በነጠላ ጫማ ሮጣ ያሸነፈችዉ

0
16

በሜክሲኮ ራራሙሪ የተሰኘው ነባር ጐሣ ተወላጅ  የሆነችው የ30 ዓመቷ ወጣት በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት በጉዋቾቺ ገደላማ ሸለቆ 63 ኪሎሜትሮችን በሸፈነው “አልትራማራቶን” ባህላዊ ቀሚስ ለብሳ፣ በነጠላ ጫማ ሮጣ በአንደኛነት ማጠናቀቋን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል::

ካንዴላሪያ ሪቫስ ራሞስ በሜክሲኮ ጉዋቾቺ ግዛት ገደላማ ሸለቆ 63 ኪሎ ሜትሮችን በሸፈነው የሴቶች ምድብ ያለ ስፖርት ትጥቅ እና ያለ ዘመናዊ ልምምድ በአንደኛነት ማጠናቀቅ ችላለች::

ወጣቷ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩጫ ውድድር የተሳተፈች ሲሆን በጐሣዋ እምነት መሰረት  ሩጫ ከአካላዊ ጥንካሬ ማግኛነት ባለፈ ከሃያማኖታዊ አስተምህሯቸው ጋር የተገናኘ መሆኑን ነው ተመራማሪዎች ያሰመሩበት::  ሩጫ በደገኞቹ ራራሙሪዎች እንደፀሎት፣ የአምላካቸው ማመስገኛ ተግባር አድርገው እንደሚከውኑት ነው የሚታመነው::

ወጣቷ በውድድሩ ለመካፈል ቅደመ ዝግጅት አላደረገችም፤ እንዲያውም በጐሳዋ በውድድሩ እንድትሳተፍ ተብረታታ ተመርቃ ስትላክም ከመኖሪያ ቀጣናዋ ውድድሩ ቦታ ጉዋቾቺ ለመድረስ 14 ሰዓታት ያለእረፍት ከባለቤቷ ጋር በእግር ተጉዘዋል::

ከዚሁ አድካሚ የእግር ጉዞ በኋላም ባህላዊ የጐሳውን ቀሚስ እና በእጅ የተሰራ ነጠላ ጫማ ተጫምታ ነው የሮጠችው:: በርካታዎቹ ተሳታፊዎች ዘመናዊ ትጥቅ፣ ዓመታትን የፈጀ የልምምድ ዝግጅት እና ልምድ ያላቸው ናቸው- የድረ ገጹ ጽሁፍ እንዳስነበበው:: ካንዴላሪያ ሪቫስ ራሞስ ግን ያለ ዘመናዊ ስልጠና እና ትጥቅ የፍፃሜውን መስመር አልፋ በአንደኛነት አጠናቃለች::

ካንዴላሪያ ከውድደሩ ፍፃሜ በኋላ በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ መካፈሏን እና ድሉ የቤተሰቦችዋም መሆኑን ተናግራለች::

በሀርቫርድ ዩኒቪርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ አጥኚ እና የማራቶን ሯጩ ዳኒኤል ሊበርማን ስለ ራራሙሪዎች ከሌላው  ጐሣ ወይም ዘር የተለየ ብርታት፣ ጥንካሬ እና ፅናት እንዳላቸው እማኝነቱን ሰጥቷል:: ለዚህም መሰረቱ ከእምነታቸው ጋር የተሳሰረ መሆኑን ነው ያሰመረበት::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 26  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here