን አለ:: የዛሬው ነገር አይጥመንም:: እንማረርበታለን:: ኑሮ ውድ ነው እንላለን:: የትኛውም ዘመን ላይ ኑሮ ርካሽ ነው ተብሎ አያውቅም:: ሲያንፍ ግን በዚያን ጊዜም ሁሉ ነገር ርካሽ ነበር እንላለን:: በወቅቱ ግን ጥሩ ነው አላልነውም ነበር:: ሁልጊዜም ኑሮ እየጨመረ፣ ዋጋ እየተወደደ ነው የሚመጣው:: በአንጻራዊነት ቢለካ የትኛውም ዘመን የራሱ ልዩ መልክ አለው:: በትናንትናው ስንደነቅ ዛሬን ሳናጣጥመው፤ የጠላነውን ዛሬን ነገ እናመሰግነዋለን:: ያ የትዝታ ጫና ነው::
ያለፈውን ጊዜ ደጋግሞ ማሰብ የአሁኑን ጊዜ አእምሮ ሰላም ያሳጣል:: ለወደፊቱ ተስፋ የመቁረጥን ሁኔታ ያመለክታል:: የስነ ልቦና ጥናቶች ይህን ሁኔታ ሩሚኔሽን ብለው ይጠሩታል:: በያሌ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና ባለሙያ ሱዛን ኖለን ባደረጓቸው ጥናቶች ሩሚኔሽን ማለት “በችግሩ፣ በምልክቶቹ፣ እና በውጤቶቹ ላይ ደጋግሞ ማተኮር ነው” በማለት ገልጸውታል::
ይህ የአስተሳሰብ ሂደት ችግሩን ከመፍታት ይልቅ በችግሩ ስሜታዊ ክብደት ውስጥ ሰውን የሚያሰጥም ነው:: አንድ ሰው “ለምን እንዲህ ሆነ?”፤ “እንዲህ ባላደርግ ኖሮ::” በሚሉ ሀሳቦች ሲዋጥ ከአሉታዊ ስሜቶች አዙሪት መውጣት ይሳነዋል::
ሩሚኔሽን ለድብርት እና ለጭንቀት መከሰት እና መባባስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል:: አእምሮ ያለማቋረጥ በአሉታዊ ትዝታዎች ሲሞላ፣ አሁን ባለው ህይወት ውስጥ ያሉ መልካም ነገሮችን የማየት እና የመደሰት ችሎታ ይቀንሳል:: ይህ ደግሞ ወደ ማኅበራዊ መገለል እና የብቸኝነት ስሜት ሊመራ ይችላል::
ሱዛን ኖለን እንዳመለከቱት ሩሚኔሽን ችግርን የመፍታት ክህሎትን ያዳክማል:: አንድ ሰው ያለፈው ስህተቱ ላይ ሲያተኩር፣ ለአሁኑ ችግሮቹ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል የአእምሮ ትኩረት እና ጉልበት ያጣል:: ይህም በዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ቀላል ውሳኔዎችን እንኳ ለማድረግ መቸገርን ያስከትላል::
ያለፈውን ጊዜ ከመጠን በላይ ማሰብ አሁን ያለውን እውነታ በተዛባ መነጽር እንድንመለከት ያደርገናል:: ለምሳሌ ያለፈውን መልካም ጊዜ ብቻ እያሰቡ “ያኔ ሁሉም ነገር ጥሩ ነበር” ብሎ ማሰብ፣ አሁን ያለውን ህይወት ዋጋ ቢስ እና አስቸጋሪ እንደሆነ እንዲሰማን ያደርጋል:: በተቃራኒው ያለፈውን መጥፎ ገጠመኝ ብቻ ማሰብ ደግሞ አሁን ባሉ መልካም አጋጣሚዎች ላይ ጥርጣሬ እና ፍራቻ እንዲኖረን ያደርጋል::
በትዝታ ጥላ ውስጥ መኖር ጉዳቶች አሉት:: ያለፈው ጊዜ በውድቀት እና በኪሳራ የተሞላ ከሆነ፣ ወደፊትም ተመሳሳይ ነገር እንደሚከሰት ማሰብ ይቀናል:: ይህ ደግሞ አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር፣ ስራ ለመቀየር፣ ወይም አዲስ ግንኙነት ለመጀመር ፍርሃት እንዲሰማን ያደርጋል::
ያለፈው ላይ ተጣብቆ መቆየት የግል እድገትን ይገታል:: ኤክኻርት ቶሌ ቶሌ”ዘ ፓዎር ኦፍ ናው” በሚለው መጽሐፉ እንደሚገልጸው፣ አብዛኛው የሰው ልጅ ስቃይ የሚመነጨው በአሁን ቅጽበት ከመኖር ይልቅ አእምሮ ያለፈውን ወይም የወደፊቱን በማሰቡ ነው:: ያለፈውን ስህተት ከመማሪያነት ይልቅ እንደ እስር ቤት ስንጠቀምበት ወደፊት ለመራመድ የሚያስችለንን ጉልበት እናባክናለን::
ያለፈውን ጊዜ መለወጥ እንደማይቻል ግልጽ ነው:: ነገር ግን ሩሚኔሽን ውስጥ ያሉ ሰዎች “ቢሆን ኖሮ፣ ባላደርግ ኖሮ፣ ቢሆን ኖሮ…” በሚል የማይለወጠውን ለመቀየር በአእምሯቸው ይታገላሉ:: ይህ ከንቱ የአእምሮ ልፋት ለወደፊቱ ለማቀድ እና ለመስራት የሚውለውን ውድ ጊዜ እና ጉልበት ያባክናል:: በዚህም ደግሞ የማይለወጠውን እና የማይቀየረውን ትናንትን ለመለወጥ ጉልበት እናባክናለን::
ከትናንት ትዝታ እስር ቤት መውጣት ይቻላል:: ያለፈውን ሙሉ በሙሉ መርሳት አይቻልም፤ ተገቢም አይደለም:: ዋናው ቁም ነገር ያለፈው ታሪክ ጌታችን ሳይሆን አስተማሪያችን እንዲሆን ማድረግ ላይ ነው::
አሁን ባለው ቅጽበት ላይ ትኩረት ማድረግን መለማመድ አእምሮ ወደ ኋላ እንዳይባዝን ይረዳል። ይህም አዕምሮን በስራ ላይ ማዋል እና በዓላማ መኖር ስንጀምር ማስተካከል እንጀምራለን:: አዕምሮ ዛሬ ላይ የሚሰራው ነገር ሲያጣ ትናንት ውስጥ ሄዶ የትዝታ አልበም ማገላበጥ ይጀምራል:: ትዝታ ያመነዥካል:: ዛሬ ላይ ስራ ስንሰጠው ወደ ትናንት እንዳይመለስ እናደርገዋለን::
ሉዊዝ ሄይዩ ‘‘ዩ ካን ሂል ዩር ላይፍ” በተሰኘ መጽሐፏ ራስን መውደድ እና ለራስም ሆነ ለሌሎች ይቅርታ ማድረግ ካለፈው ህመም ለመፈወስ ቁልፍ እንደሆነ ታስረዳለች:: ትዝታ እንደ ጥላ ነው:: አብሮን ይጓዛል፤ ነገር ግን ከፊት ለፊታችን እንዲቆም መፍቀድ የለብንም:: ያለፈውን እንደ ትምህርት ቤት በመጠቀም በአሁን ማንነታችን ላይ መስራት ያስፈልጋል:: መቆጣጠር በምንችለው ነገር ላይ ማተኮር መማር አለብን:: መለወጥ በምንችለው ነገር ላይ አቅማችንን ማፍሰስም ተገቢ ነው።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የህዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


